1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሰኔ 15ቱ የአማራ ክልል ግጭት ባለቤቶቻቸውን ያጡ ሴቶች ሮሮ

ሐሙስ፣ መስከረም 22 2012

በሰኔ 15ቱ የአማራ ክልል ግጭት ባለቤቶቻቸውን በሞት ያጡ ሴቶች መንግሥት በዘላቂነት እንዲያቋቁማቸው ጠየቁ። ኑሮን ከቤተሰባቸው ጋር ለመደጎም እንደተቸገሩ የገለጡት ሴቶች የቤት እጦትም ፈተና እንደኾነባቸው ተናግረዋል።  

https://p.dw.com/p/3Qh7P
Amhara Polizeikommissar  Zelalem Lijalem und Polizeistation
ምስል DW/A. Mekonnen

ኑሮን መግፋት ተቸግረናል ብለዋል

ፍሬሕይወት ጠና ባለቤቷን በሞት ያጣችው ሰኔ 15/2011 ዓ ም ባሕር ዳር ላይ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ነው፡፡ ፍሬህይወት በወቅቱ የ7 ወር ነፍሰ ጡር ነበረች፡፡ ከወራት በፊት ደግሞ ነብዩ ዮናስን በሰላም ተገላግላለች፡፡ ነብዩ ዛሬ 40ኛ የልደት ቀኑን እያከበረ ነው፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃ ሥራ በመፈለግ ላይ ያለችው ፍሬህይወት ጠና በፖሊስ መመሪያ መሰረት የ6 ወራት የባለቤቷን ደመወዝ ለመውሰድ በሂደት ላይ መሆኗን ለዶቼ ቬለ ተናግራለች፡፡ ሆኖም መንግሥት በዘላቂነት ሊያቋቁመን ይገባል ብላለች፡፡

የመኖሪያ ቤት ችግር ፈተና እንደሆነባት፣ ከዩኒቨርሲቲ ብትመረቅም ሥራ እንደሌላት፣ እንዲሁም ኑሮ እንደከበዳት የምትናገረው ፍሬህይወት ጠና አሁን ተከራይታ ከምትኖርበት ባሕር ዳር ለቅቃ ወደ እናቷ ቤት ነፋስ መውጫ መሄዷን አመልክታለች አጠቃላይ ያለባትን ችግርም እንደዚህ ታብራራለች፡፡ ሌላዋ ባለቤቷን በእለቱ ግጭት ያጣቸው ፍሬህይወት ተወልደ በቂ ባይሆንም የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት አንደሰጣት ተናግራለች፡፡ የባለቤቷን የ6 ወራት ደመወዝ ቀደም ሲል መቀበሏን ያመለከተችው ፍሬህየወት ተወልደ 3 ልጆቿን ለማስተማር ግን የወር ገቢዋ አነስተኛ በመሆኑ መንግሥትና ግብረሰናይ ድርጅቶች እገዛ እንዲደርጉላት ጠይቃለች፡፡

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነትና የሚዲያ አስተባባሪ ምክትል ኮማንደር መሰረት ላቀ እንዳሉት የክልሉ ፖሊስ አባላት ከደመወዛቸው በመቀነስና በግጭቱ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ወገኖችን ለማገዝ 4 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ምክትል ኮማንደር መሰረት አንዳሉት እስካሁንም ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን አስረድተዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ