1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ወጣት

ዓርብ፣ ጥር 26 2015

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ውጤቱን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ከአጠቃላይ ተፈታኞች መካከል 3.3% ብቻ ፈተናውን ያለፉ ሲሆን ከፍተኛው ውጤት 666 መሆኑ ተገልጧል። በዛሬው የወጣቶች ዓለም ፕሮግራም የወጣቱን የቀደመ ታሪክ፣ የገጠመውን ውጣውረድና የወደፊት ራዕይ በተመለከተ ወላጆቹንና ተማሪውን ለዶይቸ ቬለ ተናግሯል።

https://p.dw.com/p/4N4w2
Äthiopien Bildungsministerium gibt ESLCE Endergebnis bekannt
ምስል Solomon MUCHIE/DW

ከመላ ሀገሪቱ ከፍተኛ ነጥብ አስመዝግቧል

የ2014 ዓም የ12ኛ ክፍል ፈተና በተለየ መልኩ በዩኒቨርሲቲዎች ተካሂዶ ትምህርት ሚኒስቴር “አስደንጋጭ” ያለው ውጤት ተመዝግቧል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ውጤቱን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ከአጠቃላይ ተፈታኞች መካከል 3.3% ብቻ ፈተናውን ያለፉ ሲሆን ከፍተኛው ውጤት 666 መሆኑ ተገልጧል። በዛሬው የወጣቶች ዓለም ፕሮግራም የወጣቱን የቀደመ ታሪክ፣ የገጠመውን ውጣውረድና የወደፊት ራዕይ በተመለከተ ወላጆቹንና ተማሪውን ለዶይቸ ቬለ ተናግሯል። 

ይህን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ በአማራ ክልል የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነው ሚኪያሰ አዳነ መሆኑን ደግሞ የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር ፍቅር በላይ ለዶይቼ ቬሌ አረጋግጠዋል፣ የኮቪድና የጦርነት ሁኔታዎች ተፅዕኖ ባይፈጥሩበት ኖሮ ከዚህ በላይ ውጤት ሊያስመዘግብ ይችል እንደነበር እንደዚህ ገልፀዋል፡፡ 
“ተማሪ ሚኪያስ በ2014 አገር አቀፍ ፈተና ተፈትኖ በትምህርት ቤታችን በተፈጥሮ ሳይንስ 666 ነው ያስመዘገበው፣ ሁሉም ተማሪዎቻችን የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ናቸው፣ ልጁ እንዲያውም ከዚህ በላይ ነበር የሚጠበቀው፣ ያው በተለያየ ጊዜ ሲገቡም በግማሽ መንፈቀ ትምህርት የገቡት፣ ትምህርት ቤቱ የካቲት 11 ላይ ነበር በመጀመሪያ ጊዜ የተከፈተው፣ በኮሮናም፣ በጦርነቱም ብዙ መቆራረጦች አሉ፣ እነኚያ መቆራረጦች ባይኖሩ ኖሮ ከዚህም በላይ ውጤት ሊያመጣ የሚችልና የሚጠበቅም ነበር፣ እኛ እንዴያውም ከ680 በላይ ያመጣል የሚለውን ነበር ይዘን የነበረው፣ ነገር ግን ይህም ቢሆን አሁን በአገር አቀፍ ደረጃ በተፈጥሮ ሳይንስ አንደኛ የሆነ ውጤት ነው፡፡” 
ተማሪው በተለይ የፊዚክስና የሂሳብ ትምህርቶችን 100፣ 100 ማስመዝገቡ የተማሪውን ጥረት እንደሚያሳይ አመልክተው፣ ትምህርት ቤታቸውም ያስፈተናቸውን 69 ተማሪዎች በሙሉ ማሳለፍ መቻሉን አብራርተዋል፡፡ 
“… ሂሳብም ፊዚክስም ብታየው መቶ፣ መቶ ነው መጣው፣ … የተሸለ የሚባል ተማሪ ነው፣ ሂሳብን ብዙ ተማሪ መቶ ሊያመጣ ይችላል፣ ፊዚክስን ግን መቶ ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ነው፣ በነበረው ቆይታ አጠቃላይ ስነምግባሩ፣ ትምህርት ላይ ያለው ትኩረት፣ ጥሩ የሚባል ነው፣ በአገሪቱ ባለው መረጃ እንደተቋም የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ሰባት ትምህርት ቤቶች ናቸው መቶ በመቶ ተማሪዎቻቸውን ያሳለፉ፣ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ያስፈተናቸውን ተማሪዎች በሙሉ አሳልፏል፣ ይህም ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት 666 የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ነው፡፡” ሲሉ አክለዋል፡፡ 

Äthiopien | Bahir Dar STEM-Inkubationszentrum
ምስል Alemenew Mekonne/DW

666 ውጤት ያሰመዘገበው ተማሪ ሚኪያሰ አዳነ በውጤቱ እርሱም፣ ቤተሰቡም ጎረቤትና ጓደኛ በጣም መደሰታቸውን ጠቁሞ፣ ሆኖም የነበሩ ወቅታዊ ሁኔታዎች በፈጠሩት የጊዜ ጥበት በሁለት መንፈቀ ትምህርት ሊሰጥ የሚገባውን ትምህርት በተጨናነቀ መልኩ በአንድ መንፈቀ ትምህርት መማራቸውን አስታውሷል፡፡ 

“ ታህሳስ ላይ ነበር ትምህርት የጀመርነው፣ በሁለት መንፈቀ ትምህርት መወሰድ የነበረበትን ትምህርት በአንድ መንፈቀ ትምህርት ነበር የተማርነው፣ በጦርነቱ ምክንያት ብዙ ጊዜ አልነበረንም የተጣበበ ጊዜ ነው የነበረው፣ ያንን ጊዜ ተጠቅመን ነው ይህን ህል ውጤት ያስመዘገብነው፡፡ ቤተሰብ ጓደኛ ጎረቤት ባመጣሁት ውጤት በጣም ደስ ብሏቸዋል፡፡” 
የተማሪ ሚኪያስ ወላጅ እናት ወ/ሮ ሙሉወርቅ ደርሶ እጅግ መደሰታቸውን ገልፀው የልጃቸውን ፍፃሜ እንዲያሳምርላቸው ተመኝተዋል፡፡ 

“በጣም ደስ ብሎኛል ሌላ ምን ይሰማል፣ በእርግጥ ጎረቤቶች ልጁን ከዚህ በፊት ስለሚያውቁት ከዚህ በላይም እንዲያመጣ እናውቃለን፣ ያው ወቅቱ የፈጠረው ግርግር ጦርነት ባለበት እንደዚህ ዓይነት ውጤት ማምጣትም ከዚህ በላይ ቢማር ጥሩ ነገር ያመታ ነበር ያው በወቅቱ የተፈጠረው ጦርነትም ተፅዕኖ ስላለው ጎረቤትም ሁሉም ስለሚጠብቅ፣ ደስታ ነው ተሰማን ለአገር የሚጠቅም ልጅ ነው ፍፃሜውን ያሳምርለት ነው የምለው፡፡” ብለዋል እናት፡፡ 

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ደላንታ ወረዳ ወገል ጤና ከተማ የሚገኙት የተማሪ ሚኪያ አባት አቶ አዳነ እውነቱ በልጃቸው የትምህርት ሂደት ላይ መዋዕለ ህፃናት ላይ ሙላቷ የምትባል መምህርት ትምህርት እንዲወድ ተፅዕኖ እንዳሳደሩበት፣ መምህር የሆኑት አባትና የባንክ ሰራተኛ የሆኑት እናት የትምህርት ፍላጎት እንዲኖረው ያደረጉት ጥረትና የልጁ ተሰጥኦ ተዳምሮ ለዚህ ውጤት አድርሶታል ብለዋል፡፡ 

Äthiopien | Bahir Dar STEM-Inkubationszentrum
ምስል Alemenew Mekonne/DW

“ልጁ የትምህርት ፍላጎት እንዲያድርበት መምህር ነኝ ተነሳሽነት እንዲኖረውሆኗል፣ ከዚያም በኋላ ትንሽ ለየት የሚያደርገው ነፃ ሆኖ ነው የሚያነብበው፣ አይጨናነቅም፣ አጋዥ መጽሀፍትን እንገዛለን፣ ገጠር ነው፣ የተሟላ ነገር ብዙ የማይገኝበት ነው፣ በተቻለ መጠን እናቱም ለትምህርት ያለውን ዓላማ በማወቅ፣ ትኩረት ሰጥታ ትከታተለዋለች፣ እኔም እንደ አባትነት፣ እንደመምህርም ትኩረት ሰጥቼ እከታተለዋለሁ፣ ይበልጥ እሱም ባለተሰጥኦ ነው ይህ ተጨምሮ ለዚህ ውጤት በቅቷል” 

በጦርነቱ ወቅት ህይወትን ለማትረፍ ከቦታ ቦታ ሲዟዟሩ ልጃቸው ተስፋ ሳቆርጥ የትምህርት ቁሳቁሶችን ይዞ ይንከራተት ነበር ብለዋል እናት ወ/ሮ ሙሉወርቅ፡፡ 
“… በጦርነቱ ወቀት በመኖርና ባለመኖር መካከል ነበር እኛ አገር ለቅቀን ስንሄድ በዚያ ሰዓት መጽሐፍት ተሸክሞ ነበር የሚዞረው፣ እና መጽሀፍት ተሸክሞ እኖራለሁ የሚል ተስፋ ስለነበረው በየቦታው ስንሄድ መጽሀፍትን ይዞ ነበር የሚዞረው፣ ሌትም ቀንም ትምህርቱን ብቻ ነበር የሚያስበው በዚያ ስቃይ ውስጥ፣ አግዚአብሔር ይመስገን ፍፃሜውን ያሳምርለት፣ ” 

አባት አቶ አዳነም ተጠይቀው በተመሳሳይ ሚኪያስ ትምህርት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ተስፋ ሳይቆርጥ ተሸከሞ ከቦታ ወደ ቦታ ቦታ ሲዘዋወር እንደነበር ነው የሚያስታውሱት፡፡ 
“ … የሚከታተለው በጦርነቱ ጊዜ የያዘውን ማስታወሻ ተሸክም ሌትም ቀንም በእግራችን ስንጓዝ አልጣለውም፣ የሞተ ሰው ታያለህ፣ ተስፋ ቆርጨ መጽሐፍቱን ጣል ብየው ነበር እሱ ግን እስከመጨረሻው ታገለ፣ አገር ሰላም ሆነ ከሄድንበት ተመለስን፣ ዘግይተው ትምህርት ጀመሩ በመሆኑም ጊዜውን ባግባቡ ተጠቅሟል” 
የአጠናን ሁኔታውን፣ የቀደመ የትምህርት ሁኔታውንና የወደፊት ህልሙን በተመለከተም ሚኪያስ አስተያየቱን ሰጥቶናል፡፡ 

Äthiopien Das äthiopische Bildungsministerium hat angekündigt, dass die Schulprüfungen auf Bundesebene stattfinden werden
የትምህርት ሚንስትርፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋምስል Shewangizaw Wegyayehu/DW

“…አብዛኛውን ጊዜ በኦንላይን የሚሰጡ ትምህርቶችን እከታተል ነበር፣ መምህራን በሚገባ እከታተል ነበር፣… ከእኛ ጋ ፈተነው በሰላም ነው የተካሄደው፣ አንዳንድ ተማሪዎች ይታመሙ ነበር የፀጥታ ችግር ግን አልነበረም… ውቴቱን ጠብቄው ስለነበር ብዙም አልተዳናገጥሁ… ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ የደረጃ ተማሪ ነበርኩ ከ1 እስከ 3 እወጣ ነበር፣ 8ኛ ክፍል ላይ 92 ነው ያመጣሁት… ወደፊት አስትሮ ፊዚክስ ሰፔስ ሳይንስ፣ ስለፕላኔቶች ነው ማጥናት የምፈልገው፡፡” 

አቶ አዳነ ምጡቅ አእምሮ ያላቸው አፍሪካውያን ብዙዎቹ ለአገራቸው ኤሆኑም የሚል እምነት አላቸው፣ ልጃቸው በአገር ውስጥ ቢያጠና ፍላጎት እንዳላቸው አመልክተው፣ ሆኖም ፍላጎቱን የመጫን ዝንባሌ እንደሌላቸው ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡ 

“… እንደወላጅ ከእኛ እንዲነጠል አንፈልግም፣ አፍሪካ ብዙ ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች ያሉባት አህጉር ናት አለመታደል ሆኖ ያን እውቀት አገር ውስጥ መጠቀም አልተቻለም፣ እንደእኔ እንደ አባት አገር ውስጥ ቢኖርና ቢማር ባይርቅ እፈልጋለሁ፤ የእሱ አማራጭ ይህን ነው፣ በዚህ እቀጥላለሁ ስላለ፣ የእሱ ፍላጎት እንዲሳካ ነው የምፈልግ፡፡” 
ሚኪያስ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር የሆኑት የአቶ አዳነ እውነቱና የባንክ ሰራተኛ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉወርቅ ደርሶ የመጀመሪያ ልጅ ሲሆን ሌሎች ሁለት ተናናሽ ወንድሞች እንዳሉትም አጫውቶናል፡፡ ኑሯቸውም በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ወገል ጤና በሚባል ከተማ ውስጥ ነው፡፡ 

በ2014 ዓም ለፈተና ከተመዘገቡ 985ሺህ 354 ተማሪዎች መካከል፣ 896 ሺህ 520 ተማሪዎች ተፈትነው 29ሺህ 909 ብቻ ከ50 ከመቶ ማስመዝገባቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አሳውቋል፡፡ 

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ