1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በባሕር ዳር ለ1000 ሰዎች የዓይን ቀዶ ህክምና ተደረገ

ዓርብ፣ ሰኔ 10 2014

በአማራ ክልል የባሕርዳር ፈለገ ህይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሂማሊያን ካታራክት ፕሮጀክት ከተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ሰሞኑን በአካሄደው የዓይን ሞራ ህክምና ከ1000 በላይ ህሙማን መታከማቸውን ባለሙያዎችና ታካሚዎች ተናግረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4CoYp
Äthiopien Augenoperation in Bahir Dar Felege Hiwot Krankenhaus
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በባህርዳር ከተማ ከ1000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች የአይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና ተሰጠ

በአማራ ክልል የባሕርዳር ፈለገ ህይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሂማሊያን ካታራክት ፕሮጀክት ከተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ሰሞኑን በአካሄደው የዓይን ሞራ ህክምና ከ1000 በላይ ህሙማን መታከማቸውን ባለሙያዎችና ታካሚዎች ተናግረዋል፡፡
ሂማሊያን ካታራክት የተባለው ግብረሠናይ ድርጅት በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜዎችና አካባቢዎች የዓይን ሞራ ህክምና በመስጠት ለብዙዎች የዓይን ብርሃናቸውን እንዲያገኙ ከፍተኛ እገዛ ሲያደርግ እንደነበር የዓይን ህክምና ስፔሽሊስትና የሂማሊያን ካታራክት ፕሮጀክት ባልደረባ ዶ/ር ህይወት ደግንህ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
ከጥቅምት 29 እስከ ሰኔ 6/2014 ዓ ም በተደረገው የዓይን ሞራ ህክምና 1052 ታማሚዎች ታክመው የዓይን ብርሀናቸውን ማግኘት መቻላቸውንም ዶ/ር ህይወት ተናግረዋል፡፡
ሥራውን ሂማሊያን ካታራክትና ሆስፒታሉ በጋራ እንዳከናወኑትም ባለሙያዋ አመልክተዋል፡፡
የህክምና አገልግሎቱን ያገኙት በቅርብ የሚገኙ የክልሉ ነዋሪዎች እንደሆኑም ዶ/ር ህይወት ገልጠዋል፡፡
ህክምናው በቡድን እንደተከናወነና በርካታ ባለሙያዎች እንደተሳተፉበት ደግሞ በህክምናው ላይ ሲሳተፉ ገኘናቸው በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የዓይን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ማትያስ ጥላሁን አስረድተዋል፡፡
ከህክምና በኋላ ታካሚዎች ስሜታቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲገልፁ መመልከታቸውንም ባለሙያው ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
ከታካሚዎች መካከል የአንዳንዶቹን በሰጡት አስተያየት ለዓመታት በጨለማ መቆየታቸውን አስታውሰው አሁን በተደረገላቸው ህክምና ዓይናቸው ማየት በመቻሉ በእጅጉ ተደስተዋል፡፡
የዓይን ሞራ ግርዶሽ እይታን የሚጋርድ ችግር ነው፣ መነሻው በዋናነት የዕድሜ መግፋት ሲሆን የስኳር ህመምና ሌሎች መድኃኒቶች የሚፈጥሩት ጫና እንደሆነና በሁሉም የዕድሜ ክልል  ያሉ ሰዎችን የሚያጠቃ ህመም መሆኑን ባለሙያዎች አመልክተዋል፡፡
በአማራ ክልል ከ1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ዝቅተኛ የዓይን ብርሃን ያለባቸው ሲሆኑ፣ 300 ሺህ ያህሉ ደግሞ በዓይን ሞራ ግርዶሽ ሙሉ በሙሉ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ እንደሆኑ የዓይን ህክምና ስፔሻሊስቷ ዶ/ር ህይወት ደግነህ ገልጠዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሠ