በመስቀል አደባባዩ የቦምብ ፍንዳታ 4 ሰዎች ሞተዋል - የዓይን እማኝ
እሑድ፣ ሰኔ 17 2010ትናንት ቅዳሜ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ. ም. በመስቀል አደባባይ በነበረው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ አራት ሰዎች መሞታቸውን አንድ የአይን እማኝ ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። ከሰላሌ ተጉዘው በሰላማዊ ሰልፉ ላይ መሳተፋቸውን የሚናገሩት አቶ አባይ ተስፋዬ የተባሉት እኚሁ የዓይን እማኝ በፍንዳታው ጉዳት ደርሶባቸዋል።አቶ አባይ "ዶክተር አብይ አውርቶ ሲጨርስ ፈንጂ ለቀቁብኝ። እኔ ጋር የነበሩት አራት ሰዎች ናቸው። አራቱ ሰዎች ወዲያውኑ ሞቱ። እኔ ተረፍኩ" ብለዋል። የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ምኒስትር ደዔታው አቶ ከበደ ወርቁ ግን የሞቱ ሰዎች ቁጥር 2 ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ አቶ አባይ ሁሉ በዘውዲቱ ዘውዲቱ ሆስፒታል ተኝተው ህክምናቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ ግርማ ተክሉ የተባሉ የሰልፉ ተሳታፊ "ሰላም ነው ብለን ደም እንደሚፈስ ሳናውቅ መጥተን" ጉዳት ደረሰብን ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ግርማ በቦምብ ፍንጣሪ አፋቸው እና እግራቸው ላይ መቁሰላቸውን ገልጸዋል። "ዶክተር አብይ ንግግሩን ጨርሶ ተሰናብቶ ፊቴን ልክ ወደቤቴ እንዳዞርኩኝ አንድ እግሬን ሳላነሳ ድው አለ በቃ፤ ጭለማ ሆነብን" ሲሉ በጊዜው የነበረውን ሁኔታ አስረድተዋል።
የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ ያጠናቀረውን ዝርዝር ዘገባ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።
ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ
እሸቴ በቀለ