1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቤኒሻንጉል እና አማራ ክልሎች አዋሳን አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት 11 ሰዎች ተገደሉ

ሐሙስ፣ ግንቦት 13 2012

ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ በአዊ ብሔረሰብ ዞን ዚገምና ጓንጓ ወረዳ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት 11 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና ከ60 በላይ መኖሪያ ቤቶችም  መቃጠላቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ ከአራት  መቶ  በላይ ሰዎች  ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድባጤ ወረዳ ሸሽተዋል።

https://p.dw.com/p/3caIg
Karte Äthiopien Metekel EN

በቤኒሻንጉል እና አማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ግጭት የሰዎች ሕይወት አጠፋ

ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ በአዊ ብሔረሰብ ዞን ዚገምና ጓንጓ ወረዳ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የ11 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና ከ60 በላይ መኖሪያ ቤቶችም  መቃጠላቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ ከአራት  መቶ  በላይ ሰዎች  ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድባጤ ወረዳ መሸሻቸውንና ተፈናቃዎቹ በወረዳው አምስት ቀበሌዎች ተጠልለው እንደሚገኙ በመተከል ዞን የድባጤ ወረዳ የሚሊሻ ኃላፊ አቶ ያደታ ጌታቸው ተናግረዋል።  የአዊ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር የህዝብ ግንኙትነት ቡድን መሪ የሆኑት ወ/ሮ ጠጄ ዎሌ በበኩላቸው በዝገም ወረዳ ግጭት ተቀስቅሶ በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡ የአካባቢው ኮማንድ ፖስት በበኩሉ ጉዳዩን እየተከታተለ እንደሚገኝ ለዶይቸ ቬለ በስልክ ተናግረዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና አማራ ክልል አዊ ብሔሰረብ ዞን አዋሳኝ በሆነው ዝገም ወረዳ ጹሊ በተባለ ቀበሌ ከብት ዘርፋችኋል በሚል በተፈጠረ አለመግባባት ባለፈው ቅዳሜ  ግጭት መቀስቀሱንና በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን አንድ ከወረዳ ሸሽተው በመተከል ዞን ድባጢ ወረዳ እንደሚገኙ የነገሩን የአካባቢው ነዋሪ ጠቁመዋል፡፡ በተፈጠረው ግጭት የስምንት ሰዎች ሕይወት ወዲያ ሲያልፍ በርካታ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደ ጫካ መሸሻቸውን ተናግረዋል፡፡ እሁድ ቀጥሎ የዋለው ግጭቱ ወደ ጓንጓ ወረዳ በመስፋፋት ኢማሊ በተባለ ቀበሌ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን  አክለዋል፡፡ ሌላው የጓንጓ ወረዳ ነዋሪ እንደተናገሩት ቅዳሜና እሁድ በነበረው አለመረጋጋት ኢማሊ በተባለና ሌሎችም ስፋራዎች ላይ በደረሰው ጥቃት የሶስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ 80 የሚደርሱ  ከብቶችም መዘረፋቸውን እና 40 ጎተራዎች  መቃጠላቸውን አመልክተዋል፡፡

በመተከል ዞን የድባጤ ወረዳ አስተዳደር ሚላሻ ኃላፊ የሆኑት አቶ ያደታ ጌታቸው በበኩላቸው ከአራት መቶ በላይ  የአዊ ብሔረሰብ ዝገምና ጓንጓ ወረዳ ነዋሪዎች በግጭቱ ምክንያት ተፈናቅለው በድባጤ ወረዳ ሞጋ፣ሲርባ እና ሌሎችም አምስት ቀበሌዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው ማሕበረሰብ ጊዜያዊ ድጋፎች እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በአማራ ክልል የአዊ ብሔረሰብ  ዞን አስተዳዳር የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ የሆኑት ወይዘሮ ጠጄ ዎሌ ሰሞኑን በዞናቸው ስር በሚገኘው ዚገም ወረዳ በተፈጠረው ግጭት የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፍን በስልክ አብራርተዋል፡፡ ባለፈው ወር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ህገ ወጥ እንቅቃሴዎች በመበራከታቸው ዜጎች በሰላም ወጥቶ በሰላም እንድገቡ ለማስቻልና የተፈናቁሉ ዘጎችን ወደ ቄአቼው ለመመለስ ኮማንድ ፖስት ተቋቋሞ ስራ መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡ የኮማንድ ፖስቱ ኃላፊ ኮሎኔል መሐመድ ሐሰን በአካባቢው የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመቅረፍና ወንጀሎኞችን ለመያዝ  ጉዳዩን የሚያጣሩ የጸጥታ ሀይሎች ወደ አካባቢው መላካቸውን ጠቁመዋል፡፡ በግጭቱ ምክንያምት ከአካባቢው ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል  የሸሹ መኖራውንም አረጋግጠዋል፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ 

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ