1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በባሌ መንገድ በየጊዜው አደጋዎች የሚከፉበት ሰብስቤ ዋሻ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 19 2015

ባለፈው ቅዳሜ በኦሮሚያ ክልል ሰብስቤ ዋሻ በተባለ ቦታ ተሽከርካሪ ገደል ገብቶ 16 የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን ጨምሮ የ20 ሰዎች ሕይወት አልፏል። ከአደጋው የተረፉ መምህር እንደሚሉት አስቸጋሪው ቦታ ተደጋጋሚ አደጋ የሚከሰትበት ነው። ከዓመት በፊት 18 ሰዎች የጫነ ተሽከርካሪ በቦታው አደጋ እንደደረሰበት የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል

https://p.dw.com/p/4RtHi
Karte Äthiopien Ethnien EN

በባሌ መንገድ በየጊዜው አደጋዎች የሚከፉበት ሰብስቤ ዋሻ

ልክ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ ግንቦት 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሮቤ ተነስቶ ወደ ዶዶላ ሲያመራ የነበረው እስከነ ሾፌርና ረዳት 51 ሰዎችን ያሳፈረው “ሳንሎንግ” የተሰኘው የመዳ-ወላቡ ዩኒቨርሲቲ አውቶብስ በባሌ ተራሮች በተለምዶ “ሰብስቤ ዋሻ” በሚባል አከባቢ ተግልብጦ ወደ ገደል በመግባቱ የ20  ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ እንዲቀጠፍ እና በርካቶች የከፋ ጉዳት እንዲያስተናግዱ ምክኒያት ሆነ፡፡ 16 የዩንቨርሲቲው መምህራን፣ 2 ተማሪዎች እንዲሁም ሾፌርና ረዳትን ጨምሮ 20 ሰዎች የተቀጠፉበትን አደጋ በተሽከርካሪው ውስጥ ሆነው የተመለከቱትና በተዓምር ከአደጋው መትረፋቸውን የሚገልጹት የዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ረዳት ፕሮፈሰር አያለው ለማ፤ በወቅቱ የሆነውን እንዲህ ለዶቼ ቬለ አስረድተዋል፡፡

“ከማለዳው 11፡30 ሰዓት ከሮቤ ወጥተን 1፡15 ገደማ በተለምዶ ሰብስቤ ዋሻ ስንደርስ መኪናው ቆመ፡፡ ያው እኛ ለእረፍት መስሎን ወርደን እየተናፈስን ነበር፡፡ ሾፌሩ ግን ከረዳቱ ጋር ወርደው መኪናው በማስቸገሩ ለ10 ደቂቃ ገደማ ስጎረጉሩት ነበር፡፡ ተመልሰን ገብተን መኪናው ከተነሳ በኋላ አልታዘዝ ብሎት ስታገል ነበር ሾፌሩ፡፡ መኪናው ከልክ በላይ ቁልቁለቱን መፍጠን ጀመረ፡፡ ከ100-200 ሜትር ገደማ ከተጓዘ በኋላ ኩርባ ላይ ወደ ቁልቁለቱ ለቀቀው፡፡ ለደቂቃዎች አየር ላይ ከተንሳፈፍን በኋላ ነበር በመጨረሻም መኪናውም ተገነጣጥሎ መሬት ላይ የደረስነው፡፡”

ከአደጋው የተረፉ እኚህ መምህር እንዳሉን፤ በተሽካርካሪው ውስጥ ከነበሩት 51 የዩኒቨርሲቲው ባልደረቦች ከ40 በላይ የሚሆኑቱ መምህራን ናቸው፡፡ እሳቸውን ጨምሮ ቀላል አደጋ ያስተናገዱት ከ10 የማይበልጡ ናቸው የሚሉት መምህሩ፤ ከሞቱት 20ዎቹ በተጨማሪ ቀሪዎቹ ከባድ አደጋ ማስተናገዳቸውንም በአይናቸው የተመለከቱትን ገልጸዋል፡፡

“እነ ከመኪናው ውጪ ነው ከነወንበሩ እራሴን መሬት ላይ ያገኘሁት፡፡ ወዲያው ቆምኩና ለዩኒቨርሲቲው ደወልኩ፡፡ ሳይ ሰውነቴን ትንሽ እግሬ ላይ ስጋ ከመቆረጡ ውጭ ደህና ነኝ፡፡ አንድ ስድስት ሰዎችም ቀለል ለ ጉዳት ብቻ አስተናግደው ተነስተው ሲሮጡ ተመልክቻለሁ፡፡ ሌሎች ግን እጅግ ከፋ አደጋ ነው ያስተናገዱት፡፡”

እንደመምህሩ በዚን ቀን የተጓዙባት መኪና በብዛት የቴክኒክ ችግር ያለባት እና በብዙዎች የማትፈለግም ነበር፡፡ አደጋው የተፈጠረበት ቦታም ሁል ጊዜም ተመሳሳይ አደጋ የሚዘወተርበት እንደነበር በማከል፡፡ “መኪናዋ ከሌሎች ትለያለች፡፡ በሌሎች መኪና 11፡30 ተነስተን በ2 ሰዓት ውስጥ ዶዶላ ስንደርስ በዚህች ግን በ3 ሰዓትም አንደርስም ሁሌም፡፡ መኪናዋ አስቀድሞም ትረብሽ ነበር፡፡ ቦታውም ለአደጋው የራሱ አስተዋጽኦ ያለው መስለኛል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ አራት መኪናዎች ገብተው ወድመዋል፡፡”

አቶ ለገሰ መርጋ ደግሞ በአዳባ ወረዳ ወሻ ቀበለ በዚሁ የመኪና አደጋ ይዘወተርበታል በሚባል ስፍራ ለዓመታት ኖረዋል፡፡ የአደጋው እዛ ቦታ በየጊዜው መደጋገም ለዓመታት የአከባቢውን ማህበረሰብ ሲያስለቅስ መዝለቁንም አንስተውልናል፡፡ “በፊት መንገድ በጠጠር የተሰራ ነበር፡፡ ወደ አስፓልትነት ሲያድግም ኩርባው በበቂ ሁኑታ ሰፍቶ አልተሰራም ነበር፡፡ ወደ ገደለም መከላከያ የለውም፡፡ ልክ ይህ የአሁኑ አደጋ በተከሰተበት ቀን ከአንድ ዓመት በፊትም አንድ 18 ሰው የጫነ ሚኒባስ መኪና ማንም ሳይወጣ ነው ገደሉ ውስጥ ገብቶ የቀረው፡፡ እኛ በዚ እየኖርን 32 ተሸከርካሪዎች እዚያ ገብተው ሲቀሩ አይተናል፡፡ ዘላለም እያለቀስን ነው የምንኖረው፡፡ መቼ እልባት እንደምንሰጠው አናውቅም፡፡”

ስለዚህ አደጋ ክስተትና ስለዘለቄታዊው መፍትሄ ተጨማሪ አስተያየቶችን ከመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ እና ከኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት ግን ለዛሬ አልሰመረም፡፡

ሥዩም ጌቱ 

እሸቴ በቀለ