1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንዳርጋቸዉ እና የብርቱካን አብነት፤ የአንዱዓለም ተስፋ

ሰኞ፣ ግንቦት 20 2010

ደርግን ለመዉጋት ከተደራጁት ቡድናት የተሳካለት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ በምሕፃሩ) በ1983 ደርግን አሸንፎ ሥልጣን ሲይዝ ሌላ ተስፋ ነበር።የሠላም፤ የሕዝብ ነፃነት፤የዴሞክራሲ እና የፍትሕ ሥርፀት ተስፋ ነበር።ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ዛሬ 27ኛ ዓመቱ

https://p.dw.com/p/2yTE7
Berlin Andualem Arage
ምስል DW/Y. Hinz

ቅብብሎሽ

ሕዳር ሁለት ሺሕ አንድ-ቦን።ከጥቂት ወራት በፊት አዲስ የተመሠረተዉ የኢትዮጵያ አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትሕ (አንድነት) ባጭሩ) ሊቀመንበር ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በአዉሮጳ ሐገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት ቀጥለዉ ከጀርመን ወደ ቤልጂግ እየተጓዙ ነበር። ጠየቅኋቸዉ። መለሱ።

ሐምሌ 2002። የቀድሞዉ የግንቦት ሰባት የፍትሕ የነፃነት እና የዴሞክራሲ  ንቅናቄ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አንዳርጋቸዉ ፅጌ ለንደን ብሪታንያ ነበሩ።

ሁለቱም ያሉ-ያሰቡ ያቀዱት እስካሁን በርግጥ አልተሳካም።ሰወስተኛዉ አቶ አንዱዓለም አራጌ ነዉ። የቀድሞዉ የአንድነት ለፍትሕ እና ለዴሞክራሲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አንዱዓለም አራጌ በጀርመን እና በኔዘርላንድስ የሚያደርገዉን ጉብኝት አጠናቅቆ ዛሬ ቀትር ላይ ወደ ፓሪስ-ፈረንሳይ እየተጓዘ ነበር። ተስፋዉ-ይጎመራ ይሆን? የሁለቱ ፖለቲከኞች ምኞት፤ትግል-አብነት፤  አቶ አንዳርጋቸዉ ፅጌ በጣም ቀድመዉ፤ ብርቱካን ሚዴቅሳና እና አንዱዓለም አራጌ ብዙ ዘግይተዉ   ግን ሰወስቱም በየዘመናቸዉ በየወጣትነታቸዉ ፖለቲካዉን የተቀየጡ ናቸዉ። አንዳርጋቸዉ እንደ ወጣት ተማሪ በ1960ዎቹ የተቀየጡት የኢትዮጵያ ፖለቲካ የየዘመኑን ወጣቶች እንዳማለለ ወይም እንዳጠፋ እነሆ አርባኛ ዓመቱን አገባደደ። በ1966 የዓፄ ኃይለስላሴ ሥርዓት ሲገረሰስ የእነ አንዳርጋቸዉ ወጣት ትዉልድ ትግል ዉጤት ተደርጎ ነበር።

Großbritannien - Protest gegen Haft von  Andargachew Tsige
ምስል Imago/ZUMA Press

ደርግን ለመንግሥት-ሥልጣን፤ ሌሎች  የፖለቲካ ኃይላትን ለጠመንጃ ዉጊያ አደራጅቶ ለለዉጥ የታገለ-የጮኸዉን ወጣት የጨረሰ አስተሳሰብ ማስፈኑ እንጂ ቀቢፀ ተስፋዉ። ደርግን ለመዉጋት ከተደራጁት ቡድናት የተሳካለት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ በምሕፃሩ) በ1983 ደርግን አሸንፎ ሥልጣን ሲይዝ ሌላ ተስፋ ነበር። የሠላም፤ የሕዝብ ነፃነት፤የዴሞክራሲ እና የፍትሕ ሥርፀት ተስፋ ነበር። ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ዛሬ 27ኛ ዓመቱ። የብዙ ሺዎች ሕይወት፤ በቢሊዮን የሚገመት ሐብት ንብረት የወደመበት፤ የኤርትራ ግዛት መስዋዕት የተደረገበት ለዉጥ አቶ አንዱዓለም አራጌ እንደሚለዉ ተስፋዉ በተደጋጋሚ ነዉ የተጨናጎለዉ።

በ1997 የተደረገዉ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብን የረጅም ጊዜ የዴሞክራሲ፤ የፍትሕ እና የነፃነት ጥያቄን የሚመልስ ለዉጥ የታየበት፤ የተስፋ ጭላንጭል የፈነጠቀበት መስሎ ነበር ። ግን ያዉ ብልጭ ከማለቱ ድርግም አለ።

የ1997ቱ ምርጫ ዉጤት ሲያወዛግብ አቶ አንዳርጋቸዉ፤ ወይዘሪት ብርቱካን እና አቶ አንዱዓለም ወሕኒ ቤት ተወርዉረዋል።ሰወስቱ በየፊናቸዉ እንዳሉት ከ1997ት በኋላ ያደረጉት ትግል በ1997 ዳግም የተዳፈነዉ ተስፋ እንዲያቀጠቅጥ ለማድረግ ነበር።ሰወስቱም ተራ በተራ ግን በተለያየ ጊዜ እየተለቀሙ መታሰራቸዉ እንጂ ቁጭቱ።

Berlin Andualem Arage
ምስል DW/Y. Hinz

አራት ዓመታት ከማቀቁበት እስርቤት ዛሬ የተፈቱት  የአቶ አንዳርጋቸዉን የወደፊት ዓላማ እና ዕቅድ በርግጥ አናዉቅም። ወይዘሪት ብርቱካን ግን ከእስር ቤት ከተለቀቁ  በኋላ ተሰደዋል። አንዱዓለም ቀረ።ከስድት ዓመት ከመንፈቅ እስራት በኋላ በቅርቡ የተፈታዉ አንዱዓለም ዛሬም ጠንካራ ተስፋ አለዉ።

አንዱዓለም እንደሚለዉ በልጅነቱ የተመኘዉ በወጣትነቱ የተቀየጠዉ፤ሁለቴ ወይም ከስምት ዓመት በላይ ለእስር የዳረገዉ ሰላማዊ ትግል አሁን የለዉጥ ብልጭታ እያሳየ ነዉ።

በአንዱዓለም አገላለፅ ብልጭ ያለዉ ለዉጥ በዋዛ የተገኘ አይደለም።ባለፉት ሰወስት ዓመታት ብቻ ሺዎች ተገድለዉ፤ ብዙ ሺዎች ቆስለዉ፤ መቶ ሺዎች ተሰደዉ፤ ሺዎች ታስረዉለታል።አቶ አንዱ ዓለም አንዱ ነዉ።

አንዱዓለም እንዳለዉ ጠንካራ ፓርቲ ለመመስረት የሚያደርገዉን ጥረት ይቀጥላል። ጀርመንና ኔዘርላንድስ ከሚገኙ የቀድሞ ፓርቲዉ አባላት እና ደጋፊዎች ያገኘዉ ደጋፍም ለወደፊት ዕቅዱ አበረታች ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ