1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሱዳን የቀጠለው ተቃውሞ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 11 2014

ሱዳናውያን በተቃውሞ ጎዳናዎችን ማጥለቅለቃቸውን ቀጥለዋል። ትናንት በመላዋ ሱዳን በርካታ ከተሞች በሺህዎች የተገመቱ ዜጎች የተሳተፉባቸው የተቃውሞ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል ርምጃ እስካሁን የአንድ ሰው ሕይወት መጥፋቱ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/44aof
Sudan, Khartoum | Proteste gegen den Militärputsch
ምስል AFP/Getty Images

«የጦር ኃይሉ ከመንግሥት አስተዳደር እንዲወጣ ሕዝቡ እየጠየቀ ነው»

በበርካታ ሺህዎች የተገመቱ ሱዳናውያን በዋና ከተማ ኻርቱም እና በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ታላቅ የተቃውሞ ሰልፎችን ትናንት አካሂደዋል። ሰልፉ በጎርጎሪዮሳዊው 2019 ዓ,ም ሚያዝያ ወር ላይ ከሥልጣናቸው በሕዝባዊ አመጽ የተወገዱትን የቀድሞውን ፕሬዝደንት ኦማር አልበሽርን በመቃወም የሱዳን ሕዝብ የአደባባይ ሰልፍ ማካሄድ የጀመረበትን ሦስተኛ ዓመት ታሳቢ ያደረገ ነው። በአብዛኛው የሀገሪቱ ከተሞች ትናንት የተካሄደው እና ብዙዎች የተሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፍ አልበሽርን ከሥልጣን ካስወገደው ታሪካዊ ሕዝባዊ ትዕይንት ወዲህ በሱዳን ከተደረጉት ታላላቅ ሰልፎች አንዱ መሆኑም ነው የተነገረው። ከ30 ዓመታት በላይ ሥልጣን ላይ የቆዩት አልበሽር ከተሰናበቱ በኋላ ያለፉት ዓመታት ሱዳን አስቸጋሪ የሽግግር ሂደት ያሰተናገደችባቸው ጊዜያት ነበሩ። በሱዳን ወታደራዊ እና ሲቪል የፖለቲካ ኃይሉ የተጣመረበት አስተዳደር በብዙ ውጣ ውረድ ቢመሠረትም ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ የጦር ኃይሉ ያካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ሀገሪቱን ወደሌላ የፖለቲካ አዙሪት እና ውጥረት ውስጥ እንደከተታት ይታያል። የጦር ኃይሉን በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ መግባት አበክረው የሚያወግዙ የሱዳናውያን ቁጣም ከጥቅምቱ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ወዲህ ተባብሶ ቀጥሏል። ዘገባዎች እንደሚያሳዩትም ከጥቅምቱ መፈንቅለ መንግሥት ወዲህ ዘጠነኛው እና ታላቁ ሰላማዊ ሰልፍ ነው ትናንት በመላው የሱዳን ከተሞች የተካሄደው።

Sudan, Khartoum | Proteste gegen den Militärputsch
ምስል Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance

የወታደራዊው መፈንቅለ መንግሥት መሪ ጀነራል አብደል ፈታል አልቡርሃን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክን ወደ መንበራቸው ቢመልሱም የጦር ኃይሉን ከመንግሥት የአስተዳደር ሚና መውጣት አጥብቀው የሚጠይቁት የሱዳናውያን ተቃውሞ ግን አልበረደም። በትናንትው ዕለትም ዋና ከተማ ኻርቱምን ከኦንዱርማን ከተማ በሚያገናኘው አባይ ወንዝ ላይ የተገነባውን ድልድይ የጸጥታ ኃይሎች ለመዝጋት ቢሞክሩም የተቃውሞ ሰልፈኞቹ እገዳውን አልፈው ወደ ኻርቱም ሲገቡ አስለቃሽ ጋዝ እንደተቀበላቸው ዘገባዎች ጠቅሰዋል። የሱዳን ጦር ኃይል፣ እንዲሁም ፈጣን ድጋፍ ሰጪ የሚባለው ኃይል ወደ አውሮፕላን ማረፊያ እና ወደ የጦር ኃይሉ ዋና ጽሕፈት ቤት የሚወስዱ ዋና ዋና መንገዶችን ለመዝጋት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጸጥታ ኃይል ተሰማርቶ እንደነበርም ተገልጿል። በተቃራኒ ወገንም እንዲሁ የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ወደተሰለፉባቸው አደባባዮች የሚወስዱ መንገዶችን ሲዘጉም ታይተዋል። በተቃውሞ ሰልፍ ላይ ሱዳናውያን የሀገራቸውን ሰንደቅ አላማ እንዲሁም ከዚህ ቀደም በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የተገደሉ ዜጎችን ፎቶዎች ይዘው ወጥተዋል። በዋና ከተማ ኻርቱም አደባባይ ከወጡ የተቃውሞ ሰልፈኞች ጥቂቱ ወደ ቤተመንግሥቱ በሮች በመቅረብ ምሽቱን በደጁ ተቀምጠው ለማሳለፍ ሲሞክሩም የጸጥታ ኃይሎ በሰነዘረው የእንባ አስመጪ ጋዝ ጥቃት ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

Sudan, Khartoum | Proteste gegen den Militärputsch
ምስል Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance

ከአልበሽር አገዛዝ በተላቀቀችው ሱዳን ውስጥ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሥልጣኑን የተቆናጠጠው ወታደራዊ ኃይል አሁንም በአንድም ሆነ በሌላው መንገድ ከስፍራው ለመልቀቅ የተዘጋጀ አይመስልም።  ከወራት በፊት ከጥምሩ የሀገሪቱ የሽግግር መንግሥት ኃላፊነት በኃይል ያነሳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክን ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በበዛበት ጫና ወደ ቦታቸው ቢመልስም ከአስተዳደር እጁን እንዲያወጣ የሚጣራውን የሱዳን ሕዝብን ቁጣ ማለዘብ አልቻለም። ከተቃውሞ ሰልፈኞቹ አንዱ መሐመድ አል ፈታህ የሕዝቡን ፍላጎት እንዲህ ይገልጸዋል።

«አብዮቱ የሚንቀሳቀሰው በሱዳን ሕዝብ ነው፤ ሕዝብ ያሸንፋል ሥልጣኑንም ያገኛል። ጦር ኃይሉ ሊመራ አይገባም፣ ከእነሱ ጋር የተካሄደው ድርድርም የተሳሳተ ነው። በዚህ መዘዝም አሁን እየተሰቃየን ነው።»

Proteste gegen die Übergangsregierung im Sudan
ምስል El Tayeb Siddig/REUTERS

ሌላኛው ተቃዋሚ ሰልፈኛ ሀማዝ መሀመድ በበኩሉ ከመፈንቅለ መንግሥቱ መሪዎች ጋር ተደራድረው ዳግም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተመለሱት አብደላ ሀምዶክ ተገድደው ወደ ድርድሩ እንደመጡ ይገምታል። ምንም እንኳን ሀምዶክ ይኽን የተቀበሉ ቢመስልም የሕዝብ ድጋፍ እስካልተገኘ ድረስ ፖለቲካዊ ግብ አይኖረውም ባይ ነው። ዛሬ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የትናንቱን የተቃውሞ ሰልፍ ለመበተን የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት ርምጃ አንድ ሰው ሲገደል 125 ሰዎች መጎዳታቸውን የሱዳን ጤና ሚኒስቴር ገልጿል። አሁንም ግን የሕዝቡ ተቃውሞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የነጻነት እና የለውጥ ኃይሎች የተሰኘው የተቃዋሚዎች ስብስብ ጥሪውን አስተላልፏል። በቀጣይም የፊታችን ቅዳሜ እና በመጪው ሳምንት ሐሙስ የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄዳቸውን እንዲቀጥሉበት ሕዝቡን ተማጽኗል።

 ሸዋዬ ለገሠ 

ኂሩት መለሰ