1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምርምር የተዘጋጀው የጤፍ ዝርያና ይዞት የመጣው ስጋት

ማክሰኞ፣ ግንቦት 8 2015

አዲስ የጤፍ ዝርያ በምርምር መገኘቱን በተመለከተ ስጋታቸውን በጽሑፍ ያቀረቡት የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪው ዶክተር ሚሊየን በላይ በምርምር ሰበብ በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ጎተራ ይገኙ የነበሩ የስንዴ እና የገብስ ዘሮች ቁጥር መመናመኑን በማስታወስ ጤፍም ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይገጥመው ባይ ናቸው። በጤፍ ላይ የሚመራመሩ ባለሙያዎች ምን ይሉ ይሆን?

https://p.dw.com/p/4RSHX
Landwirtschaft Äthiopien Dreschen von Hirse
ምስል Getty Images/AFP/S. Gemechu

ጤና እና አካባቢ

የጤፍን ምርታማነት ሊያሻሽል ይችላል በተባለ የምርምር ሂደት ከተለመደው የተለየ የጤፍ ዘር በአንድ የአሜሪካን እህል ላይ ምርምር በሚያካሂድ ተቋም መዘጋጀቱ ተሰምቷል። እንዲህ ያለው በምርምር የሚፈጠር ዘር የተፈጥሮ ዘሮችን ከአርሶ አደሩ ማሳ ሊያሳጣ አለያም ለጤናም ሆነ ለአካባቢ ተፈጥሮ አሉታዊ ጫና ሊያስከትል ይችላል በሚል ስጋታቸውን የሚያሰሙ አሉ። በአንጻሩ ምርምሩም ሆነ በዚህ መልኩ የሚገኘው ዘር አዲስ የመራቢያ ቴክኒክን ተጠቅሞ በምርታማነት የምግብ እጥረት ስጋት ያቃልላል በሚል የሚሞግቱም ጥቂት አይደሉም።

ጤፍ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያም ሲባለ ያለ ጤፍ የሚሉ በርካቶች ናቸው። ጤፍ ከሀገር ሲወጣ ባህርዩን ለውጦ እኔ ነኝ ላለች ባለሙያ ሳይቀር ፈታኝ በመሆኑ ብዙዎች የሀገራቸውን ምግብ በስደት ሀገር እየናፈቁ እንዲኖሩ ግድ ብሎ ከርሟል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ጤፍ በተለያዩ ሃገራት እየተመረተ በልዩ ልዩ መልክም ለምግብነት ያውም ጤናማ ከሚባሉት ተርታ በውድ ዋጋ በየፈርጁ እየተዘጋጀ መቅረብ ጀምሯል። መመራመር የሚወደው ዓለም ግን ይኽ የበቃው አይመስልም።

እናም ይመራመርበታል። በቅርቡም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አንድ የተክሎች ምርምር ማዕከል ድንክዬ ያለውን የጤፍ ዘር በዘመናዊ ቴክኒዎሎጂ ዘዴ ተጠቅሞ ማግኘቱን ይፋ አድርጓል። የምርምር ማዕከሉ እንደሚለው ድንክዬውን የጤፍ ዘር በምርምር ለማዘጋጀት የተፈለገው ጤፍ በተፈጥሮው ሲበቅል ረዥም ሆኖ ከማሳው ላይ ከመታጨዱ አስቀድሞ በንፋስም ሆነ በዝናብ በሚደርስበት ጫና እንዳይጋሽብ ወይም ተጎንብሶ እንዳይበላሽ ለማድረግ ነው። እንዲህ ባለው አጋጣሚም የጤፍ ምርት 25 በመቶ የሚቀንሰውን በማስቀረት ምርታማነትል ለማሻሻል እንደሆነም ያስረዳል። የጋሸበ ጤፍ ደግሞ ለተለያዩ የሰብል በሽታዎችና ተባዮች የመጋለጥ እንድል ስለሚኖረው ያንን ሁሉ ያስቀራልም ባይ ነው።

የአካባቢ ተፈጥሮ ተሟጋች የሆኑት ዶክተር ሚሊየን በላይ የምርምር ተቋሙ ያወጣውን መረጃ መሰረት በማድረግ አስፈላጊው ጥንቃቄ ይደረግ ባይ ናቸው። ዶክተር ሚሊየን በምርምር ዘረመላቸው የተሻሻለ ስለሚባሉ የእህል ዝርያዎች የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች መኖራቸውን ነው ያመላከቱት። ቀዳሚዎቹም አስተማማኝነቱ እና በሀገሬው የሚገኙ ነባር የዘር አይነቶች ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተጽዕኖን የሚመለከቱ ሲሆን ኢትዮጵያን በተመለከተ ይህን የመከታተል አቅም አለ ወይ ሲሉም ይጠይቃሉ።

Äthiopien Ziegen und Teff im Sonnenuntergang
የጤፍ ማሳ አማራ ክልል ምስል Imago Images/Design Pics/P. Langer

በኢትዮጵያ የዘር ባንክ እስከ 6000 የሚደርስ ሀገር በቀል የሆነው የጤፍ ዘር አይነት እንዳለ ነው ዶክተር ሚሊየን የጠቆሙት።  የደብረ ዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ሰሎሞን ጫንያለውም ይህንኑ ነው ያረጋገጡልን። በጤፍ ላይ ምርምር ከሚያካሂዱት ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት ዶክተር ሰሎሞን እንደሚሉት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር በርካታ ሰብሎችን የተመለከተ ምርምር በስፋት ይካሄዳል። ጤፍ ግን ብዙም አልተሠራበትም ነው የሚሉት። ተመራማሪው እንደሚሉት በሄክታር በአማካኝ የሚገኘው 18 ኩንታል ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ገና ጤፍ በወጉ ስላልተጠና እና ዘመናዊ የሆነ ሳይንሳዊ ምርምር ሥራዎች ስላልተሠሩበት እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል። እሳቸው እንደሚሉትም እንዲህ ባሉት ምርምሮች የሚገኙ አዳዲስ ዝርያዎችን በማዘጋጀት አርሶ አደሩ በጡፍ በኩል ያሉበትን የምርታማነት ማነቆዎች መፍታት ይቻላል። ጤፍን በተመለከተ ምርታማነቱ ላይ ማነቆ ናቸው ካሏቸው መካከል መጋሸብ አንዱ ነው። የአሜሪካው የምርምር ተቋምም ለዚህ መፍትሄ ይሆናል ያለውን መሥራቱንም ያመለክታሉ።

የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪው ዶክተር ሚሊየን በላይ በምርምር ተገኘ የተባለው የጤፍ ዝርያ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት ቢያንስ አምስት ቢበዛ አስር ዓመት ድረስ በቂ ጥናት እና ሙከራ ሊደረግበት ይገባል ባይ ናቸው። ጥንቃቄው ተገቢ ነው በሚል ሃሳቡን የተጋሩት የምርምር ባለሙያው ዶክተር ሰሎሞን ጫንያለውም ግን የአሜሪካው የምርምር ተቋም ያዘጋጀው አዲሱ የጤፍ ዝርያን የሚመለከተው ጉዳይ ገና በሂደት ላይ መሆኑን ነው የገለጹልን። ጤፍ ቢያንስ ከ60 ሚሊየን ሕዝብ ኢትዮጵያውያን ቀለብ እንደሆነ ይታመናል። ዛሬ ዛሬ ግን ለጤና ተመራጭነቱ ሰብልነቱ በማይታወቅባቸው ሃገራት ሳይቀር ተፈላጊ እየሆነ መምጣቱ የአርሶ አደሮችን ትኩረት በአውሮጳም ሆነ በአሜሪካ እየሳበ ነው። የሚደረገው ምርምር ምርታማነቱን ማሻሻሉ አዎንታዊ ቢሆንም ነባሩ እና የተፈጥሮው ዘር በመሃል እንዳይጠፋ ጥንቃቄ እንዲደረግ ይመከራል። 

ሸዋዬ ለገሠ 

ኂሩት መለሰ