1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሰበብ አስባቡ የሚዘጋው የኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት

ዓርብ፣ ሰኔ 21 2011

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደርም በግጭት፣ በፖለቲካ ቀዉስ፤ በብሔራዊ ፈተናዎች እየተሳበበ በተለይ የኢንተርኔት አገልግሎትን ማቋረጡ እንደቀጠለ ነዉ። ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በባህር ዳር ከተማ "የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ" ተካሄደ ከተባለ ጊዜ አንስቶም ኢትዮጵያ ውስጥ ለአንድ ሳምንት ያሕል የኢንተርኔት አገልግሎት አልነበረም።

https://p.dw.com/p/3LAC1
Symbolbild Deutschland Internetausbau
ምስል picture-alliance/dpa/F. Gabbert

በሰበብ አስባቡ የሚዘጋው የኢንተርኔት አገልግሎት

ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንተርኔት አልፎ አልፎም የስልክ አገልግሎት ሲቋረጥ አዲስ ነገር አይደለም። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደርም በግጭት፣ በፖለቲካ ቀዉስ፤ በብሔራዊ ፈተናዎች እየተሳበበ በተለይ የኢንተርኔት አገልግሎትን ማቋረጡ እንደቀጠለ ነዉ። ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በባህር ዳር ከተማ "የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ" ተካሄደ ከተባለ ጊዜ አንስቶም ኢትዮጵያ ውስጥ ለአንድ ሳምንት ያሕል የኢንተርኔት አገልግሎት አልነበረም። ባለፉት ሶስት ሳምንታት ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ጊዜ የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል። ይህም የብሔራዊ ፈተና በተሰጠበት ወቅት እና ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በባህር ዳር ከተማ "የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ" ተካሄደ ከተባለ ጊዜ አንስቶ ነው። የኢንተርኔት መቋረጡ ምን አይነት ተፅዕኖ ፈጠረ? አግባብስ ነው ወይ?
በብሔራዊ ፈተናዎች ሲሰጡም ይሁን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተከተገደሉ በኋላ ኢንተርኔት ለተቋረጠበት ምክንያት መንግሥትም ይሁን ኢትዮ ቴሌኮም በይፋ የሰጡት መግለጫ የለም።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ግን በአንድ ወቅት የኢንተርኔት አገልግሎትን መዝጋት አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ገልጸው ነበር። «ቴክኖሎጂን በመገደብ፣ መረጃን በመገደብ የሚደረግ ማንኛውም የተቃርኖን ስራ ዘላቂነት የለውም። እኛ ስንፈልግ የምንዘጋው ስንፈልግ የምንከፍተው ከሆነ አደጋ አለው። ግን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ብዙ ሰዎች እንዳይሞቱ ዳታን ዘግተንም ቢሆን የሰው ህይወትን ማትረፍ ከቻልን መጥፎ አይደለም።»

Symbolbild Facebbok vs Datenschutz Risse im Straßenbelag mit erodiertem Facebook Logo
ምስል imago/Ralph Peters

ድሮም በቂ እና ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት በሌላት ኢትዮጵያ በሰበብ አስባቡ ለቀናቶች አገልግሎት ሲቋረጥባት ትልቅ ተፅዕኖ መኖሩ ግልፅ ነው። ይህንን አገልግሎት ለማቋረጥ መንግሥት ከሚያወጣዉ ከፍተኛ የገንዘብ ክፍያ ባሻገር፣ በኢንተርኔት የሚሰጡ አገልግሎቶች በሙሉ ይስተጓጎላሉ።ከሁሉም በላይ የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ኢንተርኔትን መዝጋት ሰዎች መረጃና የመረጃ አገልግሎት የማግኘት መብታቸዉን መጋፋት ነዉ። በኢንተርኔት ካፌ ንግድ የሚተዳደረው ሀብታሙ ግን  የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ በስራው ላይ ተፅዕኖ ቢፈጥርበትም ትክክለኛው ርምጃ ነው ይላል።« ዋጋ አስከፍሎኛል ግን ከሀገር አይበልጥም ብዬ ችዬዋለሁ» ኑርዬ ኢንተርኔትን በብዛት የሚጠቀመው  እንደ ፌስቡክ ካሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘደዎችን መረጃ ለማግኘት ነው። እሱም የኢንተርኔት መቋረጡ አግባብ ነው ይላል። «ሀገር እስክትረጋጋ ድረስ የኢንተርኔት መቋረጡ በእኛ ላይ ተፅዕኖ አድርሷል ብዬ አልገምትም»

ስሙን መጥቀስ ያልፈለገው ወጣት ግን የኢንተርኔት መዘጋቱን በፍፁም አይደግፍም። « አማራ ክልል ውስጥ ብዙ ነገር እየሆነ ስለሆነ በዚህ አጋጣሚ ብዙ መረጃ አጥተናል።እና መዘጋቱን አልደግፈውም።» በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነው አብዱላዚዝ ግን የኢንተርኔት አገልግሎት አሁን የተቋረጠው ለራሳችን ሲባል ነው ይላል። « ከአመት በፊት ለአንድ ቀንም ሲዘጋ ደስተኛ አልነበርኩም። አሁን ግን ለሀገራችን ሰላም አስፈላጊ ነው።»

በአፋር ክልል የሚኖረው መስፍንም ቢሆን የኢትንተርኔት መቋረጡን በበጎ ከሚያዩት መካከል ነው። በሀገሪቱ ግጭቶች ሲከሰቱ በፍጥነት የኢንተርኔት አገልግሎትን መዝጋቱ በአገር ደረጃ ዘለቄታዊ መፍትሔ ያመጣል ብሎ ባያምንም ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ነው የሚናገረው። « እንደ አደገው ሀገር ስናስብ ኢንተርኔት መቋረጥ የለበትም ግን እኛ እና ዛሬ ላይ የፈራው ቴክኖሎጂ ብዙ አልተጣጣምንም።»ኢንተርኔት መጠቀም ቢያንስ እንደ ጀርመን ባሉ ሀገራት ከመሰረታዊ መብቶች አንዱ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ሶስት ሳምንታት ውስጥ የነበሩትን የኢንተርኔት መቋረጦች መምህርት መስከረም ለሁለት ከፍላ ነው የምታየው።« ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታ የተረጋጋ አይደለም። ትንሽ ነገር ብዙ ችግር የሚያመጣበት ሁኔታ ነው። ከዛ አንፃር በመንግስት በኩል ያለውን ስጋት እረዳለሁ። በፈተና የተዘጋውን ነገር ግን አልስማማበትም። ሌላ መንገዶች መፈለግ ይቻል ነበር። መምህርት መስከረም የሰሞኑን የኢንተርኔት መዘጋት ስጋቱን ብትረዳም፤ በውስጧ የጫረው አንድ ጥያቄ አለ። ለምን የሚል?« መዝጋቱን መክፈቱን ያመጣው ምንድን ነው?የምንግባባበት ሀቅ ስለሌለ ነው።»

Äthiopien Addis Ababa nach Putschversuch
ምስል Getty Images/AFP/E. Soteras

 ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ