1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግጭቱ እንደቀጠለ ነዉ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 9 2011

የሞያሌ ሆስፒታል በሞርታር ጥይት ተመትቶ አገልግሎች መስጠት አቁሟል።የአይን ምሥክሮች እና ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ግጭቱ በከተማይቱ በስተሰሜን በቀለ ሞላ በተባለዉ ሆቴል አካባቢም ቀጥሎ የዋለዉ

https://p.dw.com/p/3AKp6
Infografik / Karte Protests and violence in Ethiopia,  2016

ሞያሌ ዉስጥ ባንድ ሳምንት ጊዜ ከ40 በላይ ሰዉ ተገደለ

በትናንትናው ዕለት በሞያሌ ከተማ በሚገኘው የበቀለ ሞላ ሆቴል በነበረ ተኩስ ቢያንስ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣን እና የአይን እማኞች ተናገሩ። በከተማዋ የሚገኘው ሆስፒታል በከባድ መሳሪያ ከተመታ በኋላ ሰራተኞች ለደኅነታቸው በመሸሻቸው አገልግሎት መስጠት ማቋረጡም ተሰምቷል።

የቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳኜ ቦሩ «ከሰዓት አካባቢ መከላከያ ሰራዊት ጣልቃ የመግባት አዝማሚያ ነበር። ወደ አመሻሽ አስራ አንድ ሰዓት አካባቢ በቀለ ሞላ የሚባል ሆቴል በእኛ ሚሊሺያ ላይ ወደ ሰባት ስምንት የሚሆኑ ሰዎች በመከላከያ እንደተጎዱ ነው መረጃ ያለኝ» ሲሉ ለDW ተናግረዋል።

ከሞያሌ ከተማ በ200 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የሚገኘው የያቤሎ ሆስፒታል የድንገተኛ ሕሙማን አስተባባሪ አቶ ሞሉ ዲማ «አጠቃላይ ያቤሎ ሆስፒታል የመጣው ትላንት እስከ ማታ 22 በጥይት የተመታ፤ ሰባት ሰው እዛ እንደሞተ ነው» ሲሉ ተናግረዋል። አቶ ዳኜ «የሞያሌ ሆስፒታል በአራት ከባድ መሳሪያ ተመቶ እዛ ውስጥ ያለ ባለሙያ እንዳለ ሸሽቶ አገልግሎት አቋርጧል። በጣም ከባድ ሁኔታ ላይ ነው ያለንው። ያቤሎ ሆስፒታል አሁን ማስተኛ ቦታ ራሱ የለም። በጣም በጣም ችግር ላይ ነው ያለንው። ያለው ባለሙያ ራሱ አይበቃም።» ሲሉም አክለዋል።

በሞያሌ ከተማ በሚገኘው የበቀለ ሞላ ሆቴል 7 ሰዎች ለሞት ያበቃው ተኩስ በምን ምክንያት እንደተቀሰቀሰ እስካሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ያለው ነገር የለም። አዲስ ስታንዳርድ የተባለው የድረ-ገፅ ጋዜጣ ከአካባቢው ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ እንደዘገበው ችግሩ በተፈጠረበት ወቅት የሞያሌ ከተማን የጸጥታ ሁኔታ የመቆጣጠር ኃላፊነት ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለማስረከብ በቦረና እና በጋሬ ጎሳዎች ተወካዮች መካከል ውይይት በመደረግ ላይ ነበር። አንዳንድ የዜና አውታሮች በትናንትናው ዕለት ብቻ በሞያሌ ከተማ በነበረ ግጭት 13 ሰዎች መሞታቸውን ዘግበዋል።

በቦረና ኦሮሞ እና በጋሬ ሶማሌ ጎሳዎች ግጭት በምትናጠው የሞያሌ ከተማ የመገበያያ መደብሮች እና የመግሥት መስሪያ ቤቶች ተዘግተው ሰንብተዋል። ባለፈዉ ሳምንት ዳግም ባገረሸዉ ግጭት ከአርባ በላይ ሰዉ መገደሉ ተነግሯል።

 ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ 

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ