1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሳህል አካባቢ አገራት እየጨመረ የሚታየዉ ሁከት

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 2 2014

ከመካከለኛዉ የሳህል ሃገራት የታጠቁ ቡድኖች ጥቃት ለመፈጸም  ለምሳሌ ወደ ቤኒን እያቀኑ ነው። የታጣቂዎቹ ወደ አካባቢዉ መግባት መላውን አካባቢ እንዳያዳክም ያሰጋል። እንደ አለመታደል ሆኖ በየሃገራቱና በየግዛቶቹ ጥቃቱን ለማስቆም ምንም ዓይነት መፍትሄ እስካሁን አልተገኘም።

https://p.dw.com/p/447QV
Benin Symbolbild Sicherheit
ምስል Stefan Heunis/AFP

በናይጀርያ ቤኒን ቡርኪናፋሶ የጽንፈኞች ጥቃት አሳሳቢ ነዉ

በያዝናቸዉ ወራት እና ሳምንታት ቤኒን ለመጎብኘት በጣም ጥሩ አየርና ቦታ መኖሩን የሚያሳዩ ማስታወቅያዎች የማኅበራዊ መገናኛ አዎታሮችን አጨናንቀዋል። የጎርጎረሳዉያኑ ዓመት ማብቅያና የጎርጎረሳዉያኑ አዲስ ዓመት መባቻ በተለይ ቤኒንን መጎብኘት ለሚፈልጉም ሆነ ለአስጎብኝ ድርጅቶች ተፈላጊ የቱሪዝም ወቅት ነዉ። በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ የቤኒን ዜጎችና ትዉልደ ቤኒናዉያን ቤተ-ዘመዶቻቸዉን ሊጠይቁ ወደ ትዉልድ ሃገራቸዉ የሚመለሱበትም ወቅት ነዉ። ከአዉሮጳ ለሚመጡ ጎብኝዎች ደግሞ በሃገራቸዉ ብርዳማ ወቅት ሲገባ ሃገራቸዉን ጥለዉ ወደ ቤኒን መምጣትና ፀሐይን መሞቅ የሚፈልጉበት አመቺ ወቅት ነዉ። ሆኖም ግን የአካባቢዉ የፀጥታ ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ ይመጣ ይመስላል። በቤኒን በሰሜን ናቲቲንጉ ከተማ የሚገን የአንድ ሆቴል ባለቤት ሳንኒ ቃሲም ያሳሰባቸዉ ነገር አለ። የሆቴል ክፍል ለመከራየት የተመዘገቡ 27 ሰዎች ኦሚክሮን በተባለዉ ልዉጥ የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ክፍል የያዙ ሰዎች ወደ ሆቴሉ እንደማይመጡ ተናግረዋል ይላሉ። ሆቴሉን ለመያዝ ፈልገዉ የነበሩት ሃገር ጎብኝዎች  ሆቴሉ ምን ያህል ደህንነቱ የተጠበቀ ነዉ የሚልም ጥያቄዎችም  በተደጋጋሚ አቅርበዉላቸዋል። በሰሜናዊ ቤኒን ኅዳር መጨረሻ እና ታህሳስ መጀመሪያ ላይ ሁለት ጥቃቶች ተፈፅመዋል።ይህ ዓይነት ጥቃት በሀገሪቱ ሲፈፀም ለመጀመሪያው ጊዜ ነው። በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ቦታዎች ፖርጋ እና ባኒኮራ በተባለ ቡርኪና ፋሶ ድንበር ላይ የሚገኝ በቤኒን ታዋቂ ፓርክ አጠገብ ላይ የሚገኝ ቦታ ነዉ። ቦታዉ የቤኒን እና መላው ምዕራብ አፍሪቃን የሚያገናኝ ማዕከላዊ ቦታም እንደሆን ይነገርለታል።  ጥቃቱን የፈፀሙት አካባቢዉ ላይ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ጽንፈኞች ናቸዉ ተብሎአል።  

Benin | Pendjari Nationalpark
ምስል Katrin Gänsler/DW

«እርግጥ ነዉ ከተለያየ አቅጣጫ ወሪ ይሰማል። ነገሩ በምስራቅ እና በምዕራብ ቤኒን ከጎርጎረሳዉያኑ ኅዳር 29 እና ​​ታህሳስ 1 መካከል ስለተከሰቱት ሁለት ጥቃቶች ነዉ።  በአሁኑ ጊዜ በሬዲዮና በቴሌቭዥን የሚሰራጭ መረጃ ብቻ መኖሩን ነዉ የምናዉቀዉ።»

የናቲቲንጉ ከተማ ነዋሪዎች የሚተዳደሩት በአብዛኛዉ ከተማዋ ከምታገኘዉ የቱሪዝም የገቢ ነዉ። የቱሪዝም ተጠቃሚዎቹ የጉዞ አስጎብኝዎች ብቻ ሳይሆኑ በቡድን የሚመጡ ጎብኝዎች የሚቀመጡበት ሆቴሎች፣ የምግብ ሸቀጣሸቀጥ መደብሮች ጭምር ሁሉ ናቸው። በአፍሪቃ ፓርኮች ድርጅት የሚተዳደረውን የፔንድጃሪ ፓርክን ደህንነት ለመጠበቅ  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙ ተሠርቷል።

የደከመዉ ቱሪዝም

Benin | Sanny Kassim
ምስል Katrin Gänsler/DW

ይሁና በጎርጎረሳዉያኑ ግንቦት 1፣ 2019 ዓም ምሽት፣ አንድ ቤኒናዊ አስጎብኚ በታጣቂዎች ተገድሎአል። ሁለት የፈረንሳይ ዜጎች ታግተዋል።  በአሁኑ ጊዜ የሽፍቶች ታጣቂዎች እና የአሸባሪዎችን  ትኩረት ስቦ የሚገኘዉ በምዕራብ አፍሪቃ የቤኒን ሰሜናዊ ክፍል ብቻ አይደለም። ከጎርጎረሳዉያኑ 2016 ዓመት ጀምሮ በሰሜናዊ ክፍል ከባድ ጥቃቶች በተፈፀሙባት በቡርኪናፋሶም የጽንፈኞች ጥቃት እና ብጥብጥ እየተስፋፋ መጥቶአል።  

«ሁኔታዉ እየተባባሰ ነዉ የመጣዉ። የሳህል አካባቢ ላለፉት ለአስር ዓመታት ገደማ በተለያዩ አማጽያን ቡድኖች ግፊት ዉስጥ ነዉ ያለዉ። እነዚህ አማፅያን እንደ አይቮሪ ኮስት፣ ቤኒን እና ቶጎ ባሉ ጎረቤት ሀገራት ዉስጥ ዘልቆ የመግባት አዝማሚያም አላቸው።»

ከመንደር እስከ ከተማ

በቡርኪናፋሶ ውስጥ እስከዛሬ ታዋቂው የሽርሽር መዳረሻ በባንፎራ ክልል የሚገኘዉ ፏፏቴ እና ደን እንዲሁም  በደቡብ ምዕራብ የቦቦ-ዲዮውላሶ ከተማ ነበር። አሁን ግን አካባቢዉ በታጣቂዎች በመያዙ አስጊ ስፍራ በሆኑን በዝያዉ አካባቢ ላይ በሚገኘዉ ትምህርት ቤት ዉስጥ የሚሰሩት መምህር ሲድ-ላሚን ሰሎካ ይናገራሉ። እንደመምህሩ በከተማ ዉስጥ ብዙም አስፈሪ ሁኔታ አይታይም።  በገጠር እና በትናንሽ መንደር ዉስጥ ግን ሁኔታዉ ሌላ ነዉ።

«ከተማ ውስጥ ሲሆን ፣ ይህ የስጋት ጫና በፍፁም አይታሰብም። በገጠሩ እና በትናንሽ መንደሮች ዉስጥ ግን ህዝቡ በጣም ስጋት ዉስጥ ነዉ። አንዳንዴም ጽንፈኛ ታጣቂዎቺ ቦታዉ ላይ ይመጣሉ። ጥቃት ባይፈፅሙ እንኳ ከባድ ጫና ይፈጥራሉ። ሰዎች እንደነሱ ፅንፈኛ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ።» 

ቦቦ-ዲዮላ ከተባለዉ ከቦርኪናፋሶ ከተማ ወደ 200 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የደቡባዊ ማሊ የንግድ ማዕከል ሲካሶ ይገኛል። በዚህ ክልል ጥቅምት ወር ላይ አምስት ሰዎች ታፍነዉ ተወስደዋል። ከሳህል ሃገራት መካከል ነፃ እና እድገት አላት በምትባለዉ በናይጀርያ የጽንፈኛ ታጣቂዎች ጉዳይ አሳሳቢና መወያያ ርዕስ ነዉ።  እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር 2001 በናይጀርያ የተመሰረተዉ ታጣቂ ቡድን ቦኮሃራም በጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር 2010 ዓመት ከአስር ዓመት በኋላ አክራሪ ፅንፈኛ ታጣቂ ቡድን ሆኖ ተጠናከሮ ወጥቶአል። ቡድኑ ከናይጀርያ አልፎ በሰሜናዊ ካሜሩን እና በኒጄር ጥቃቶችን ቢያደርስም ጥቃቱ እየተወሰደ ያለዉ  እንደ  አካባቢያዊ ክስተት ሆንዋል ሲሉ በምዕራብ አፍሪቃ የዓለም አቀፍ የውዝግቦች አጥኚና ተንታኝ ድርጅት የፕሮጀክት ኃላፊ ራይንሆልድ ዳፓኔ ይናገራሉ።  

Karte - Westafrika - EN

 «የታጠቁ ሽፍቶች ብቻ አይደሉም። ኢስዋፕ እና አንሳር የተሰኙት በናይጀርያ የሚንቀሳቀሱት የጽንፈኛ ቡድኖች ይመስሉናል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ጥቃቶቹ እንዴት እንደሚፈፀሙ ምን ዓይነት መሳርያዎች ጥቅም ላይ እንደሚዉሉ ማስረጃ ነዉ። አንዳንዶቹ  ጥቃቶች በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ ከተፈጸሙት ጋር ተመሳሳይ ናቸው።»

ከመካከለኛዉ የሳህል ሃገራት የታጠቁ ቡድኖች ጥቃት ለመፈጸም ለምሳሌ ወደ ቤኒን እያቀኑ ነው። የታጣቂዎቹ ወደ አካባቢዉ መግባባት መላውን አካባቢ እንዳያዳክም ያሰጋል። በምዕራብ አፍሪቃ የዓለም አቀፍ የውዝግቦች አጥኚና ተንታኝ ድርጅት የፕሮጀክት ኃላፊ ራይንሆልድ ዳፓኔ እንደሚሉት በምዕራብ አፍሪቃ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ያሉ ግዛቶች አሉ።

«በአሁኑ ወቅት በምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ በታጣቂ ቡድኖች ጥቃት የሚፈጸምባቸው በርካታ አገሮች አሉ። እንደ አለመታደል ሆኖ በየሃገራቱና በየግዛቶቹ ይህን ለማስቆም ምንም ዓይነት መፍትሄ እስካሁን አልተገኘም። አሁንም በመንግስት ቁጥጥር ስር ሳይሆን  በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ያሉ ሙሉ ግዛትና ክልሎች አሉ።»

አዜብ ታደሰ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ