1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ንግግር

ማክሰኞ፣ ሰኔ 7 2014

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 13ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ አራት ኪሎ በሚገኘው የምክር ቤቱ የጉባኤ አዳራሽ ተካሂዷል። በምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለቀረቡላቸው ልዩ ልዩ ምጣኔ ሀብትን፣ ሰላምና ፀጥታን እንዲሁም የአገሪቱን ፖለቲካ የተመለከቱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ እንዲሁም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

https://p.dw.com/p/4ChNC
Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed im Parlament
ምስል Solomon Muche/DW

በምክር ቤቱ አባላት ከተነሱ ኢኮኖሚ ነክ ጥያቄዎች መካከል "የኑሮ ውድነት መባባስ ሕዝብን በእጅጉ እያማረረ በመሆኑ መንግሥት ይህንን ለመፍታት ምን እየሰራ ነው" የሚለው ይገኝበታል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ በአገሪቱ እየተከሰቱ ባሉ ውጫዊ እና ውስጣዊ ችግሮች መነሻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሥራ አጥነት ምጣኔ 17.7 በመቶ መድረሱ አሳሳቢ መሆኑ ተጠቅሶ ጥያቄ ቀርቧል።

በሌላ በኩል አገራዊ የለውጥና የሽግግር ሂደትን አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ "ባለፉት 4 ዓመታት ውስጥ ቃል የገቧቸው የለውጥ ተግባራት ምን ያህል ተፈፅመዋል ? ለውጡና አገራዊ ሪፎርሙ ሀዲዱን ስቶ ከመስመሩ አልወጣም ወይ ? ሪፎርም ተብሎ ሲገለጽ የነበረው ሂደት አልከሸፈም ወይ ? ዛሬም እኔ አሻግራችኋለሁ በሚለው አቋምዎት እንደፀኑ ነው ወይ?" የሚሉ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት ተከትሎ ውድመትና ዝርፊያ እንዲሁም መፈናቀል ለደረሰባቸው አካባቢዎች መንግሥት በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም ምን እየሠራ እንደሆነም ጥያቄ ቀርቧል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ከትግራይ ክልል ድንበር አካባቢ ያሉ ዜጎች ዘላቂ ሰላም አለማግኘታቸውና ከትግራይ ክልል ወደ አማራ ክልል የሚገቡ ተፈናቃዮችን በሚመለከት መንግሥት ምን ለመሥራት አስቧል የሚል ጥያቄ ቀርቧል።
አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን በተመለከተ "ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ? ኮሚሽኑ ሥራውን በነጻነትና በገለልተነት እንዲያከናውን መንግሥት ምን ድጋፍ እያደረገ ነው" የሚል ጥያቄ ቀርቧል። "ነፍጥ አንግበውም ሆነ መሣሪያ ሳይይዙ በምክክር ሂደቱ አንሳተፍም የሚሉ ቡድኖችን አቋም በተመለከተ የመንግሥት አቋም ምንድን ነው" የሚለውም ተነስቷል።
"ሕወሓት አሁንም ጦርነት ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ እየተናገረ ይገኛል። በመሆኑም መንግሥት አደጋውን ለመከላከል ምን ያኽል ዝግጁ ነው? " በሚል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠይቀዋል።

Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed im Parlament
ምስል Solomon Muche/DW

በአማራ ክልል ከሰሞኑ እየተደረገ ነው የተባለውን "ሕግ የማስከበር ዘመቻ " ተከትሎ "መልካም ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው። ይህ የኅብረተሰቡን የሕግ ይከበርልን ጥያቄ እየመለሰ ያለ እርምጃ ስለሆነ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" በሚል ሥራውን ያበረታቱ የምክር ቤት አባል ነበሩ።
ይሁንና " ከኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የሕወሓት ቡድንን በመመከት ረገድ ከፍተኛ ሚና የነበረውን ፣ አሁንም በተጠንቀቅ ቆሞ ኢትዮጵያን ለመጠበቅ ምሽግ ውስጥ ያለውን ፋኖ እና የፋኖ አባላትን ማሰርና ማሳደድ እየታዬ ነው፣ ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት በዘመቻ ሕግ የማስከበር ሥራ የሚከናወነው በስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ የሚተገበር በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እና በሌሎች አካባቢዎች ኮማንድ ፖስቶች ተቋቁመው የሚካሄዱ ኦፕሬሽኖች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሆነ የአፈፃፀም መርማሪ ቦርድ በሌለበት ሁኔታ እየተሰሩ ስለሆነ የዜጎች መብቶች ሳይሸራረፉ እየተከበረ ስለመሆኑ ይብራራ" በሚል በአማራ ክልል ብቻ 4500 ሰዎች መታሰራቸው ተጠቅሶ ጥያቄ ቀርቧል።

Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed im Parlament
ምስል Solomon Muche/DW

"መንግስት ሕግ ያስከብር ማለት መንግስት ሕግ እየጣሰ ዜጎችን ያሸብር ማለት አይደለም። መንግስት ሕግ የማስከብር መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታ አለበት ሲባል ማስከበርና መጠበቅ ያለበትን ሕግ የመጣስና የማፍረስ መብት አለው፤ ይኑረው ማለት አይደለም። ባለፈት ሦስት ሳምንታት «ሕግ ለማስከበር» በሚል በከፈተው ዘመቻ ዜጎች በሕገመንግስቱና ኢትዮጵያ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት መከበር ስምምነቶች ጭምር ጥበቃ የሚደረግላቸውን መብቶቻቸውን የጣሰ፤ ከሕግ ማስከበሩ ይልቅ ሕጋዊ ሂደቶችን ያልተከተለ መሆኑ፣ ሕግ ለማስከበር በሚል ሕግ እየተጣሰ ሕፃናትን ጨምሮ 35 የሚደርሱ ዜጎች ያለፍርድ በፀጥታ አካላት ተገድለዋል። 40 የሚጠጉ የድርጅቴ አመራሮችና አባላት ታስረዋል።" ሲሉ የተቃዋሚው የአብን አመራር አባል ጠይቀዋል።
"ከ20 በላይ ጋዜጠኞች ታስረዋል። በርካታ ሺዎች ያለፍርድቤት ትእዛዝ በቀንና በሌሊት በፀጥታ አካላት እየታፈኑ ወዳልታወቀ ቦታ ተወስደው ተሰውረዋል። እስካሁንም ፍርድቤት ያልቀረቡና ቤተሰብ የማይጠይቃቸው፤ የት እንዳሉም የማይታወቁ ዜጎች አሉ። ሕግ በመጣስ እና ሕዝብን በማሸብር ግን ሊሆን አይገባም። የሚሉ ጥያቄዎችም ቀርበዋል።

በተለያየ መልኩ እየተነሳ ያለን የድርድር ጉዳይ በተመለከተ ጉዳዩ ለሕዝብ ግልጽ እንዲደረግለት እና ተጀምሮም ከሆነ የድርድር ሂደቱ " አማራን እና ኤርትራን ያገለለ እንዳይሆን" የሚሉ ጥያቄዎችም ቀርበዋል።

ሰለሞን ሙጬ
ልደት አበበ