1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በመንገድ ደህንነት ቀን በተሽከርካሪ አደጋዎች 49 ሰዎች ሞቱ

ሰኞ፣ ኅዳር 15 2012

በኢትዮጵያ የሚደርሰው የተሽከርካሪ አደጋ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን የዕድሜ ገደብ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ። በኦሮሚያ ትናንት እሁድ በሰባት የተለያዩ አካባቢዎች በደረሱ አደጋዎች የ34 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ60 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል። 

https://p.dw.com/p/3Tha1
Äthiopien Busunfall in Addis Abeba
ምስል DW/S. Muchie

በመንገድ ደህንነት ቀን በደረሱ የተሽከርካሪ አደጋዎች 49 ሰዎች ሞቱ

በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚደርሰው የተሽከርካሪ አደጋ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን የዕድሜ ገደብ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጀምር የፌደራል ትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ። በኦሮሚያ ክልል ትናንት እሁድ ብቻ በሰባት የተለያዩ አካባቢዎች በደረሱ የተሽከርካሪ አደጋዎች የ34 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ60 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል። 

ትላንት ከደረሱት የመኪና አደጋዎች አስከፊ የተባለውን እና የ18 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው አደጋ የተከሰተው ከአዲስ አበባ አቅራቢያ በምትገኘው ሆለታ ከተማ አካባቢ ነው። አደጋው ሲከሰት በቦታው የነበሩ አንድ የአይን እማኝ ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት ሃያ ሰዎችን አሳፍሮ የነበረ ሚኒባስ መኪና በጠባብ መንገድ ላይ ከልክ ባለፈ ፍጥነት እየተሽከረከረ ባለበት ወቅት ከጭነት መኪና ጋር በመጋጨቱ አደጋው አስከፊ ሆኗል።   
“ሀይሩፉ ወደ አምቦ ነው የሚሄደው አንደኛው ደግሞ ወደ ሆለታ ነው የሚመጣው። ሁለቱም በመንገዳቸው ላይ ነው ያሉት። ሁለቱም ከርጽ ኣካባቢ ነበሩ። አንደኛው መኪና ቁልቁለቱን ሲይዝ በሾፌሩ በኩል ያለው የፊት ለፊት ጎማ በፈንዳቱ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ከሃይሩፉ የህዝብ ማመላለሻ ጋር ተጋጩ። ሃይለኛ የፍንዳታ ድምጽም ተሰማ። ወዲያው በመስታወት በኩል ሰዎች መውደቅ ጀመሩ፤ ሶስት በጽኑ የቆሰሉ ሰዎችን አወጣን፤ 16 አስክሬንም አነሳን። “
በዚሁ ዕለት የተከሰተው ሌላኛው አደጋ ደግሞ በምስራቅ ወለጋ ዞን ሌቃ ዱለቻ ወረዳ ገተማ በምትባል ትንሽ ከተማ አቅራቢያ ነው። በአደጋው የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን እና በ31 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት መድረሱን የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አሰፋ ነገሪ ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል።
“እኛጋ የመጡት ብዛታቸው 33 ናቸው። ከሰላሳ ሶስቱ ሁለቱ ሞተዋል።”
የመንገዶች ደህንነት አለመጠበቁ እና የአሽከርካሪዎች የብቃት ችግር በየጊዜው ተመሳሳይ አደጋዎችን ለማስተናገድ ተገደናል ሲሉ የድንገተኛ አደጋዎች ስፔሽያሊስቱ ዶ/ር አሰፋ አስረድተዋል።
“በመንገዶች ላይ በጣም መሰራት አለበት ። መንገዶቻችን ለተሽከርካሪዎች አመቺ አይደሉም። ምልክቶች የሉም። በተለይ ወደ ገጠር አካባቢ ሲኬድ አደገኛ መንገዶች ላይ ምንም የተቀመጠ ነገር የለም ። በተጨማሪም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት ተሽከርካሪዎች አሮጌ በመኾናቸው እና የአሽከርካሪዎች አንዳንድ ጊዜ የሚፈጥሩት ቸልታ አደጋ እየፈጠረ ነው።”
በትናንትናው ዕለት ከሁለቱ ስፍራዎች ከደረሱት አደጋዎች በተጨማሪ በቢሾፍቱ የ1 ሰው ሞት እና 14 ሰዎች ላይ ደግሞ ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል። በአርሲ ዞን አዳባ ወረዳ ደግሞ በመኪና አደጋ የ7 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ 5 ሰዎች ላይ ደግሞ ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት ተከስቷል። በምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳም በተመሳሳይ አደጋ የ4 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን በምስራቅ ሸዋ ዞን አደኣ ወረዳ ኡዴ ደንካካ ቀበሌ ትናንት ሌሊት በደረሰው የትራፊክ አደጋ በአንድ ሰው ላይ የሞት በ18 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ከየአካባቢዎቹ ያገኘናቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የተሽከርካሪ አደጋ በየአመቱ የአምስት ሺህ ሰዎችን ህይወት እንደሚቀጥፍ እና 15 ሺህ ሰዎችን የአካል ጉዳተኛ እንደሚያደርግ የፌደራል ትራንስፖርት ሚኒስቴር ገልጿል። በትራፊክ አደጋዎቹ ከ800 ሚሊዮን ብር የሚልቅ ንብረት ለውድመት እንደሚዳረግም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል። ሚኒስቴሩ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን የአገልግሎት ዘመን የሚገድብ አሰራር በሁለት ወር ውስጥ ተግባራዊ እንደሚያደርግ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ እንዳልካቸው ጸጋዬ ተናግረዋል።
“የዕድሜ ገደባቸው ወይም ያረጁ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገቡበት ኹኔታ ጋር ተያይዞ ያንን የሚያስቀር መመሪያ አሁን ተዘጋጅቷል። በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል። ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች የዕድሜ ገደብ የሚወስን መመሪያ በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል። ሁሉም ተሳፋሪዎች ቀበቶ እንዲያስሩ የሚያስገድድ መመሪያም በዚህ ወር ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ተሰርቶ እንደተጠናቀቀ አንድ ላይ ተግባራዊ ይደረጋል። “
የበርካታ ሰዎችን ህይወት በቀጠፉትና በርካቶችን ለአካል ጉዳት በዳረጉት የትናንትናዎቹ አደጋዎች የደረሱት መንግስት አገር አቀፍ የመንገድ ደህንነት ቀንን በሚያከብርበት ቀን መሆኑ የተለየ አጋጣሚ መሆኑን በርካቶች ይናገራሉ።

ታምራት ዲንሳ

ተስፋለም ወልደየስ