1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሰው የሚያርሱ ገበሬዎቸ እና በጎንደር የተገደሉ ሙስሊሞች

ዓርብ፣ ሚያዝያ 21 2014

«ይህ ህመም የሙስሊሙ ብቻ አይደለም።ይህ ህመም የክርስቲያኑ ብቻም አይደለም።ይህ ህመም ለሰው ልጆች ክብር የሚጨነቁ የሚያስቡ ሁሉ ህመም ነው።»የሚል አስተያየት ስጥተዋል።

https://p.dw.com/p/4AbHK
Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Jakub Porzycki/NurPhoto/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

 በዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅት  በድርቅ ሳቢያ የእርሻ በሬዎቻቸውን ያጡ አርሶ አደሮች በሰው ሲያርሱ በሚያሳየው ፍቶ፣በጠቅላይ ሚንስትሩ የጓሮ ግብርና ጉብኝት እንዲሁም በጎንደር ከተማ በተፈጠረው ችግር በተገደሉ ሙስሊሞች  ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ዘንድ የተሰጡ አስተያየቶችን  አሰባስበናል። 
በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን የሚገኙ  አርሶ አደሮች  በድርቅ ሳቢያ ለእርሻ ስራ የሚገለገሉባቸው ከብቶች በማለቃቸው፤  ሰዎች በሬዎቹን ተክተው ሲያርሱ የሚያሳየው እና በማኋበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰራጨው  ፎቶ፤  በዚህ ሳምንት በርካታ አስተያየት የተሰጠበት እና ብዙ ያነጋገረ ጉዳይ ነበር።
ሂዌ ነኘ በሚል የፌስ ቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት «ችግራችን ሄዶ ሄዶ እዚህ ደርሷል»ይላል።አቢኮ ዳዊት በበኩላቸው «አሁን ለእነዚህ ሰዎች የሚሆን ገንዘብ ጠፍቶ ነው? ምን አለበት ብንተባበር።»ሲሉ፤ሄለን ዓለሙ  ደግሞ«ዓለም በቴክኖሎጅ የት ላይ ደርሳለች እኛ ወደ ኋላ ተጉዘን በበሬ ከማረስ ወደ ሰው ተሸጋገርን።ወደ ጥንታዊ ዘመን ያሳዝናል።» መክብብ አረጋ ደግሞ «በጣም የሚያሳዝንና ልብ የሚነካ ችግር ነው ፈጣሪ በቃ ይበለን።»ብለዋል።ዳዊት በፀጋ በበኩላቸው «የስቃያችን ብዛቱ! ድርቁ፣ ሌብነቱ፣ ማፈናቀሉ፣ ጦርነቱ፣ ግድያው፣ ረሃቡ፣ የሃይማኖት እና የብሔር ግጭቱ፣ ስደቱ፣ የኑሮ ውድነቱ  በምድር ላይ ያሉ መከራዎች ሁሉ ተጠራርተው በአንድ ላይ የሰፈሩብን ኢትዮጵያውያን ግን ምን ነክቶን ነው?  ኢትዮጵያውያን ግን ምን ሆነን ነው?»በማለት ጠይቀዋል።አብዱ ከማል ደግሞ «እባካችሁ በፌስቡክ ፎቶ ከመለጠፍ ወጥተን መረዳዳት እንጀምር።»ብለዋል። «ዘንድሮ በችግር እየቀለድን እንለፈው እንጅ  ገና የማናየው እና የማንሰማው ችግር የለም,።»ያሉት ደግሞ መሰረት ፈቀደ ናቸው።
በሳምንቱ መጀመሪያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ  ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክር ቤት ጋር ውይይት ካካሄዱ በኋላ የከተማ ግብርና  እንቅስቃሴ አንድ አካል ነው የተባለውን  እና በጽሕፈት ቤቱ ቅጥር ግቢ የሚከናወነውን የጓሮ ግብርና ለስብሰባው ተሳታፊዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያስጎበኙ መታየታቸው በማኋበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካቶችን አነጋግሯል። 
ይህ ይግብርና ዘዴ የውሃ ብክነትን፣ ቁሳቁሶችን እንደገና መጠቀምን እና የቦታ እጥረትን ባማከለ መልኩ የሚካሄድ መሆኑን በመግለፅ የከተማ ነዋሪዎች የከተማ ግብርናን እንዲተገብሩ የሚያበረታታ መሆኑንም ጠቅላይ ሚንስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ጭምር አስፍረዋል።  እሳቸው ይህን ይበሉ እንጅ ወቅቱን ያልዋጄ ነው በሚል ጉዳዩ በርካታ ትችት አስተናግዷል።
ጋሻው ድንቄ  «የጓሮ ግብርና ከሚገመግሙ የሃገሪቱን ሰላምና ደህንነት የዜጎች ሞት እና ስደት ቢገመግሙ ይሻል ነበር። የሰው ደም እየፈሰሰ ስለ ጓሮ አትክልት  እረ ይታሰብበት!» ሲሉ፤ ሽመልስ ገበየሁ «ኧረ እባካችሁ ሀገራችን የገባችበትን ችግር የሚመጥን ስራ ስሩ!!!»ብለዋል። 
ዘሚካኤል ግርማይ በበኩላቸው «በአንድ የሚንስቴር መስራያ ቤት በአንድ ቅርንጫፍ ሊሰራ የሚችልን ነገር  የመንግስት ይልቁንም የሚንስቴሮች ሁሉ ጠቅላይ ስራ ሆኖ ይረፍ።ይህንን እኮ ያለ በጀት ያን ሁሉ ስራ የሰራው  ጋሽ አበራ ሞላ ቢሊዮን ብር ቢመደብለት የበለጠ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው።እየዞሩ ምግብ ማደልም ቢሆን እነ ቻቺ ታደሰ ከልብ ይሰሩት ነበር::»ሲሉ ተችተዋል።ጌታቸው መኮንን  «ክቡር ጠቅላይ ሚንስቴሩ እርሰዎ በችግኝ እና በፓርክ «ቢዚ» ሆነዋል ዜጎች ደግሞ የእሳት እራት እየሆኑ ነው፡፡» የሚል አስተያየት አስፍረዋል። አሌክስ ዘፅዓት «ብልጽግናዎች ሆይ;ሕዝብ በረሃ፣: በግጭትና ጦርነት አልቆ ዛፍና አትክልት ላይ ልትነግሱ ነው እንዴ!?»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። ታዴ ጋቢይት የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ «ህዝብ እየተነቀለ ችግኝ የሚንከባከብ መሪ! » ብለዋል። ፈይሰል ሬድዋን በበኩላቸው  «ሰው እየተጨፈጨፈ ግብርና ላይ?» ብለዋል። እንድርያስ አምሳለ «ለምን የግብርና ሚንስትር አይሆኑም?» ሲሉ፤«ጠቅላይ ሚንስትሩ ሀሳበዎ አይከፋም። ግን አብዛኛው ከተሜ እንኳን አትክልት የሚያለማበት ለጎኑ ማረፊያ ቤት የሌለው መሆኑን አጥተውት ነው? »የሚል ትችት ያሰፈሩት ጆኒ በላይ ናቸው። 
ከቀናት በፊት በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ  ሼህ ከማል ለጋስ በተባሉ የሀይማኖት አባት ስርዓተ ቀብር ላይ በተከሰተ ችግር  የተገደሉ ሙስሊሞች ጉዳይ በዚህ ሳምንት ብዙዎችን ያሳዘነ እና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም ብዙ ያነጋገረ ጉዳይ ነው። ግድያውን የክልሉ መንግስት ፣ የተለያዩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ፣  የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና ሌሎች  በርካታ ግለሰቦችና ተቋማት አውግዘውታል። በዚህ እኩይ ተግባር የተሳተፉ  አጥፊዎችን መንግሥት ለሕግ እንዲያቀርባቸውም ተጠይቋል።
ይህንን ተከትሎ አህመድ ሁሴን የተባሉ አስተያየት ሰጪ «በጣም የሚያሳዝን ነው።በጾም ወቅት ምስኪን ሙስሊሞችን የገደላችሁ ወንጀለኞች በህግም በፈጣሪም ፊት ተጠያቂ ናችሁ።መንግስትም ወንጀለኞችን አጣርቶ ለፍርድ ያቅርብ ። ህዝቡም ወንጀለኞችን ያጋልጥ »ብለዋል። 
ሀዋ ቃሲም በበኩላቸው «በጎንደር የተከሰተው ችግር አሳፋሪ ነው።በተለይ የተነሳበትና የተዛመተበት መንገድ ። የወገኖቻችን በዚህ መልኩ መሞታቸው እጅግ የሚያሳዝን ነው። የወገኖቻችንን ነብስ ፣ፈጣሪ በጀነት ያኑርልን።»ሲሉ፤  ሶሎሞን ይዲዲያህ በበኩላቸው «የጎንደር ሙስሊሞች መሞታቸው ያሳዝናል። አሁንም በዚህ መንገድ እየተናቆርን መቀጠላችን ለመለወጥ ያለንን ዘገምተኝነት ያሳያል::» ብለዋል።
ጋዜጠኛ ኤልያስ አማን «በጎንደር የተፈጠረውና ኃይማኖትን መሰረት ያደረገው ጥቃት ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም! በጥቂት ጸብ አጫሪዎች በሰላም አብሮ የኖረው ህዝብ ሰላሙ ሊደፈረስ፣ የሰው ህይወት ሊጠፋ አይገባም!»በማለት ፅፏል።
አርሴዶ አርሴዶ በሚል የፌስ ቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ «ይህ ህመም የሙስሊሙ ብቻ አይደለም።ይህ ህመም የክርስቲያኑ ብቻም አይደለም።ይህ ህመም ለሰው ልጆች ክብር  የሚጨነቁ የሚያስቡ ሁሉ ህመም ነው።»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
 አጎ ያኮቦ በበኩላችው «እትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት አባቶች ሰላምና ፍቅርን መሰበክ ስገባቸው  የአንዱን ሃይማኖት መጥፎነት ለተከታዮች ይሰብካሉ፣የብሔር መሪዎች የአንድን ብሄረሰብ መጥፎነት ያወራሉ፣ የፖሊቲካ ፓርቲዎችና መሪዎች የአንድን ፖሊቲካ ፓርቲ መጥፎነት ይሰብካል። እሺ እቺን ሀገር ማን ከጥፋት ይታደጋት ?  ቆም ብለን እናስብ ፈጣሪስ ምን  ይለናል?»ብለዋል።
ባሴ እሸቱ ደግሞ«ክልሉ መግለጫ ከመስጠት የዘለለ እርምጃ ወስዶ ህዝቡን ማረጋጋት አለበት። እርምጃ መወሰድ ከቻላችሁ ህዝብን ትታደጋላችሁ። ከመግለጫ ወደ ተግባር ግቡ። »ሲሉ፤ አቤል ጌታው ደግሞ «ችግሩን የሰው ህይወት ሳይጠፋ ለምን ቶሎ ማስቆም አልተቻለም።እንዴት ከፀጥታ ሀይሉ በላይ ሆነ?»የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
በሌላ በኩል «ከኢትዮጵያ ሰላም እንጂ  ከኢትዮጵያ ሑከት ማናችንም አናተርፍም!»በሚል ጠቅላይ ሚንስትሩ ያወጡትን መግለጫ ተከትሎ ፤ ፀጋ ቢተው«እኔም እንደእርሰዎ እላለሁ እርሰዎም የሀገሪቱን የስልጣን ቁንጮ ይዘው እንደኔ ይላሉ።ጉድ እኮ ነዉ የገጠመን ጎበዝ»ሲሉ። ሰናይት በቀለ  በበኩላቸው«ህዝቡም ጠቅላይ ሚንስትሩም እኩል የሚያማርሩባት ሀገር።መፍትሄ ስንጠብቅ እንደታዛቢ ሆነው።ምክር ይሰጡናል።ወቾ ጉድ።»ብለዋል። ሰኢድ ሽኩር «በሰላም ዙሪያ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት  አጥፊን በደንብ መቅጣት ያስፈልጋል ።»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ዮሐንስ መኮንን «እሳት በእሳት አይጠፋም !በሚል በፌስ ቡክ በፃፉት ደግሞ «የሃይማኖት ተቋማት ዋነኛ ተልዕኳቸው ተከታዮቻቸውን በሥነምግባር በማነጽ ለሀገር እና ለወገን የሚጠቅሙ ዜጎች ማድረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው ተከታዮቻቸውን የሰማዩን መንግሥት እንዲወርሱ ማስቻል ነው።በሀገራችን በተግባር የምንታዘበው ምንድነው? የሃይማኖት ተቋማት ለተከታዮቻቸው እንኳንስ የነፍስ እረፍት የሥጋ ሰላም ማሰጠት እንዴት ተሳናቸው? »ሲሉ ጠይቀዋል።
ሰኚ ቦ ሸፈር «ጎንደር ላይ ለተገደሉት ሙስሊም ወንድሞቻችን እናዝናለን፣ ድርጊቱንም እናወግዛለን። ነገር ግን ጎንደር ላይ ለተገደሉት ሙስሊሞች አዝነናል ማለታችን ጎንደር ላይ በተገደሉት ክርስቲያኖች ተደስተናል ማለታችን አይደለም። በአንጻሩ የመስጊድ መቃጠልን እናወግዛለን ስንል ደግሞ  የቤተክርስቲያንን መቃጠል ለበጎ ነው እያልን እንደግፋለን ማለታችን አይደለም።እንደ ዜጋ ሁላችንም በሀገራችን ላይ እኩል የመኖር መብት አለን።»ካሉ በኃላ «በሁሉም ወገን የሞተው ሰው  ነው። ሙስሊሙም፣ክርስቲያኑም፣መገደልየለባቸውም።መስጊዱም፣ቤተክርስቲያኑም፣መውደም የለባቸውም።የአንዱን በኡኡታ የሌላውን በዝምታ፣ማስተናገድ ይቅር።ገዳይም፣አቃጣይም፣አደብ የሚገዛው፣መልካም የሠራን የሚሸልም፣ጥፋተኛውንና ወንጀለኛውን፣ደግሞ ለህግ አቅርቦ የሚቀጣ፣ፍትህ ሲሰፍን በመሆኑ የህግም የበላይነትም ይረጋገጥ።»በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል።

Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Ozan Kose/AFP/Getty Images
Äthiopien | Gondar
ምስል Alemnew Mekonnen/DW
Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Nicolas Economou/NurPhoto/picture alliance

ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ