1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ድባጢ ወረዳ 7 ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኝ ተናገሩ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 17 2013

በድባጢ ወረዳ ሰባት ሰዎች ተገድለው ሬሳቸው መገኘቱን የአካባቢው ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥት በአካባቢው "ሽፍታ ገባ" የሚል ጥቆማ እንደደረሰው አረጋግጧል። በቡለን ከተገደሉ 207 ሰዎች መካከል የስድስት ወር ጨቅላን ጨምሮ 17 ሕፃናት እንደሚገኙበት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታውቋል። 43 ሺሕ በላይ ተፈናቅለዋል

https://p.dw.com/p/3nErX
Karte Äthiopien Metekel EN

የክልሉ መንግሥት 43 ሺሕ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን አስታውቋል

በቤኒሻንጉል  ጉሙዝ  ክልል ድባጢ ወረዳ ትናንት አርብ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት ሰባት ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ የአካባቢው ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። በመተከል ዞን በኩጂ በተባለ ወረዳ በአንድ ቀን 207 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ 43 ሺሕ ሰዎች መፈናቀላቸውን የክልሉ መንግሥት አረጋግጧል። 

በድባጢ ወረዳ ስህረን በተባለ አካባቢ ትናንት አርብ ሌላ ጥቃት መፈጸሙን የአካባቢው ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። "ስህረን ላይ የተገደለው በትክክል የተገኘው ሬሳው ሰባት ነው" ያሉት የዐይን እማኙ ሸሽተው ወደ ጫካ የገቡ በሕይወት ይኑሩ ወይም ይሙቱ እንደማይታወቅ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋሹ ዱጋስ በተጠቀሰው አካባቢ  "ሽፍታ ገባ" የሚል ጥቆማ ለክልሉ መንግሥት እንደደረሰ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። "ስህረን ጎጥ ላይ ጠዋት ወደ አምስት ሰዓት ገደማ ነው ሽፍታ ገብቷል የሚል መረጃ የደረሰን። ሽፍታው ካለ እሱን አጥቅቶ ሕዝቡን ለመታደግ ወዲያውኑ ኃይል ወደዚያ አንቀሳቅሰናል። እስካሁን ምንም የደረሰን ሪፖርት የለም" ሲሉ ተናግረዋል። "በጥቃቱ ምን ያክል ጉዳት ደረሰ? ሕይወት ጠፍቷል? የቆሰለ ሰው አለ? የሚለው ነገር እስካሁን የደረሰን ነገር የለም" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

ባለፈው ረቡዕ 207 ሰዎች በተገደሉበት የመተከል ዞን አሁንም ሥጋት እንዳለ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪ "ዶቢ፣ ባሩዳ እና በኩጂ በጣም ጠንካራ ቀበሌዎች ነበሩ። በኩጂ ላይ ያን ያክል ሲፈጸም የሚያሳዝን ነገር ነው። ከዚያ ባሻገር ደግሞ አሁንም ኃይል እንጠይቃለን። እኛ ጋ ያለ የጸጥታ ኃይል በጣም አነስተኛ ነው" በማለት አሁንም ሥጋት እንዳለ አስረድተዋል። 

ረቡዕ ታኅሳስ 13 ቀን 2013 ዓ.ም በተፈጸመው ጥቃት ከተገደሉ መካከል የስድስት ወር ጨቅላን ጨምሮ 17 ሕፃናት እንደሚገኙበት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታውቋል። ኮሚሽኑ ትናንት አርብ ባወጣው መግለጫ "በጥቃቱ ሕይወታቸው ካለፉ አዋቂዎች መካከል 133ቱ ወንዶች ሲሆኑ 35ቱ ሴቶች ናቸው። አንድ የስድስት ወር ሕጻንን ጨምሮ በጥቃቱ አስራ ሰባት ሕጻናት ተገድለዋል። ቀሪ ሃያዎቹ አዛውንቶች መሆናቸው ተረጋግጧል" ብሏል።  ኮሚሽኑ "ከሟቾች መካከል ሁለቱ በቡለን ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እያለ ታኅሣሥ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. የሞቱ መሆናቸውን" ከቡለን ከተማ የሥራ ኃላፊዎች እንዳረጋገጠ አትቷል። 

የጥቃቱ ሰለባዎች ከትናንት በስቲያ ሐሙስ በጅምላ በአንድ ጉድጓድ መቀበራቸውን ወረዳውአረጋግጧል። የቡለን ወረዳ ኮምዩንኬንሽ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ካሳሁን አዲሱ "ግድያው አሰቃቂ በሆነ መንገድ የተፈጸመ ከመሆኑ እና አስከሬኑም ከቆይታ አንፃር ለቀብር አስቸጋሪ ስለነበረ፤ የሟች ቤተሰቦችም በአብዛኛው ከድንጋጤ እና ከፍርሐት የተነሳ ስላልነበሩ በአካባቢው የቀሩ የሟች ቤተሰቦች፣ ከሁሉም የዕምነት ተቋማት መሪዎች እና የአገር ሽማግሌዎች በመረጡት ቦታ የቀብር ሥርዓቱ ተፈጽሟል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከአካባቢው እንደተፈናቀለ አረጋግጧል።  በኮሚሽኑ መረጃ መሠረት ጭላንቆ፣ በኩጂ፣ ዲሽባኮ እና ባር ከተባሉ የቡለን ወረዳ አራት ቀበሌዎች የተፈናቀሉ ከ500 የሚበልጡ ሰዎች በጋሌሳ ቀበሌ በሚገኝ የአውቶቡስ መናኃሪያ ተጠልለው ይገኛሉ።

"በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀበሌውን ጥለው ከ40 ኪ.ሜ. በላይ በእግራቸው በመጓዝ ወደ ቡለን ከተማ በመግባት ላይ ይገኛሉ" ብሏል። "በቡለን ከተማ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና አንድ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ግቢ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ተጠልለዋል" ያለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን "አፋጣኝ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ" አሳስቧል። 

ረቡዕ ማለዳ ከተፈጸመው "ጭፍጨፋ" በኋላ ወደ 43 ሺሕ ገደማ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ  ክልል የአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽነር ታረቀኝ ታሲሳ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  "በሰሞኑ ከ43 ሺሕ በላይ ሰዎች ናቸው የተፈናቀሉት። ዲባጢ ወረዳ ጋሌሳ፣ ቡለን ከተማ እና በቆጂ የሚባል ቦታ ላይ ነው [ተፈናቃይ] ዜጎች እየተሰበሰቡ ያሉት" ብለዋል። 
ኃላፊው በአካባቢው በተፈጠረው ቀውስ ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ጉዞ የጀመሩ ተሽከርካሪዎች ከታሰበው መድረስ ሳይችሉ ቀርተው መንገድ ላይ መቆማቸውንም ተናግረዋል።አቶ ታረቀኝ "ቻግኒ ላይ አምስት መኪናዎች ለሁለት ቀን ቆመዋል። እንደዚሁም ግልገል በለስ ከተማ ላይ ሁለት መኪናዎች ቆመዋል" ብለዋል። 

ነጋሳ ደሳለኝ
እሸቴ በቀለ