1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምስራቅ አፍሪቃ ከፍተኛ ዝናብ የደቀነዉ አደጋና የደቡብ ሱዳን የሰላም ዉል

ቅዳሜ፣ ኅዳር 20 2012

በድርቅና በረሀብ ስማቸዉ ተደጋግሞ ሲጠራ የቆዩት የምስራቅ አፍሪቃ ሀገሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ  ሀገራቱ ወቅቱን ያልጠበቀና ከፍተኛ መጠን ያለዉ ዝናብ እየጣለ ነዉ። ለዚህ ከፍተኛ ዝናብ መነሻዉ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት  በአየር ንብረት መዛባት ሳቢያ  የዉቅኖሶች ሙቀት እየጨመረ መምጣቱ  ሲሆን፤

https://p.dw.com/p/3U0y0
Kenia Überschwemmungen
ምስል picture-alliance/AP

ትኩረት በአፍሪቃ

በጎርፍ መጥለቅለቅን፣ የሰብል ዉድመትን እንዲሁም የመሬት መንሸራተትን በማስከተል በሰዎችና በንብረት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነዉ። ችግሩ ባልተከሰተባቸዉ የቀጠናዉ ሀገሮችም ስጋቱ እያንዣበበ መሆኑን ትንበያዎች ያሳያሉ።

ከምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት መካከል አንዷ በሆነችዉ ኬንያም በቅርቡ በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች በጣለዉ ከፍተኛ ዝናብ  የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋ አጋጥሟቸዋል። በሀገሪቱ ፓኮት በተባለዉ ግዛት ምዕራባዊ አቅጣጫ በጎርጎሮሳዉያኑ ያለፈዉ ህዳር ወር መጨረሻ በጣለዉ ከባድ ዝናብ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት በማስከተሉ  ከ120 በላይ ሰዎች ሞተዋል።ከ 260  ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል።የአካባቢዉ ነዋሪ ፒተር ሎኮር እንደሚሉት በአደጋዉ መንገድና ድልድይን የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶችም እንዳልነበሩ ሆነዋል።የነዋሪዎቹ ቤቶችና ጥሪቶቻቸዉም በጥቂት ስዓታት ዉስጥ ወድመዋል።

«በየትኛዉም ቦታ የመሬት መንሸራተት አለ።የቆምንበት መሬት እንኳ በማንኛዉም ስዓት ሊንሸራተት ይችላል።በዚህ ሁኔታ  ብዙ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።ሰዎች የመኖሪያ ቤቶቻቸዉን ለቀዋል።እናም በአሁኑ ስዓት ማንም ቤቱ ዉስጥ መተኛት አልቻለም ምክንያቱም ቀጣዩ የመሬት መንሸራተት መቼ ሊከሰት እንደሚችል አናዉቅም።ብዙ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።በእዉነቱ ማንኛዉም በዚህ አካባቢ የሚኖር ሰዉ ሁሉ ወደ ቤቱ ለመመለስ ይፈራል።»

በአካባቢዉ ነዋሪዎች ላይ የደረሰዉ ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑም ለህይወት አድን ሰራተኞች ሳይቀር ሁኔታዉ አስቸጋሪ እንደነበር ይነገራል።የምዕራብ ፖኮት አዉራጃ ኮሚሽነር ፍሬዲሪክ ኪማንጋ እንደሚሉት ተጎጅዎቹን ወደ ጊዚያዊ ማቆያ ቦታ ማዛወር ግዴታ ነዉ።

Sudan Überschwemmungen
ምስል Reuters/A. Campeanu

 «ሰወች የመሬት መንሸራተት ያለባቸዉን ረባዳ ቦታዎች ለቀዉ ወደ ሌሎች ማዕከሎች እንዲሄዱ እየገፋፋናቸዉ ነዉ። ዝናቡ ለምን ያህል ጊዜ  እንደሚቀጥል ስለማናዉቅም ፤የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት የምግብ፣ የመድሃኒት አቅርቦቶችንና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማግኔት እንሰራለን ።«

በኬንያ የተከሰተዉ ጎርፍ ብዙዎችን ለሞትና ለመፈናቀል ከመዳረጉ ባሻገር  በጤና ረገድም እያሳደረ ያለዉ ጫና ቀላል እንዳልሆነ እንዳልሆነ ይነገራል።የምዕራብ ፖኮ ሪፈራል ሆስፒታል ከፍተኛ ሀኪም ዶክተር ታአቡ ሲሙ እንደሚሉት ከአደጋዉ የተረፉ ሰዎች የሳንባ ምች፣የተቅማጥና የሰዉነት መቆሳሰልን በመሳሰሉ በሽታዎች  እየተጠቁ ነዉ።

በኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እያደረስ ይገኛል። የሌሎቹን ሀገሮች ያህል ባይሆንም በመሬት መንሸራተትና በጎርፍም መጠነኛ ጉዳት በአንዳንድ አካባቢዎች አጋጥሟል።

በሌላዋ ምስራቅ አፍሪቃዊት ሀገር ደቡብ ሱዳንም በጎርጎሮሳዊዉ ህዳር ወር መጀመሪያ  ከመዲናዋ ጁባ በስተ ምስራቅ አቅጣጫ 340 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ፒቦር« በተባለች ከተማ በደረሰ የጎርፍ መጥለቅለቅ ከ50 በላይ ሰዎች ህይወት አልፏል።የአካባቢዉ የዕርዳታ ሰራተኞች እንደገለፁት ኢትዮጵያን በቅርብ በምታዋስነዉ  በዚህች የጠረፍ ከተማ የተከሰተዉ ጎርፍ ትምህርት ቤቶችን፣የገበያ ስፍራዎችንና መሰረተ ልማቶችን ያወደመ ሲሆን በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችም  ከቤት ንብረታቸዉ እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።በዚህም አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ደቡብ ሱዳናዉያን የበሽታና የረሃብ አደጋ ተደቅኖባቸዋል።

Südsudan Überschwemmungen Hütten
ምስል Getty Images/AFP/P. Louis

በሶማሊያም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በተፈጥሮና ሰዉ ሰራሽ አደጋ ለስደት የተዳረጉ  መሆናቸዉን የተባበሩት መንግስታት ዘገባ ያሳያል።ከነዚህም ዉስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በሀገሪቱ ከሚካሄደዉ የርስበርስ ግጭት በተጨማሪ ጎርፍና ድርቅን በመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ቀያቸዉን ለቀዉ የተሰደዱ መሆናቸዉን ዘገባዉ ያሳያል።

በታንዛንያም በጎርጎሮሳዊዉ ያለፈዉ ህዳር መጀመሪያ ማዋንዛ በተባለ አካባቢበጣለዉ ከባድ ዝናብ 10 ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረገ ጎርፍ ተከስቷል።

በአጠቃላይ በምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት እየታየ ያለዉ ይህ ያልተለመደ ከባድ ዝናብ የህንድ ዉቅያኖስ ከተለመደዉ በላይ ሙቀቱ በመጨመሩ ሳቢያ የመጣ ሲሆን ለዓመታት የዘለቀዉ የደን መጨፍጨፍና ድርቅም አስተዋፅኦ እንዳደረገ ይነገራል።በአሁኑ ወቅት በህንድ ዎቅያኖስ የሚታየዉ ከፍተኛ ትነትና ሙቀትም በመጭዎቹ 6 ሳምንታትም  ከባድ ዝናብ በአካባቢዉ ሀገራት ይጠበቃል ሲሉ የአየር ትንበያ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።የአየር ንብረት ለዉጥን የሚያስከትለዉን ጉዳት በዘላቂነት ለመከላከልም በሀገራቱ የአካባቢ ጥበቃ ስራ መጠናከር እንዳለበት ባለሙያዎቹ አሳስበዋል።

የደቡብ ሱዳን የሰላም ዉል ሳንካዎች

በጎርጎሮሳዊዉ ሰኔ 2011 ቀን ነጻነቷን ያወጀችዉ ደቡብ ሱዳን ላለፉት ስድስት ዓመታት ሰላም ርቋት ነዉ የቆየችዉ።በሀገሪቱ  ከጎርጎሮሳዊዉ 2013 ዓ/ም ጀምሮ  ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርና ምክትላቸዉ የነበሩት ሪክ ማቻር  ጎራ ለይተፈዉ ሲፋለሙ ቆይተዋል። በሁለቱ ተፈላሚ ሀይሎች  መካከል ሰላም ለማዉረድም በጎርጎሮሳዊዉ መስከረም 2018 የሰላም ስምምነት ተደርጎ ነበር።በስምምነቱ ሁለቱ ተፋላሚ ሀይሎች በጋራ ጦር ማቋቋምን፣የአንድነት መንግስት መመስረትን እንዲሁም የቀድሞዉን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻርን ወደ ቦታቸዉ መመለስን ያካተተ ነበር።ይህ ስምምነት በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት የደቡብ ሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሽረርም በወቅቱ ይህንን ብለዉ ነበር።

«የሽግግር መንግስት መመስረት በተለዬ ሁኔታ አስፈላጊ ነዉ።ምክንያቱም ምርጫ ለማካሄድ መዘጋጀትን ይጠቁማል። ምርጫዎች ደግሞ በጥቃት ሳይሆን በዲሞክራሲያዊ መንገድ መሪዎቻቸዉን እንዲመርጡ  ለዜጎች ዕድል ይሰጣሉ።ያ የሚሆነዉ ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት መደራጀት፣ መተቸትና መቀስቀስ ሲችሉ ነዉ።ያ ሁኔታ ግን እስካሁን አልተፈጠረም። »

ይህ የሚሆነዉ ግን የተቃዋሚ ሀይሎችም ይሁን የሳልቫኪር መንግስት የሰላም ስምነቱን በሙሉ ልብ ከተገበሩት  ብቻ መሆኑንም ዴቪድ ሽረር ገልጸዉ ነበር።

«የመጀመሪያዉና አስፈላጊዉ ቁልፍ ነገር የፖለቲካ ፈቃደኝነት ነዉ።ፓርቲዎች የሽግግር መንግስት ለመመስረት የደረሱትን ስምምነት መከተል አለባቸዉ።በሁለተኛ ደረጃ እነዚህ ሀይሎች እንደገና ሲዋሃዱ የሚመጣዉ መሻሻልም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ለሰላም ስምምነቱ ያላቸዉን ቁርጠኝነት ያሳያል።»

Uganda Südsudan - Friedensgespräch zwischen Präsident Kiir, Oppositionsführer Machar und der ugandische Präsident Museveni
ምስል Getty Images/AFP/S. Sadurni

 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም ዓቀፍ አጥኚ ቡድን ከሰሞኑ ያወጣዉ ዘገባ ግን የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት የተፈራረሙትን የሰላም ሥምምነት ገቢር ለማድረግ እያቅማሙ ነዉ በማለት ወቅሷል። ለዚህም እንደምክንያት የተነሳዉ ሁለቱ ተፋላሚ ሀይሎች በተፈራረሙት ዉል መሠረት ከሁለቱም ወገን 83 ሺሕ ተዋጊ ኃይል መመዝገብ የነበረበት ቢሆንም ከስምምነቱ ዉጭ ፕሬዝዳንት ሳላባኪር  ከራሳቸዉ ጎሳ አባላት ብቻ በብሄራዊ የፀጥታና ደህንነት ቢሮዉ በቀጥታ የሚታዘዙ 10 ሺህ አዳዲስ ተዋጊዎችን መልምለዋል በመባሉ ነዉ።ይህ የሳልቫኪር ተግባርም የሀገሪቱን ሰላም አደጋ ላይ ይጥላል ሲል የተባበሩት መንግስታት  ድርጅት ተችቷል።

መንግስት በስምምነቱ መሠረት ማስመዝገብ ከሚገባዉ የወታደር ብዛት እስካሁን ያስመዘገበዉ 7,400 ብቻ ሲሆን በተቃዋሚ በኩል ግን 32 ሺሕ ተዋጊዎች ተመዝግበዋል።

ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች  በመስከረሙ ውይይት  በጎርጎሮሳዊዉ ያለፈዉ ኅዳር  የአንድነት መንግስት  ለመመስረት ተስማምተዉ የነበረ ቢሆንም ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሰላም ውሉን ተግባራዊ እያደረገ አይደለም በሚል የመንግሥት ምሥረታውን በ አንድ መቶ ቀናት በማራዘም ወደ መጪዉ የካቲት ገፍተዉታል።

ይህንን ተከትሎም  አሜሪካ በደቡብ ሱዳን የሚገኙ አምባሳደሯን በቅርቡ መጥራቷ ይታወሳል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም የሳልባኪር መንግስት የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ያለዉ ቁርጠኝነት አነስተኛ ነዉ ሲል ተችቷል።

Uganda Flüchtlinge aus Südsudan
ምስል Getty Images/D. Kitwood

የድርጅቱ ዘገባ አያይዞ እንዳቀረበዉም  በአዲሲቱ አፍሪቃዊት ሐገር ላይ የተጣለዉን ማዕቀብ ጎረቤት ሐገሮች  በተደጋጋሚ መጣሳቸዉን አመልክቷል።እንደ ዘገባዉ  ማዕቀብ የተጣለባቸዉ የአማፂ ቡድን መሪዎች ኬንያ ዉስጥ የባንክ ሒሳብ ከፍተዉ እንዳሻቸዉ ይሰራሉ። አንድ የአማፂ ቡድን መሪ ደግሞ የዩጋንዳ ፓስፖርት ይዘዉ፣ በኬንያ አዉሮፕላን ደቡብ አፍሪቃ ድረስ መጓዛቸዉን አጥኚ ቡድን አጋልጧል። ዩጋንዳ ማዕቀብ ለተጣለበት የአማፂ መሪ ፓስፖርት ከመስጠቷ በተጨማሪ የይ ሪቨር በተባለዉ የደቡብ ሱዳን ግዛት ጦር ማስፈሯን የዓለም አቀፉ ድርጅት አጥኚ ቡድን አስታዉቋል።ጥናቱ ኢትዮጵያና ሱዳንም ማዕቀቡን በተለያዩ መንገዶች ጥሰዋል በማለት ወቅሷል።

በደቡብ ሱዳን በሁለቱ ተቀናቃኝ ሀይሎች የስልጣን ዉዝግብ ለአምስት አመታት በዘለቀዉ የእርስ በርስ ጦርነት እስካሁን  ከ400 ሺህ በላይ የሀገሪቱ ዜጎች ህይወታቸዉን አጥተዋል።አራት ሚሊዮን ዜጎችም ቤት ንብረታቸዉን ጥለዉ ተሰደዋል።ሁለቱ ተቀናቃኝ ሀይሎች ግን ሞቱንም ሆነ ስደቱን ለማቆም እስካሁን የረባ መፍትሄ አላመጡም።

ፀሐይ ጫኔ

ተስፋለም ወልደየስ