1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሳዑዲ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን በአፋጣኝ እንዲፈቱ የአውሮፓ ምክር ቤት አሳሰበ

ሐሙስ፣ መስከረም 28 2013

የአውሮፓ ምክር ቤት በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአፋጣኝ እንዲፈቱ አሳሰበ። የምክር ቤቱ አባል "የኢትዮጵያውያኑ አያያዝ ሰብዓዊነት የጎደለውና አሳፋሪ ነው" ብለዋል። ሳዑዲ አረቢያን አጥብቆ የተቸው የአውሮፓ ምክር ቤት ስደተኞች በፈቃደኝነት ክብራቸው ተጠብቆ የሚመለሱበትን መንገድ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያመቻች ጠይቋል

https://p.dw.com/p/3je1r
Coronavirus - Sitzung des EU-Parlaments in Brüssel
ምስል AFP/K. Tribouillard

ሳዑዲ አረቢያን ያወገዘው የአውሮፓ ምክር ቤት ውሳኔ

የአውሮፓ ምክር ቤት በቂ የጤና አገልግሎት እና ምግብ በሌለበት የንጽህና መጠበቂያ እየተቸገሩ በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች የሚገኙ ስደተኞች እና ፈላሲያን አያያዝ እጅግ እንዳሳዘነው ዛሬ አስታወቀ። "በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች የሚገኙ ስደተኞች ሞት እጅግ ያሳዝናል ተቀባይነትም የለውም" ያለው ምክር ቤቱ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ነፃ እና ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንዲመረምሩ ጥሪ አቅርቧል።

ምክር ቤቱ በምርመራ ተጣርቶ ጥፋተኞች ፍትሐዊ ዳኝነት ሊያገኙ ይገባል ያላቸው በድንበር አካባቢ በስደተኞች ላይ ጥይት መተኮስ፣ ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ መግደል፣ ስቅየት መፈጸም፣ ኢ-ሰብዓዊ አያያዝን የመሳሰሉ ጉዳዮች ናቸው።

ምክር ቤቱ ሕፃናት፣ ሴቶች እና በተጋላጭ ኹኔታ ውስጥ የሚገኙትን በማስቀደም የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያዊ ስደተኛ እስረኞችን በአፋጣኝ እንዲፈቱ ጥሪ አስተላልፏል። ይኸን ጥሪ ያቀረበው በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ስደተኞች የተመለከተ እና ሳዑዲ አረቢያን በብርቱ የተቸ ባለ 24 ነጥቦች ውሳኔ ሲያሳልፍ ነው። ውሳኔው በምክር ቤቱ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ጸድቋል።

የውሳኔ ሐሳቡ ለውይይት ሲቀርብ ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ አባል ሳሚራ ራፋኤል "በሳዑዲ አረቢያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያወግዝ ውሳኔ መተላለፉ ጠቃሚ ነው። ይኸ ውሳኔ አብረውን ለሚሰሩት ለኢትዮጵያ እና ለሳዑዲ አረቢያ የዜጎች መብቶች ችላ ማለት እንደማይኖርባቸው ጠቃሚ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው" በማለት ለዶይቼ ቬለ ፋይዳውን አስረድተዋል።

"እኛ የአውሮፓ ምክር ቤት አባላት እዚያ እየሆነ ስላለው ነገር በሰማንው እና በተመለከትንው ምስል እጅግ ደንግጠናል። ሰዎች እና መሰረታዊ መብቶቻቸው እየተጠበቁላቸው አይደለም። ሁሉም ሰው ዕኩል ኤኮኖሚያዊ ዕድል እንደሌለው ልንረዳ ይገባል። ኢትዮጵያውያን ስደተኛ ሰራተኞች ደሕንነቱ የተጠበቀ የሥራ ከባቢ፤ እኩል ክፍያ እና አያያዝ የማግኘት መብት አላቸው። እኛ የአውሮፓ ምክር ቤት አባላት ዓለም አቀፍ ህግ በሳዑዲ አረቢያ እንዲህ እየተጣሰ ከእነዚህ አገሮች ጋር ወዳጅነት ሊኖረን አይችልም ብለን እናምናለን" ሲሉ ጉዳዩ በቸልታ ሊታለፍ እንደማይገባ ተናግረዋል። ኔዘርላንዳዊቷ ሳሚራ ራፋኤል እንዳሉት "የኢትዮጵያውያኑ አያያዝ ሰብዓዊነት የጎደለው እና አሳፋሪ ነው።"

የምክር ቤቱ ጠጠር ያለ ውሳኔ የተደመጠው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች የሚገኙ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ይዞታ አሳሳቢ መሆኑን ካስታወቁ በኋላ ነው።

ባለፈው ሳምንት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ ባደረገው ምርመራ ሶስት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሳዑዲ እስር ቤቶች መሞታቸውን እንዳረጋገጠ አስታውቆ ነበር። ሌሎች 4 ሰዎች ለመሞታቸው በእስር ቤቶች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን መረጃ እንዳገኘ የገለጸው አምነስቲ እንዳለው በእስር ቤቶች ካለው የበሽታ መስፋፋት፣ የምግብ፣ የውኃና የሕክምና እጦት አኳያ የሟቾች ቁጥር ከፍ ሊል ይችላል። ኢትዮጵያውያኑ ከየመን በሒቲዎች ከተባረሩ በኋላ በሳዑዲ አረቢያ የጸጥታ ኃይሎች ተይዘው አል-ዳየር፤ ጂዛን፤ ጂዳ እና መካ በሚገኙ እስር ቤቶች ታስረዋል።

የአውሮፓ ኅብረት "ከየመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚገባ ማንኛውም ሰው ደሕንነቱ ተጠብቆ ምግብ፣ መድሐኒት እና የጤና አገልግሎት፣ የግል ንጽህና መጠበቂያ ወደ ተሟላለት፤ መስኮት ያለው፣ የጸሀይ ብርሀን ወደሚያገኝበት ተገቢ የመቀበያ ማዕከል መዘዋወሩን" የአገሪቱ ባለሥልጣናት ሊያረጋግጡ ይገባል ብሏል።

የኮሮና ወረርሽኝ እና የሳንባ ነቀርሳን የመሳሰሉ በሽታዎች ከአንዳቸው ወደ ሌላቸው እንዳይተላለፉ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ያለው የአውሮፓ ምክር ቤት ሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶችን ለስደተኞች እና ፈላሲያን ማቆያ ከመጠቀም እንድትቆጠብ አሳስቧል።  

Saudi-Arabien Verteidigungsminister von der Leyen & bin Salman al-Saud
የአውሮፓ ምክር ቤት ከኢትዮጵያውያን ሰብዓዊነት የጎደለው አያያዝ በተጨማሪ በከማል ኻሾግጂ ግድያ፣ በየመን ቀውስ እና በሴት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አያያዝ ሳዑዲ አረቢያን ተችቷልምስል picture-alliance/dpa/R. Jensen

የኢትዮጵያ መንግሥት በፈቃደኝነት፣ ደሕንነታቸው እና ክብራቸው ተጠብቆ የታሰሩ ዜጎቹ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን መንገድ እንዲያመቻች ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል። የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹን ለመመለስ ከዓለም አቀፉ የፈላሲያን መርጃ ድርጅት (IOM) ሊተባበር እንደሚችል ጥቆማ የሰጠው የአውሮፓ ምክር ቤት እንዳለው በተለይ ለሕፃናት፣ ሴቶች እና ተጋላጭ ሰዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል።

ኔዘርላንዳዊቷ የምክር ቤቱ አባል ሳሚራ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ኢትዮጵያውያኑ የታሰሩበትን ኹኔታ በፋጣኝ እንዲያሻሽሉ፤ የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የሚመለሱበትን መንገድ እንዲያመቻች አሳስበዋል። ሳሚራ እንደሚሉት የኢትዮጵያ መንግሥት በፈቃዳቸው መመለስ የሚፈልጉ ዜጎች መብታቸው ተከብሮ እና ኹኔታዎች ተመቻችተውላቸው ወደ አገራቸው የሚያቀኑበት መንገድ ሊያመቻች ይገባል። "መመለስ ከፈለጉ ያለ እንቅፋት ሊመለሱ ይገባል" ብለዋል።

ሳሚራ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ይኸው ውሳኔ የአውሮፓ ኅብረት የዲፕሎማሲ ተወካዮች ሳዑዲ አረቢያን በመጎብኘት "በትክክል ምን እየሆነ እንደሆነ እና ስደተኞቹ የትኞቹ መብቶቻቸው እንዳልተከበሩላቸው እንዲያጣሩ" ጠይቋል።

የአውሮፓ ኅብረት እና አባል አገራት የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹን ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት የለይቶ ማቆያ ማዕከላትን አቅም በማሳደግ፣ በምርመራ፣ በመጓጓዣ አቅርቦት እና ስነልቦናዊ ድጋፍ እንዲያግዙ ምክር ቤቱ ጠይቋል።

ውሳኔው ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የሳዑዲ አረቢያው ንጉስ ሰልማን ቢል አብዱል አዚዝ አል-ሳዑድ እና የአውሮፓ ኮሚሽንን ጨምሮ ለሚመለከታቸው እንዲላክ ምክር ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ