1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በህዳሴው ግድብ ድርድር የአሜሪካዊው ዲፕሎማት ትችት

ዓርብ፣ የካቲት 27 2012

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውኃ አሞላል እና አለቃቀቅን በተመለከተ ኢትዮጵያ ግብፅ እና ሱዳንን የማነጋገር ኃላፊነቱን ዩናይትድ ስቴትስ ለግምጃ ቤት ሹሞቿ መስጠቷ እንዳስገረማቸው በኢትዮጵያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሺን ተናገሩ።

https://p.dw.com/p/3YzDV
BG Grand Renaissance Dam | Standort des Grand Ethiopian Renaissance Damms (2013)
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Asmare

ህዳሴው ግድብ ድርድር የአሜሪካዊው ዲፕሎማት ትችት

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውኃ አሞላል እና አለቃቀቅን በተመለከተ ኢትዮጵያ ግብፅ እና ሱዳንን የማነጋገር ኃላፊነቱን ዩናይትድ ስቴትስ ለግምጃ ቤት ሹሞቿ መስጠቷ እንዳስገረማቸው በኢትዮጵያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሺን ተናገሩ። ዴቪድ ሺን ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ  ዩናይትድስቴትስ የመልካም አሸማጋይ ሚና መጫወት ከፈለገች  አቋሟ ሚዛናዊ መሆን ይኖርበታል በማለት ተናግረዋል። ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሼን፤ አሁን በአሜሪካው ጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች መምህር ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ። የቻይና፣ አፍሪካ፣ የባሕረ ሰላጤው ሃገራት እና የአፍሪካ ግንኙነት እንዲሁም በቀይ ባሕር ጉዳዮች ተመራማሪም ናቸው። በዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት እና በዓለም ባንክ አሸማጋይነት በታላቁ የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል ፣ አለቃቀቅ እና አስተዳደር ላይ በኢትዮጵያ ግብፅ እና ሱዳን መካከል ሲደረግ የነበረው ድርድር በመጨረሻው ሰዓት ኢትዮጵያ ከድርድሩ በመቅረቷ ሳይቋጭ ቀርቷል። ዴቪድ ሼን ከዶይቸ ቬለ ጋር በነበራቸው ቆይታ ዩናይትድ ስቴትስ ሦስቱን ሃገራት ለማሸማገል የግምጃ ቤት ዘርፏን መምረጧ ግርምትን እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። ለድርድሩ መቋጫ ውጤት ማጣት ለድርድሩ ባህሪ የተሻለ ዕውቀት ያለው አካል ማሸማገል ነበረበት ይላሉ። 
«የትራምፕ አስተዳደር እና የግምጃ ቤቱ ምክር ቤት በተለይም ሚኒስትሩ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምን ያህል ውኃ መሞላት አለበት፤ ከተሞላ በኋላስ በየዓመቱ ወደሱዳን እና ግብፅ የሚወርድ ምን ያህል ውኃ መለቀቅ ይኖርበታል በሚለው ላይ ሦስቱን ሃገራት ለማሸማገል ከሚገባው በላይ ወደጉዳዩ ውስጥ መግባታቸውን ተረድተሀል ብዬ እገምታለሁ። እኔ እንደተረዳሁት  ጥያቄው  ከግብፁ ፕሬዚዳንት ኣልሲሲ በቀጥታ ወደፕሬዝደንት ትራምፕ እንደመጣ ነው። ለለግምጃ ቤት ሚኒስትሩም ሊከናወኑ የሚገባቸውን ኃላፊነቶች ፈርመው ሰጥተዋል። ከጥር ወር መጀመርያ ጀምሮም ዋሽንግተን እና በተለያዩ ቦታዎችም በርካታ ስብሰባዎች አካሂደዋል።  ነገር ግን  ዩናይትድ ስቴትስ ሶስቱን ሃገራት ለማሸማገል በቂ ባለሞያዎች የሚገኙበት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እያለ ስለድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ብዙም ዕውቀት የሌለው ግምጃ ቤቱ ይህንን ኃላፊነት እንዲወስድ መደረጉ እኔን ያስገረመኝ አንደኛው ጉዳይ ነበር»  

Grand Ethiopian Renaissance Dam
ምስል picture-alliance/dpa/G. Forster

 ዩናይትድ ስቴትስ ገለልተኛ ሆና ማደራደር ነበረባት በሚል ከምክር ቤቶቿ አባላት ጭምር ወቀሳ እየተሰነዘረባት ይገኛል። ይህንኑ ተከትሎም  ለዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ እና ከግብፅ ማንኛቸው የበለጠ አስፈላጊዋ ናቸው ብለው ያስባሉ የሚል ጥያቄ ተነስቶላቸው ነበር። 
 «ከታሪካዊ መሠረቱ ብንመለከት በእርግጥ ሁለቱም ሃገራት ለዩናይትድ ስቴትስ በጣም ጠቃሚ ናቸው። አፍሪካን በሚመለከቱ  ጉዳዮች ኢትዮጵያ ከግብፅ በተሻለ ለዩናይትድ ስቴትስ በጣም ጠቃሚ ሀገር መሆኗን እሞግታለሁ። እርግጥ ነው ፤ በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳይ ላይ ግብፅ ትልቅ ሚና እንዳላት አይካድም። ግብፅ የመካከለኛው ምስራቅን በሚመለከቱ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ የበለጠ ጠቀሜታ አላት። የመካከለኛው ምሥራቅ እና የአፍሪካን ጉዳይ በአንድነት የምታቀርብ ከሆነ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ከሁለቱ ሃገራት ጋር ያላት የግንኙነት ባህሪ የሚያሳየው ፤ በእውነት ለመናገር ግብፅ ከኢትዮጵያ የተሻለ ለዩናይትድ ስቴትስ አስፈላጊ ሀገር ነች ማለት ይቻላል።»
አሜሪካ የፍልስጥኤምን ጉዳይ እልባት ለማበጀት ይዛ የመጣችው ሃሳብ በአረብ ሃገራት በኩል ተቀባይነት በማጣቱ የግብፅን ድጋፍ ለማግኘት በድርድሩ ለግብፅ በመወገን ካይሮን ለመጥቀም አስባ ይሆን? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዴቪድ ሺን ሃሳቡ በአንዳንድ ምሁራን እና በመንግሥት አካባቢ ያሉ ሰዎች  ዘንድ እየተነሳ ያለሃሳብ መሆኑን ያስረዳሉ። ይህን አስመልክተውም አሜሪካ የእስራኤል እና ፍልስጤምን ግጭት ዘላቂ እልባት ያስገኛል ብላ ያቀረበችው የሁለት ሀገርነት የሰላም ሃሳብ በአብዛኞቹ የአረብ ሃገራት ተቀባይነት ማጣቱ ግብፅን የምትይዝበት አንዱ መንገድ የህዳሴውን ግድብ ፍላጎት ማስጠበቅ ሊሆን እንደሚችል ነው ዴቪድ ሺን የሚገልጹት።
«ይህ እርግጥ ነው ሊሆን ይችላል ፤ ዩናይትድ ስቴትስ የፍልስጥኤማውያንን ጥያቄ ለመፍታት ላቀረበችው የሰላም ሀሳብ ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘት ትፈልጋለች። በአብዛኞቹ የአረብ ሃገራት ደግሞ ብዙ ተቀባይነት የለውም። እናም ይህ ከግብፅ ጋር አንድ ነገር ሰጥቶ በለውጡ ለፍልስጤም ባቀረበችው ሃሳብ ድጋፍ ለማግኘት ያለመ ግብይት ሊሆን ይችል ይሆናል። ግን ጉዳዩ እርግጥ ይህ ይሁን አይሁን ግን አላውቅም።» 
ዴቪድ ሺን ከመምህርነት ስራቸው ጎን ለጎን የቻይና አፍሪካ ፣የገልፍ ሃገራት እና የአፍሪካ ግንኙነት እንዲሁም በቀይ ባህር ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን ይሰራሉ።

መክብብ ሸዋ

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሠ