1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

በበረዶ ዘመን በባሌ ተራራ ሰዎች እንደኖሩ በጥናት ተረጋገጠ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 8 2011

የሰው ልጅ አመጣጥን የሚያጠኑ ኢትዮጵያውያንም ሆነ የውጭ ተመራማሪዎች ቅሪተ አካሎችን እስካሁን ሲያገኙ የቆዩት በሸለቆማ ቦታዎች ነበር። በኢትዮጵያውያን እና የውጭ ሀገር ባለሙያዎች ትብብር በቅርቡ የተደረገ አንድ እና በዚህ ሳምንት ጥናት ግን የሰው ልጅ በበበረዶ ዘመን በተራራማ ቦታዎች ይኖር እንደነበር አረጋግጧል።

https://p.dw.com/p/3Nu5q
Äthiopien Wald
ምስል Imago/blickwinkel

በበረዶ ዘመን በባሌ ተራራ ሰዎች እንደኖሩ በጥናት ተረጋገጠ

ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ስትጠቀምበት የቆየችውን “የ13 ወር ጸጋ” የተሰኘውን የቱሪዝም መለያውን ወደ “ምድረ ቀደምት” ስትቀይር ኩሉሲ እስከ ቡና መገኛነቷን ተማምና ነው። ሉሲን የተከተሉት አርዲ፣ ሰላምም ሆነች ኢዳልቱ በእርግጥም ሀገሪቱ የቀደምቶች ሀገር ለመሆኗ ምስክር ሆነዋል። በዚህ ሳምንት ይፋ የተደረገ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ የሆነ አዲስ የምርምር ውጤትም ሀገሪቱ የጥንታውያን ሰዎች መኖሪያ እንደነበረች ተጨማሪ ማረጋገጫ ሰጥቷል። 

የሰው ልጅ ከበርካታ ሺህ ዓመታት በፊት እንዴት እና የት ይኖር እንደነበር ያመለከተው ይህ ጥናት የተደረገው ከሰው ልጅ አመጣጥ ምርምር ጋር ስሟ ተደጋግሞ በሚነሳው በአፋር አይደለም። በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ በምትገኘው በባሌ እንጂ። በአዲስ አበባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የእጽዋት ባዮሎጂ እና የባዮዳይቨርስቲ ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ስለሺ ነሞምሳ በጥናቱ ላይ ከተሳተፉ ስምንት ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች አንዱ ናቸው።

Äthiopien Feuer im Nationalpark Bale Berge
ምስል Ethiopian Wildlife Conservation Authority

“በባሌ ተራራ ላይ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ጥናት ሲካሄድ ነበር” የሚሉት ፕሮፌሰር ስለሺ “በረዶ በነበረበት ዘመን በተለይ ወደ ኋላ አካባቢ ሰዎች እዚያ ይኖሩ ነበር። በተለይ በፊንጫ ሀበራ በሚባል ቦታ ከ31 ሺህ እስከ 47 ሺህ ዓመት በፊት ሰዎች በተደጋጋሚ ይኖሩ እንደነበር የሚገልጹ መረጃዎች ናቸው የተገኙት” ሲሉ በጥናቱ ምን አዲስ ነገር እንደተገኘ ያስረዳሉ። 

የቅድመ ሰው ዘር ታሪክ አጥኚዎች ቅሪተ አካሎችን ያገኙባቸው እንደ ሀዳር እና ዲቃቃ ያሉ አብዛኞቹ ቦታዎች ሸለቋማ ናቸው። የባሌ ተራራውን ጥናት የወጠኑት ተመራማሪዎች ግን ከዘመናት በፊት በምድር ላይ ይመላለሱ የነበሩት ሰዎች ከፍ ባሉ ተራራማ ቦታዎች ይኖሩ እንደው ለማወቅ ነበር የተነሱት። በምርምሩ የተሳተፉት እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአርኪዮሎጂ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶ/ር አለምሰገድ በልዳዶስ አንዳንድ ጊዜ የከባቢ አየሩ በሚያስቸግርበት ወቅት የሰው ልጅ ወደ ተራራማ ቦታዎች የመሸሽ አካሄድ ይከተል ነበር ይላሉ።  

“ታችኛው የመሬት ክፍል፣ ሸለቆው በማይመችበት ጊዜ፣ climatic aridity በሚኖርበት ጊዜ የሰው ልጅ ወደ ተራራማ ስፍራዎች ይሸሻል። ይሄ ማለት ምን ማለት ነው? በማያቋርጥ ሁኔታ የሰው ልጅ በአንድ አይነት መልዕከ ምድር ላይ ብቻ አይደለም የከተመው ማለት ነው። ተራራማ ስፍራዎችንም ይጠቀሙባቸው ነበር። ግን ተራራማ ስፋራዎች ላይ በስፋት ይኖር እንደነበር የሚያስችል መረጃ አልተገኘም ነበር። ይህንን መረጃ ነው እኛ ያገኘነው” ይላሉ ዶ/ር አለምሰገድ።

የሰው ልጅ በተራራዎች ላይ መኖር የጀመረው ከቅርብ ሺህ አመታት ወዲህ ነው ተብሎ ለረዥም ጊዜያት ይታመን ነበር። በደቡብ አሜሪካዊቷ ፔሩ፣ በኤንዲስ ተራራ ላይ ቁፋሮ ሲያደርጉ የቆዩ አርኪሎጂስቶች በጎርጎሮሳዊው 2014 ይህንን እምነት የሚያፋርስ ግኝት አስተዋውቀዋል። ከባህር ጠለል 4,500 ሜትር ከፍታ ባለው ቦታ ላይ ምርምራቸውን ሲያካሄዱ የቆዩት አጥኚዎች የሰው ልጅ በዚያ ቦታ የዛሬ 12 ሺህ ዓመት ገደማ በፊት ይኖር እንደነበር ማስረጃዎች አግኝተዋል።ከሶስት ዓመት ቆይታ በኋላ ደግሞ ሌሎች ተመራማሪዎች የሰው ልጅ ከዚያም ቀደም ብሎ በተራራ ሰፍሮ እንደነበር የሚያረጋግጥ የምርምር ውጤት ይዘው መጡ። እነዚህኞቹ ምርምራቸውን ያካሄዱት በሩቅ ምስራቋ የቻይና ግዛት ቲቤት ነበር። የጥናታቸውም ውጤት ቲቤቲያውያን ከ12,600 ዓመት በፊት በሂማሊያ ተራራ ላይ ሰፍረው እንደነበር በተጨባጭ የሚያረጋግጥ ሆነ። የባሌ ተራራው የምርምር ውጤት ከሁለቱ የጥናት ግኝቶች በምን ይለያል? ዶ/ር አለምሰገድ ምላሽ አላቸው።

Andengletscher
ምስል ddp images/AP Photo/Karel Navarro

“የእኛ የባሌውን ጥናት ለየት የሚያደርገው አንደኛ በተደጋጋሚ የሰው ልጅ  የሰፈረበት፣ የኖረበት ቦታ መሆኑ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ሲከትሙ ምን አይነት የምግብ ምንጭ እንደነበራቸው የሚያሳይ መረጃ ይዘን በመውጣታችን ነው ለየት የሚያደርገው። በተጓዳኝም ብዙ መረጃዎችም ሰብሰበናል። ለምሳሌ በዚያ አካባቢ ይኖሩ የነበሩት፤ ማህበረሰቦች ልበላቸው፤ በተደጋጋሚ እሳት እንደሚጠቀሙ ከነበረው የከሰል (charcoal) ክምችት ማየት ይቻላል። 

ከባልጩት (obsidian) እንደ ጥሬ ዕቃ በመጠቀም የድንጋይ መሳሪያዎችን ሲያመርቱ እንደነበር መረጃ አለን። ይሄ መረጃ ስልህ ደግሞ በጣም ብዙ መረጃ ነው። ለምሳሌ በትንሹ ስለ ድንጋይ መሳሪያው ብነግርህ ከ1,011 በላይ የድንጋይ መሳሪያዎች የተቆጠሩት። ሌሎችም አይነት የእንስሳት ቅሪተ አካሎች ተገኝተዋል። እንደ ብርቅየው የተራራ ኒያላ፣ ባቡን፣ ቀበሮ እንደ እነዚህ አይነት ተጓዳኝ ግኝቶች አሉ። ይሄ የሚያመለክተው ምንድነው? የሰው ልጅ ተራራማ ቦታ ላይ መስፈሩ ብቻ ሳይሆን በጣም ለረዥም ጊዜ አለማቋረጥ ባሌ ተራራ ላይ መክተሙን የሚያሳይ የግኝት ውጤት ስለሆነ ለየት ያደርገዋል፤ ብዙም መረጃ የሚሰጥ የጥናት ውጤት ነው” ይላሉ ዶ/ር አለምሰገድ። 

በአጠቃላይ ሃያ ሁለት ተመራማሪዎች የተሳተፉበት የእዚህ ጥናት ውጤት “ሳይንስ” በተሰኘው የምርምር ውጤቶች በሚታተሙበት ጆርናል አማካኝነት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ለንባብ በቅቷል። የጥናት ውጤቱ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት እንዲስብ ካደረጉት ምክንያቶች የ“በረዶ ዘመን” ተብሎ በሚታወቀው ወቅት ሰዎች በተራራ ሰፍረው እንደነበር ያመላከተ በመሆኑ ነው። እንኳን በዚያ ዘመን አይደለም በአሁኑ ወቅትም የሰው ልጅ፤ ከፍታቸው ከባህር ጠለል ከሶስት ሺህ ሜትር በላይ በሆኑ፤ እንደ ባሌ ባሉ ተራራዎች ለመኖር እንደሚቸገር የሚያውቅ ከ30 እና 40 ሺህ ዓመታት በፊት በዚያ ቦታ የነበሩት ሰዎች እንዴት ሁሉን ተቋቁመው ኖሩ የሚል ጥያቄ ማንሳቱ አይቀርም። “ፕሌስቶሴን” የሚባለውን ዘመን ምንነት በማስረዳት የሚንደረደሩት ዶ/ር አለምሰገድ በጥናቱ ውጤት ላይ ተመርኩዘው በዚያን ዘመን በባሌ ተራራ የነበረውን ሁኔታ ያብራራሉ። 

Neandertaler Jagt auf Höhlenbär
ምስል imago/StockTrek Images/J. Faro

“ፕሌስቶሴን (pleistocene) የሚባለው በጂኦሎጂክ የጊዜ መለከያ መሰረት ከ1.8 ሚሊዮን እስከ 10 ሺህ ዓመት ያለው ዘመን ነው። ይሄ በብዛት በምንድነው የሚታወቀው አብዛኛው የመሬት ክፍል በበረዶ የተሸፈነበት ዘመን ስለነበረ ነው። ግን ሁሉም ቦታ በበረዶ ተሸፍኗል ማለት አይደለም። ለምሳሌ አሁን የፊንጫ እና የሀቤራ ዋሻ ከበረዶ ግግሩ ዝቅ ባለው አካባቢ ላይ ነው የሚገኘው። ወደ 3,469 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ነው ያለው። ይሄ የበረዶ ግግሩ በብዛት አይነካውም ነበር። 

ሌላ ደግሞ በበረዶ ዘመን የሚኖረው የሰው ልጅ ዝርያ ተብሎ የሚታወቀው ሆሞ ኤሬክተስ (homo erectus) ይባላል። ሆሞ ኤሬክተስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአፍሪካ ወጣ የሚባለው፣ ወደ አውሮፓ የሄደው ዘጠኝ መቶ ሺህ፣ አንድ ሚሊዮን ዓመት አካባቢ ነው። ወደ አውሮፓ፣ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሲሄድ ያጋጠመው የከባቢ አየር በጣም ቀዝቃዛ ነው። ያንን በምንድነው ሊቋቋመው የቻለው በእሳት ነው። የሰው ልጅ እሳትን የዛሬ 750 ሺህ፣ 800 ሺህ ዓመት አካባቢ ነው ያገኘው። የእሳት መገኘት ደግሞ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው። ለሰው ልጅ ሙቀትን ይሰጠዋል፣ ከአውሬዎች ይከላከልለታል። 

አሁን ይሄንን ወደ ባሌ ተራራ ባመጣልህ ብዙ ከሰል ይጠቀሙ ነበር። ያ ደግሞ ተጨማሪ ሙቀት ይፈጥርላቸው ነበር ማለት ነው።  ያ ማለት ምን ማለት ነው? ሰውነታቸውም ለምዶ ያንን አካባቢ መላመድ ችሏል። ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ በሂደት የፈጠራቸውን የድንጋይ መሳሪያ ግኝቶች፣ ከእንደገና ደግሞ የእሳት ግኝቶች እንደ ባህል ለውጥ መገለጫ (cultural evolution) አድርገን ብናየው የነበረውን የቅዝቃዜ ተጽዕኖ ተቋቁመው መኖር አስችሏቸው ነበር” ሲሉ ዶ/ር አለምሰገድ ሰፋ ያለ ገለጻቸውን ይቋጫሉ። 

በባሌ ተራራ ከትመው የነበሩ ሰዎች ስፍራውን እንዲመርጡ ካደረጋቸው ምክንያቶች አንዱ ለምግብነት ሲጠቀሙበት የነበረውን እንስሳ በቦታው ላይ እንደልብ ማግኘታቸው እንደሆነ ተመራማሪው ያስረዳሉ። በቁፋሮ የተገኙ አጥንቶችም የዚያን ጊዜ ሰፋሪዎች ምግባቸውን እንዴት ያዘጋጁ እንደነበር ጭምር ማመላከታቸውን ፕሮፌሰር ስለሺ ይገልጻሉ። “አሁን ባሌ ተራሮች ላይ እንደ ብርቅዬ እንስሳ ነው ያለው። የአይጥ (rodents) ዘር ውስጥ  ትልቁን አይጠ መጎጥ የሚባለውን (mole-rates) እርሱን ነው [ይመገቡ የነበረው]። ትልቁ ለምሳሌ አንድ ኪሎ ግራም ይመዝናል። እና እርሱን ሲበሉ እንደነበርና አዘገጃጀት መንገዳቸውም አሁን በጥናቱ ከተገኙ አጥንቶች የታወቀ ነው ማለት ነው። ያ ደግሞ ምንድነው? ጠብሰው ይበሉ እንደነበር ነው። ይሄ እንግዲህ የተቃጠሉ አጥንቶች ስለተገኙ ያንን ያመለክታል ማለት ነው” ይላሉ ተመራማሪው።

Äthiopien Universität Adis Ababa
ምስል picture alliance/robertharding/M. Runkel

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ከአራት የጀርመን እና ከአንድ የስዊዘርላንድ ዩኒቨርስቲዎች ጋር ያጣመረው በባሌ ተራራ የተካሄደው ጥናት ቀጣይነትእንዳለው ተነግሯል። በባሌ ተራራ በብዛት የሚገኘው የአስታ እጽዋት በጥንት ጊዜ የነበረው ስርጭት በምርምሩ ሁለተኛ ምዕራፍ እንደሚጠና ፕሮፌሰር ስለሺ ይናገራሉ። “አስታ በተለይ ሳኔቲ ላይ አለ። በመሃላቸው ደግሞ የእዚህ የሳኔቲ ጠፍጣፋ ቦታ አለ። ከታች ደግሞ አስታ አለ እና ያኛው የድሮው ሽፋኑ ምን ያህላል? የሚለውን ለማወቅ ነው። እና ሰው ብዙውን ጊዜ እዚያ እንደሚኖር የሚያመላክተው ታች እንደነበሩ ነው። ከዚያ በላይስ ይኖራሉ ወይ? የሚለውንም አጣምሮ የሚያይ ነው ሁለተኛው ምዕራፍ” ይላሉ ።

ዘርፈ ብዙ ባለሙያዎች ባካተተው የባሌ ተራራው ጥናት አርኪዮሎጂስቶች፣ የአፈር ተመራማሪዎች፣ ፓሌኤኮሎጂስቶች እና ባይሎጂስቶች በየሙያ ዘርፋቸው ያለውን ክፍል ሲያጠኑ ቆይተዋል። በሁለተኛው ምዕራፍም ይሄው አካሄድ እንደሚቀጥል ዶ/ር አለምሰገድ ይገልጻሉ። የፕሮፌሰር ስለሺን ገለጻ ተንተርሰው በሁለተኛው ምዕራፍ ከእርሳቸው የጥናት ዘርፍ ምን እንደሚጠበቅ ያስረዳሉ። 

“እነርሱ የከባቢ አየር ሁኔታውን፣ የአካባቢ ስርጭቱን ሲመለከቱ እኛ ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ cultural የሆነውን በደንብ እናጠናለን። ለምሳሌ አሁን ብዙ የቤተ ሙከራ ስራ የሚጠብቃቸው በርካታ የከሰል ክምችቶች አሉ። እነዚያ የከሰል ክምችቶቹ የትኛው የእጽዋት ዝርያ እንደሆኑ መለየት ራሱ ከጥቅምት በኋላ ለመስራት ያቀድነው ስራ ነው” ይላሉ ዶ/ር አለምሰገድ። 

ተስፋለም ወልደየስ 

ነጋሽ መሐመድ