1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሞያሌው ግጭት

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 4 2011

በግጭቱ የሰዎች ህይወት ጠፍቷል ፣ንብረት ወድሟል፤ ሆስፒታል ተዘግቷል በርካቶችም ተፈናቅለዋል። የህክምና ባለሞያዎችም ሳይቀሩ ተሰደዋል። ከመካከላቸው ትናንት በግጭቱ የተጎዱትን ሲያክሙ በነበሩበት ሆስፒታል ያዩትን እና የሆነውን  የሚናገሩት እኚህ  የሞያሌ ሆስፒታል ሐኪም አንዱ ናቸው።

https://p.dw.com/p/3A3tp
Äthiopien vertriebene Moyale-Bewohner in der Oromia-Region
ምስል privat

የሞያሌው ግጭት

በኦሮምያ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ ባለፉት ሦስት ቀናት በተቀሰቀሰ ግጭት የሰዎች ህይወት እና ንብረት መጥፋቱን በርካቶችም መሰደዳቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ። እስከ ትናንት ድረስ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የሞያሌ ሆስፒታልም በግጭቱ ምክንያት ሥራውን ማቆሙን፣ሠራተኞቹም ህይወታቸውን ለማዳን ከከተማይቱ መሸሻቸውን አንድ የሆስፒታሉ ባልደረባ ለDW ገልጸዋል። DW በስልክ ያነጋገራቸው ወደ ተለያዩ ቦታዎች የተሰደዱ ሰዎች ምንም ዓይነት እርዳታ እንዳላገኙም ገልጸዋል። 
በሞያሌ ከተማ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ13 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።  ነዋሪዎች እንደሚሉት ግጭቱ እስከ ዛሬ በከተማዋ አይተዉት የማያውቁት ነው። እነርሱ ከባድ ሲሉ ከ«ጦርነት» ጋር በሚያስተካክሉት ግጭት፣ ከሞቱት ሌላ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው በርካቶች ናቸው። በግጭቱ ንብረት ጠፍቷል፤ ሆስፒታል ተዘግቷል በርካቶችም ተፈናቅለዋል። የህክምና ባለሞያዎችም ሳይቀሩ ተሰደዋል። ከመካከላቸው ትናንት በግጭቱ የተጎዱትን ሲያክሙ በነበሩበት ሆስፒታል ያዩትን እና የሆነውን  የሚናገሩት እኚህ  የሞያሌ ሆስፒታል ሐኪም አንዱ ናቸው። ከተለያዩ አካባቢዎች በሰሙት መረጃ መሠረት የሟቾቹ ቁጥር ከ13 ትም ሊበልጥ ይችላል ብለዋል ሐኪሙ ። በግጭቱ የተጎዱትን ትናንት በህክምና ሲረዱ የነበሩት እኚህ ሐኪም፣ ዛሬ በስራ ገበታቸው ላይ አልተገኙም። ማምሻውን ሆስፒታሉ ላይ የደረሰው ሁሉንም ነገር ቀይሮ ሆስፒታሉንም የመኖሪያ ቀያቸውንም ለቀው ለመሸሽ ተገደዋል። የሞያሌ ሆስፒታልም አግልግሎት መስጠት ማቆሙን ተናግረዋል።በንግድ ስራ የሚተዳደር DW ያነጋገረው ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ ሰኞ ግጭቱ ሲቀሰቀስ ገበያ ውስጥ ስራ ላይ ነበር። ያኔ ከመደብሩ ሸሽቶ ከወጣ በኋላ ወደ ቤቱም ሆነ ወደ ንግዱ መመለስ አልቻለም። አሁን ኬንያ ድንበር አካባቢ ባለ ስፍራ ላይ ነው የሚገኘው። የተፈናቀሉት ሀኪም እንደሚሉት በአሁኑ ግጭት ከሞቱት መካከል አዛውንቶች እና ባለሀብቶች ይገኙበታል። ሐኪሙም ሆነ ነጋዴው በየቦታው የተበተነው የሞያሌ ነዋሪ ወደ ከተማዋ ሊመለስ ቢፈልግ እንኳን ዋስትና አለው ብለው አያስቡም። ስለ ግጭቱ የዞንኑን እና የከተማዋን ባለሥልጣናት ለማነጋገር ሞክረን ነበር፤ልናገኛቸው አልቻልንም ።

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ