1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች ድጋፍ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 4 2014

በኤስኦኤስ የህጻናት ማሳደጊያ መንደር መስራች ሔርማን ገማይነር ስም የተሰየመው የዕርዳታ ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች አራት ሚሊዮን ዩሮ መደበ። ገንዘቡ በኤስኦኤስ ኢትዮጵያ በኩል በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ማኅበረሰቦች ለመደገፍ ይውላል።

https://p.dw.com/p/4CZQz
Äthiopien | SOS-Kinderdörfer | Hermann Gmeiner Fonds
ምስል Alemnew Mekonnen

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች ድጋፍ

በአማራ፣ በትግራይና በአፋር ክልሎች በጦርነት ምክንያት የከፋ ችግር የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ማገዝ የሚችል የ4 ሚሊዮን ዩሮ (220 ሚሊዮን ብር) ድጋፍ የጀርመኑ ሔርማን ግማይነድር ፈንድ አስታወቀ፣ በኤስኦኤስ የህጻናት መርጃ በኩል ተግባራዊ የሚሆነው ፕሮጀክቱ  በአማራ ክልል ሶስት ዞኖች በተመረጡ ወረዳዎች 130ሺህ ህዝብ ተጠቃሚ ሆናሉ  ብሏል፡፡ የተጠቃሚ ወረዳ ተወካዮች ድጋፉ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ጥረት እንደሚያደርጉ አመልክተዋል፡፡
በጥቅምት 2013 ዓም የተጀመረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አሁንም ለብዙዎች ህይወት መመሳቀል ምክንያት ነው፡፡
ጦርነቱ በርካታ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመትን ያስከተለ ሲሆን በአማራ፣ በትግራይና በአፋር ሰብአዊ ቀውሱ አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
በጀርመን አገር የሚገኘው በህፃናት እንክብካቤ ላይ የሚሰራው HGFD የተባለው ደርጅት በሶስቱ ክልሎች የተፈጠረውን ሰብአዊ ቀውስ ሊያግዝ የሚችል የ2 ዓመት ፕሮጀክት የጀመረ ሲሆን ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ 4 ሚሊዮን ዩሮ መፍቀዱን የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚስተር ዊልፍሬድ ዊስሎትሲል  አመልክተዋል፡፡
ፕሮጀክቱን በባለቤትነት ተቀብሎ የሚያስተገብረው የSOS Ethiopia ኃላፊ ሳህለማሪያም አበበ ከተፈቀደው 220 ሚሊዮን ብር ውስጥ 145 ሚሊዮን ብር በአማራ ክልል ዋግሕምራ፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ አካባቢዎች በስራ ላይ የሚውል ሆናል ብለዋል፣ ቀሪ 75 ሚሊዮን ብር በቀጣይ ለአፋርና ትግራይ ክልሎች ለተመሳሳይ ስራ ይውላል ነው ያሉት፡፡ 
በSOS Ethiopia የሰብአዊ እርታዎች አስተባባሪ አቶ ቢኒያም አስፋው በብሮጀክቱ በአማራ ክልል 130 ሺህ ህዝብን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቅሰው በፕሮጀክቱ የሚሰሩ ተግባራትን ዘርዝረዋል፡፡
ከሰሜን ወሎ ግብርና ቢሮ የተወከሉት አቶ ባዬ ተሸመ፣ በጦርነቱ ወቅት የግብርና ስራው መጎዳቱን አስታውሰው ፕሮጀክቱ እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ከዋግኽምራ ሰቆጣ ጤና ጽ/ቤት የተገኙት አቶ ታምሩ ቢምረውም በብሔረሰብ አስተዳደሩ ገአበርገሌ፣ ከጻግብጂና ከትግራይ የተፈናቀሉ በርካታ ህፃናትና አረጋዉያን እንዳሉ ጠቅሰው የተፈቀደው ገንዘብ ለታለመለት ኣላማ እንዲውል እንሰራለን ነው ያሉት፡፡
ከደቡብ ወሎ ኩታ በር ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን አቶ ጌታቸው ይመር፣ ጦርነቱ ህፃናትን፣ ሴቶችንና አረጋውያንን በእጅጉ የጎዳ መሆኑን ጠቁመው የፕሮጀክት ድጋፉ ብዙ ችግሮችን ያቃልላል ብለዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ በቅርቡ በነበረው ጦርነት በአማራ ክልል ብቻ 288 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ጉዳዩን ሲያጠና የነበረ የጥናት ቡድን በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ዓለምነው መኮንን

Äthiopien | SOS-Kinderdörfer | Hermann Gmeiner Fonds
ምስል Alemnew Mekonnen