1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል114 ኢንቨስተሮች የተበደሩትን ገንዘብ ይዘው ተሰወሩ

ሐሙስ፣ ሰኔ 9 2014

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል114 ኢንቨስተሮች ከልማት ባንክ 2 ቢሊዬን ብር ብድር ወስደው ወደ ስራ ሳይገቡ መሸሻቸውን የክልሉ ገጠር መሬት አስተዳደርና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በባለ ሀብቶች ለልማት የተወሰደው 69ሺ ሄክታር መሬት ሳይለማ መቆዩቱን የቢሮው ኃላፊ አቶ አመንቴ ግሺ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4Cmrb
Äthiopien Benishangul Region, Stadt  Metekel
ምስል Negassa Dessakegen/DW

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የተበደሩ ባለሃብቶች ተሰወሩ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል114 ኢንቨስተሮች ከልማት ባንክ  2 ቢሊዬን ብር ብድር  ወስደው ወደ ስራ ሳይገቡ  መሸሻቸውን የክልሉ ገጠር መሬት አስተዳደርና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በባለ ሀብቶች ለልማት የተወሰደው 69ሺ ሄክታር መሬት ሳይለማ መቆዩቱን የቢሮው ኃላፊ አቶ አመንቴ ግሺ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  የጸጥታ ችግር በለለባቸው የክልሉ ስፍራዎች በማዕድን ዘርፍ የተሻለ ምርት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡ 22 ኩንታል ወርቅ እስካሁን ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱንም አክለዋል፡፡በክልሉ ወርቅ፣ድንጋይ ከሰል፣መዳብ፣እምነበረድ፣እጣን ምርትና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ይገኛሉ፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በርካታ ባለሀብቶች በእርሻ ኢንቨስትመንትና የተለያዩ የተፈጥሮ ማዕድን ልማት ዘርፍ በዘንድሮ ዓመት መሰማራታቸውን የክልሉ  የገጠር መሬት አስተዳደርና ኢንቨስትመንት ቢሮ አመልክቷል፡፡ በክልሉ በአሁኑ ጊዜ 9 መቶ የሚደርሱ ባለሀብቶች በተለያዩ ስራ ዘርፎች ተሰማርተው እንደሚገኙ የቢሮው ኃላፊ አቶ አመንቴ ግሺ ለዶቼቨሌ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ባለሀብቶች መካከል 114 የሚደርሱት  ከልማት ባንክ  ብድር ወስድው ወደ ስራ ሳይገቡ መቆየታቸውን አብራርተዋል፡፡ ባለሀብቶቹ ወደ ስራ ባለመግታቸውና መሬቱ ባለመልማቱ የክልሉ መንግስት በሚሊዩን የሚቆጠር ገንዘብ  የመሬት ግብር ማጣቱንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በዘንድሮ ዓመት ከፍተኛ የእርሻ ኢንቨስትመንትና የማዕድን ሀብት መነቃቃት እየተስዋለ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን  በክልሉ 12 ዓይነት የማዕድነት ሀብቶች እንደሚገኙም የክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አመንቴ ግሺ አስታውቋል፡፡ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በማዕድኑ ዘርፍ በርካታ ወጣቶች መሰማራታቸውን ገልጸው 10 የተደራጁ ማህበራት ደግሞ በቅርብ በክልሉ በእርሻ ኢንቨስትመንት መሰማራታቸውን አክለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን በክልሉ ምክር ቤት 13ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በመጋቢት ወር/2014ዓ.ም  በሰጡት ማብራሪያ በባህላዊ የወርቅ አምራቾች በኩል ከ1ሺ ኪ.ግ በላይ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱንም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ የእርሻ ኢንቨስትመንትና ማዕድን ዘርፈ ልማት 4 መቶ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች መሰማራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ ከዚህ ቀደም በኢንቨስትመንት ስራ የተሰማሩ እና መሬት አስይዘው ያላለሙ እና ለተገቢው ዓላማ ላይ ያላዋሉ ባለሀብቶችን የማጥራት ስራ እንደሚሰራም ቢሮው አመልክተዋል፡፡ የክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና ኢንቨስመንት ቢሮ ባለሀብቶች በክልሉ የተለያዩ ስራ አማራጮች እንዲሰማሩ ባቀረበው ጥሪ መሰረት 74 የዲያስፖራ አባላት በታህሳስ ወር በአሶሳ በመገኘት በእርሻና ሆቴል ዘርፍ ለመሰማራት ጥያቄ ማቅረባቸውም ተገልጸዋል፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሠ