1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

«በሺዎች የሚቆጠሩ እህቶቻችን በነፃ ነው እየሰሩ ያሉት»

ዓርብ፣ መስከረም 22 2013

ባንቺ ይመር  የ «እኛለኛ በስደት» ማህበር መስራች እና የሴቶች መብት ተሟጋች ናት። ለጉልበት ስራ ወደ ሊባኖስ የተሰደዱ ወጣት ኢትዮጵያውያት በአሁኑ ወቅት ስለሚገኙበት ሁኔታና ስለ ማህበሯ እንቅስቃሴ አጫውታናለች።

https://p.dw.com/p/3jKJW
Libanon Verein Egna Legna Besidet
ምስል Banchi Yimer

ባንቺ ይመር  የ «እኛለኛ በስደት» ማህበር መስራች

ሊባኖስ ውስጥ የቤይሩት ወደብ ላይ ሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ግዙፍ የኬሚካል ፍንዳታ ከመከሰቱ በፊትም ቢሆን በኮሮና ወረርሽን ስጋት በሃገሪቱ በተጣለው የእንቅስቃሴ ዕገዳ የተነሳ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከስራቸው ተፈናቅለው ጎዳና መውጣታቸው ይታወሳል። በፍንዳታ አደጋ ምን ያህል ኢትዮጵያውያን እንደተጎዱ በውል ባይታወቅም፤ አደጋው የደረሰበት አካባቢ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይኖሩ እንደነበር ተገልጿል። አልፎ አልፎ ሊባኖስ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የኢትዮጵያ ቆንስላው ጄኔራል ጽሕፈት ቤት በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ይፋ ቢያደርግም አሁንም ስፍር ቁጥር የሌላቸው በተለይም በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ፈጣን ርዳታ እንደሚሹ ነው ባንቺ ይመር ለዶይቸ ቬለ (DW) የገለፀችው። «በሺዎች የሚቆጠሩ እህቶቻችን በየአሰሪዎቻቸው ቤት ያለ ደሞዝ በነፃ ነው እየሰሩ ያሉት።» የቤት ሰራተኞቹ ለከፍተኛ የአዕምሮ ህመም ብቻ ሳይሆን የተዳረጉት ባንቺ እንደምትለው « በአሰሪዎቻቸው የቆንስላው በር ላይ የሚጣሉበት ሁኔታ ነው ያለው» ። ሁሉም ወደ ሀገራቸው ነው መመለስ የሚፈልጉት።
ከ300,000 በላይ ኢትዮጵያውን ሊባኖስ ውስጥ ይገኛሉ የምትለው ባንቺ ይመር ሊባዮኖስ ውስጥ ለ7 ዓመታት በቤት ሠራተኝነት በተለያዩ ቤቶች ተቀጥራ ሠርታለች። በነዚህም ዓመታት ውስጥ ብዙ ፈተናዎችን መጋፈጥ ነበረባት። በቂ ምግብና መተኛ ቦታ አለማግኘት እንዲሁም ወሲባዊ ትንኮሳ በምሳሌነት የምትጠቅሳቸው ናቸው። ይህም ይበልጥ ለሴቶች መብት እንድትሟገት እና ድጋፍ ሰጪ ማኅበር እንድትመሰርት ገፋፍቷታል። እጎአ በ 2017 የመሠረተችው የ«እኛለኛ በስደት» ማህበር በአሁኑ ሰዓት ችግር ለገጠማቸው የቤት ሰራተኞች ከፍተኛ ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል። « ከ 6000 በላይ ለሚሆኑ የሰው ቤት ሰራተኞች የምግብ ድጋፍ አድርገናል። ከ 200 በላይ የሚሆኑ እህቶቻችንን ጥቂት የሌላ አገር ዜጎችን ጨምሮ ቲኬት ገዝተን አሳፍረናል። »  ትላለች ባንቺ። 
ሊባኖስ ውስጥ የኮሮና ወረርሽን ስጋት እና ግዙፉ ፍንዳታ ከተከሰተ በኋላ ያለው የኢትዮጵያውያን ይዞታ ይባባስ እንጂ ፤ ከዚያም በፊት ወደ አረብ አገር የሚሄዱ ወጣት ኢትዮጵያውያት ብዙ ችግር ሲገጥማቸው ተስተውሏል። ያም ሆኖ በርካቶች በሕጋዊም ይሁን በሕገ ወጥ መንገድ ከመጓዝ አልተቆጠቡም። ችግሩ ምኑ ጋር ነው ያለው? ከብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን ጋር የተወያየችው ባንቺ እንደምትለው አብዛኞቹ  ወጣቶች «ወይ ችግሩን እያወቁ የተሳካላቸውን ሰዎች ብቻ እያዩ የሚሰደዱ ናቸው ወይም ደግሞ በቤተሰብ ግፊት የሚላኩ እና ያለውን ችግር እንኳን የሚያመዛዝኑበት እድሜ ላይ የማይገኙ ናቸው»። ሌላም ትልቅ ችግር አለ ትላለች ባንቺ። « ትልቁ ችግር ያለው ከኢትዮጵያ መንግሥት ነው። ምክንያቱም የመንግሥት ቅጥረኛ ሆነው የተሰበሰቡት ሰዎች 18 ላልሞላቸው ልጆች ነው የ 26 እና 27 እድሜ ፓስፖርት እየሰጡ ያሉት።» ከዚህም ሌላ ደላሎች ትልቅ ፈተና እንደሆኑ ትናገራለች። ስለሆነም ባንቺ ለወጣቱ ያላት መልዕክት ሀገራቸውን ለቀው እንዳይሰደሱ ነው። «ያልፍልናል ብለን በኋላ አብደን፣ አካላችን ጎድሎ ኢትዮጵያ ከምንገባ፣ ቤተሰብ ያሳልፉልኛል ብለው ልከው አስክሬናቸውን ከሚቀበሉ እዛው ከነድህነታችን ሀገራችሁ ብትኖሩ ነው የሚሻለው» ትላለች የ«እኛለኛ በስደት» ማኅበር መስራች እና ለሴቶች መብት የምትሟገተው ባንቺ ይመር። የ32 ዓመት ወጣቷ በቤት ሠራተኝነት ትሠራ ከነበረችበት ሊባኖስ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ ወደ ካናዳ ሄዳ አዲስ ሕይወት ለመመስረት ችላለች። ቢሆንም ሊባኖስ ውስጥ በመሰረተችው ማኅበር እና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት ወጣት ኢትዮጵያውያን ላይ ስለሚደርሰው በደል በየጊዜው ማሳወቁን አላቋረጠችም። 

Libanon Verein Egna Legna Besidet
«እኛለኛ በስደት» ማህበርን በአሁኑ ሰዓት ሊባኖስ ውስጥ እየመሩ ያሉ አምስት ሴት ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ።ምስል Banchi Yimer
Libanon Verein Egna Legna Besidet
ማህበሩ ለቤት ሰራተኞች ከሚሰጠው ርዳታ አንዱ የምግብ ድጋፍ ነውምስል Banchi Yimer


ልደት አበበ
ማንተጋፍቶት ስለሺ