1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባለፉት ሁለት አመታት ከ250 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረቢያ ተጠርዘዋል

ሐሙስ፣ ነሐሴ 9 2011

ሳዑዲ አረቢያ ሕገ-ወጥ ያለቻቸውን የውጭ አገር ዜጎች ማባረር ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በወር 10 ሺሕ በአጠቃላይ ከ260 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን መጠረዛቸውን ሒውማን ራይስት ዎች ባወጣው ዘገባ አስታውቋል። በዘገባው በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚያመሩ ኢትዮጵያውያን የከፋ ስቅየት እንደሚገጥማቸው ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/3NwHc
Jemen Aden illegale Migranten aus Afrika
ምስል picture-alliance/Xinhua/M. Abdo

ባለፉት ሁለት አመታት ከ250 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረቢያ መጠረዛቸውን ሒውማን ራይትስ ዎች አስታወቀ። ኢትዮጵያውያኑ በግዳጅ ከመባረራቸው በፊት በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች አስከፊ የእስር ጊዜ እንደሚያሳልፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በዛሬው ዕለት ባወጣው ዘገባ ገልጿል። 

በዘገባው መሠረት በወር 10 ሺሕ በአጠቃላይ ወደ 260 ሺሕ ገደማ ኢትዮጵያውያን ከጎርጎሮሳዊው 2017 እስከ መጋቢት 2019 ባሉት ጊዜያት ወደ አገራቸው በግዳጅ ተመልሰዋል።
በጎርጎሮሳዊው ኅዳር 2017 ዓ.ም. የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ሕገ-ወጥ ያላቸውን የውጭ ዜጎች በግዳጅ ወደ አገራቸው መጠረዝ ሲጀምር 500 ሺሕ ገደማ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ እንደነበሩ ዓለም አቀፉ የስደተኞር መርጃ ድርጅት (IOM) ይገምታል። የሳዑዲ ባለሥልጣናት ዘመቻውን ከጀመሩ በኋላ የአገሪቱን የሥራ አሊያም የመኖሪያ ሕግጋት ተላልፈዋል ያሏቸውን የውጭ አገር ዜጎች በቁጥጥር ሥር አውለው መክሰሳቸውን አሊያም መጠረዛቸውን የሒውማን ራይትስ ዎች ዘገባ ይጠቁማል። 

Jemen afrikanische Migranten in Harad
ምስል DW/Saeed Al soofi

ባለፈው ነሐሴ የሳዑዲ አረቢያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የመኖሪያ ፈቃድ የሕግ ጥሰት የፈጸሙ 2.8 ሚሊዮን ሰዎች፣ የሥራ ፈቃድ ሕግጋትን የተላለፉ 557 ሺሕ ሰዎችን ጨምሮ 3.6 ሚሊዮን ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ወደ ሳዑዲ አረቢያ ገብተዋል የተባሉ 61,125 ሰዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ሒውማን ራይትስ ዎች ገልጿል። 

ቀይ ባሕርን ወይም የኤደን ባሕረ ሰላጤን በጀልባ በማቋረጥ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን በየመን የጉልበት ብዝበዛ እና ስቅየት እንደሚገጥማቸው ድርጅቱ አስታውቋል። 

ሒውማን ራይትስ ዎች አነጋገርኳቸው ያላቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ከአቅማቸው በላይ በጫኑ ጀልባዎች ያለ ምግብ እና የመጠጥ ውሀ ያደረጉት እስከ 24 ሰዓታት የሚረዝም ጉዞ እጅግ አደገኛ እንደነበር ተናግረዋል። “በጀልባው ላይ 180 ሰዎች ነበሩ። ነገር ግን 25 ሞተዋል” ሲል አንድ ከሳዑዲ አረቢያ ተጠርዞ የተመለሰ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ የገጠመውን ለሒውማን ራይትስ ዎች ተናግሯል።

ስደተኛው “ጀልባው ችግር ውስጥ ገብቶ ማዕበል ይመታው ነበር። ብዙ ሰው ጭኖ በመጨናነቁ ሊሰምጥ ሲል ደላላው ወደ 25 የሚሆኑትን እያነሳ ወደ ባሕር ወረወራቸው” ብሏል። በዘገባው ቃለ-መመጠይቅ የተደረገላቸው ኢትዮጵያውያን የመን ሲደርሱ ከሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እጅ መውደቃቸውን ገልጸዋል። አምስቱ ስደተኞች ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲያስልኩ ወይም በኢትዮጵያ ወይም በሶማሊያ የሚገኝ አድራሻ እንዲያቀርቡ ለማስገደድ አካላዊ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል።

የሒውማን ራይትስ ዎች ዘገባ «ስደተኞች ተይዘው የሚቆዩባቸው መጠለያዎች በየመናውያን የሚተዳደሩ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ድብደባ ይፈጽማሉ» ይላል። በሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እጅ የሚገኙ ስደተኞችን ለማስለቀቅ ቤተሰቦች የመኖሪያ ቤት እና መሬት መሰል ሐብታቸውን እስከ መሸጥ እንደሚደርሱም ሒውማን ራይትስ ዎች አትቷል። 
የኢትዮጵያ፤ የመን እና ሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት ስደተኞች የሚገጥማቸውን መከራ ለማስቀረት፣ ሕጋዊ የተገን አሰጣጥ ሥርዓት ለማበጀት እና በጸጥታ አስከባሪዎቻቸው የሚፈጸሙ ግፎችን ለመፈተሽ በቂ እርምጃ አልወሰዱም ሲል ሒውማን ራይትስ ዎች ወቅሷል።

Jemen afrikanische Migranten in Harad
ምስል DW/Alsoofi

ሥራ አጥነትና ሌሎች ኤኮኖሚያዊ ፈተናዎች፤ ድርቅ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ባለፉት አስር አመታት ቀይ ባሕርን በጀልባ በማቋረጥ እና በየመን በእግር በመጓዝ ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንዲጓዙ የገፏቸው አበይት ምክንያቶች ናቸው ብሏል።  በሳዑዲ አረቢያ እና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ባለው የሥራ ዕድል ምክንያት በኢትዮጵያውያኑ ተመራጭ ናቸው ያለው ሒውማን ራይትስ ዎች «አብዛኞቹ ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ይጓዛሉ። እዚያም ሲደርሱ ሕጋዊ አይደሉም» ብሏል። 

በሒውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ፌሊክስ ሖርን «በሳዑዲ አረቢያ የተሻለ ሕይወት ተስፋ ያደረጉ በርካታ ኢትዮጵያውያን በባሕር መሞት፤ ስቅየትና ሌሎች ግፎችን ጨምሮ ለመናገር የሚከብዱ አደጋዎች ይገጥሟቸዋል» ሲሉ ተናግረዋል። «የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፍ አጋሮቹ በመተባበር በጀርባቸው ከያዟቸው ልብሶቻቸው በቀር ምንም የሌላቸውና ዕገዛ የሚጠይቁት የሌላቸውን ተመላሾች ሊረዳ ይገባል» ብለዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ