1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቅርሶቻችንን ማስመለስ የሕልዉና ጥያቄ ነዉ

ዓርብ፣ ኅዳር 21 2011

ከአፍሪቃ የተዘረፉት ጥንታዊና ባህላዊ ቅርሶች 90 % የሚገኘዉ በአዉሮጳ ሃገራት ዉስጥ መሆኑ ተመልክቶአል። ፈረንሳይ ከአፍሪቃ የዘረፈችዉን ቅርስ ለመመለስ በምታደርገዉ አዲስ የማሻሻያ ሕግ ረቂቅ ምን ይሆን? የቅርስ እና የታሪክ ምሁራኑ እንተናገሩት «ለረጅም ጊዜ ዉሰት» በሚል ኢትዮጵያ ለተዘረፉት ቅርሶቿ መመለስ ድርድር ዉስጥ አትገባም።   

https://p.dw.com/p/398nJ
Das Victoria und Albert Museum, in dem äthiopische Raubschätze ausgestellt wurden, feiert den äthiopischen Tag
ምስል DW/H.Demissie

ቅርሶቻችንን ማስመለስ የሕልዉና ጥያቄ ነዉ

የአፍሪቃ ሃገራት በቅኝ ግዛት እጅ ስር ከወደቁ ጊዜ ጀምሮ በአዉሮጳ ሃገራት መንግሥታት የተዘረፉ ቅርሶች እንዲመለሱ የአፍሪቃ ሃገራት በመወትወት ላይ ይገኛሉ። የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮ ሃገራቸዉ በቅኝ ግዛት ዘመን በዝርፍያም ሆነ በስጦታ መልክ ወደ ሃገርዋ ቤተ-መዘክሮች የያዘቻቸዉን እንዲሁም በየግለሰቡ ቤት የሚገኘዉን ታሪካዊ የአፍሪቃ ቅርስ ለማስመለስ የሚያስችል የሕግ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችል ዝርዝር ይቀበላሉ ተብሎአል ይጠበቃል። ይህ የፈረንሳይ ርምጃ በቅኝ ተይዘዉ ለነበሩትና ታሪክና ቅርሳቸዉ ለተዘረፉት አፍሪቃ ሃገራት ቅርስ መመለሥ አንድ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ነዉ ሲሉ ታዋቂዉ የሴኔጋል የኤኮኖሚ ባለሞያ ፌልዊን ሳር እና ፈረንሳዊዉ የቅርስ ታሪክ አዋቂ ቤኔዲክት ሳቮይ ገልፀዋል።  የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮ ከቅኝ ግዛት ሃገሮች የተዘረፉ ቅርሶችን ለመመለስ ጥረት የጀመሩ የመጀመርያዉ የአዉሮጳ ሃገር መሪ መሆናቸዉን ተነግሮላቸዋል። ፕሬዚዳንት ማርኮ ለዘመናት በሃገራቸዉ ተይዞ የነበረዉን ቅርስ አሳልፈዉ ለባለቤቱ ለመስጠት የሚያደርጉትን ጥረት አብዛኞች ቢወስዱም፤ የአመላለሱ ሁኔታ እንዴት ይሆን? ብለዉ የሚጠይቁ ጥቂቶች አይደሉም። በአዉሮጳ የሚገኙ በርካታ ቤተ-መዘክሮች በዉሰት መልክ ቅርሶቹ ለተዘረፉበት ሃገር በዉሰት ለመስጠት ቢስማሙም፤ ኢትዮጵያና ግሪክ ግን «ዉሰት» የሚለዉን ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ዉድቅ አድርገዋል። በኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዩናስ ደስታ እንደገለፁትም የተዘረፉ ቅርሶችን ለማስመለስ ሃገራችን ጠንካራ ሕግ አላት ፤ «ዉሰት» የሚባል ነገር አይሰራም ብለዋል።

Das Victoria und Albert Museum, in dem äthiopische Raubschätze ausgestellt wurden, feiert den äthiopischen Tag
ምስል DW/H.Demissie

«ቅርስ የማስመለስ ጉዳይ በሃገራችን ምናልባት ዓለም ላይ ያሉ ሕጎችን ታሳቢ አድርጎ ጠንካራ የሚባል ሕግ ነዉ የወጣዉ። ይህ ሕግ ለማንኛዉም አካል የቅርሶቹ ባለይዞታ ግለሰብም ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የቅርሶቹ ባለይዞታ ሊሆን ይችላል።  ቅርሶቹ የመንግሥት ብቻ አይደሉም። ቅርሶቹንም ከሃገር የማዘዋወር መብትን አይሰጥም። በሁለተኛ ደረጃ ከሃገር የወጡ ቅርሶችን የማስመለስ እንጂ ፤ ከማስመለስ በመለስ ማንኛዉንም አይነት ድርድር ማድረግ እንደማይቻል በሕግ ተዘግቶአል። ማንናዉም ባለስልጣን ወደ ዉጭ የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ ከተያዘዉ ሕግ በመለስ ምንም አይነት ድርድር እንዲያደርግ አይፈቅድም። ቅርስን በማስመለስ ረገድ የአንዳንድ አፍሪቃ ሃገሮችን ሕግ ከአፍሪቃ አንፃር ስናየዉ ልል መሆናቸዉን እናስተዉላለን። በሃገራችን  የምናየዉ ሕግ በዓለም ጠንካራ የሆነ ሕግ ተብሎ የሚጠቀስ ሕግ መጽደቁን ነዉ የምናየዉ።»

ኢትዮጵያ ቅርስን በማስመለስ ረገድ ያላት አቋም ጠንካራ ሆኖ ሳለ እስከዛሬ ለማስመለስ የተቻለዉ በጣት የሚቆጠሩ ቅርሶችን ነዉ ይህ ለምን ይሆን? አቶ ዮናስ ደስታ፤ 

Das Victoria und Albert Museum, in dem äthiopische Raubschätze ausgestellt wurden, feiert den äthiopischen Tag
ምስል DW/H.Demissie

« ይህን ጠንካራ ሕግን ይዘን እስከዛሬ በምንፈልገዉ ሁኔታ ከሃገር የወጡ ቅርሶቻችንን በማስመለሱ ረገድ ለምን ዉጤታማ አልሆነም ለሚለዉ የሃገራችን ተፅኖ ፈጣሪነት ጉዳይ አንዱ ነጥብ ነዉ። ብዙዎቹ ቅርሶቻችን ተዘርፈዉ ባሉበት ሃገራት የርዳታ ገንዘብ የሚሰጡ ፤ እና ጠያቂ እነሱ ደግሞ መላሽ የሆኖበት ሁኔታ ላይ ነዉ ያለነዉ። ቅርሶቹን በማስመለሱ ሂደት ደግሞ ለመመለስ እሺ ባይሉም ፤ እኛ ምን ተጽኖ ልንፈጥር የምንችልበት ሂደት አለ ብለን ስንጠይቅ ድህነታችን በጣም ሲንፀባረቅ እናያለን። በጊዜ ሂደት ሃገራችን በእድገትዋ ትለወጣለች ። በዚህም ቅርሶቻችን በጊዜ ሂደት ትዉልድ ማስመለሱ የማይቀር እዉነታ ነዉ። ከአፍሪቃ የተዘረፉ ታሪካዊ ቅርሶችን በተመለከተ፤ በፕሬዚደንት ማክሮ የቀረበዉ ሪፖርት ፤ በተወሰነ መልኩ ከዚህ ቀደም ከነበራቸዉ በጣም ደረቅና ጠንካራ አቋም በተወሰነ መልኩ እየተለሳለሱ መምጣታቸዉን ያሳያል። የፕሬዚዳንቱን አቋም በበጎ ልናየዉ ብንችልም ፤ ጥንቃቄ መዉሰድ ያለብን ብዙ የመግለጫዉ ወይም «ሪፖርቱ » ዉስጥ የተጠቀሰዉ ቅርሶቹን በዉሰት መልክ ለረጅም ጊዜ መዉሰድ የሚለዉ ነዉ። ግን በኢትዮጵ ሕግ የራሳችንን ቅርስ ልንበደር የምንደራደርበት ቀዳዳ የለም። በሁለተኛ ደረጃ በብድር መልክ ስንወስደዉ ልናስቀምጠዉe የንችለዉንም ጣጣ ማሰቡ መልካም ነዉ። ይህን ስል የራሳችንን ቅርስ ለረጅም ጊዜ ስነዋሰዉ  ባለቤትነቱ የነሱ ነዉ ብለን በተወሰነ መልኩ እየሰጠን መሆኑን መገንዘብ አለብን።»   

በታላቋ  ብሪታንያ መዲና ለንደን በሚገኛው በቪክቶርያ  እና አልበርት ሙዚየም መስከረም 20 ቀን 2011 ዓ.ም  ከቀትር ጀምሮ «ወደ ብርኃን የኢትዮጵያ ባህላዊ ቀን» በሚል መጠሪያ  በሙዚየሙ በቀረበው ዝግጅት መቅደላን ማስታወስ በሚል ዓላማ ከ 2010 ሚያዝያ ወር ጀምሮ ከኢትዮጵያ ከተዘረፉ ታሪካዊ ቅርሶች የተወሰኑትን ለህዝብ ዕይታ ከማቅረብ በተጨማሪ «ወደ ብርኃን የኢትዮጵያ ባህላዊ ቀን»  ሲል ዝግጅት ማድረጉ ቤተ- መዘክሩ ጎብኚዎችን ለማግኛት ያካሄደዉ ዝግጅት ነበር።  ሙዚየሙ  ማለት ቤተ-መዘክሩ ቅርሶቹን ለአውደ  ርዕይ ያበቃቸው የእንግሊዝ ጦር ድልን 150ኛ ዓመት በማስታወስ ነበር። ከጣልያን የአክሱም ሐዉልት መመለሱን ያስታወሱት በኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዩናስ ደስታ አሁንም እጅግ በጣም ብዙ የኢትዮጵያ ድንቅ ቅርሶች የሚገኙት በዉች ሃገራት ነዉ።

«የተዘረፉ ቅርሶችን የማስመለሱ ጉዳይ ለኢትዮጵያዉያን ዉጤታማ የሆኑ ተሞክሮዎችም አሉ ፤ አሁንም ግን ያልተመለሱ እጅግ ብዙ ቅርሶች በዉጭ ሃገራት አሉ። ይህን ለማስመለስ ደግሞ የዜጎችም የመንግሥትም ጥረት እየተደረገባቸዉ ያሉ ጉዳዮች ናቸዉ። ግን እነዚህ ጉዳዮች ፍሪ እንዲያፈሩ የዓለም አቀፍ ተሳትፎ ምን ይመስላል የሚለዉን ጉዳይ ስናጤን ሃገራችን ላይ ቅርስን ለማስመለስ ምንም ያህል የጠነከሩ ሕጎች እና ፍላጎቶች ቢኖሩም ከሃገራችን ድንበር ዉጭ በሌላ ሃገራት ያሉ ቅርሶችን ለማምጣት እና ዉጤት ላይ ለመድረስ በሃገራችን የተደነገጉት ሕጎች ብቻ በቂ አይደሉም። ስለዚህ የዓለም አቀፍ ሕጎችን የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን እንዲሁም በዋናነት ቅርሶቹ ካሉባቸዉ ሃገራት ጋር ያለን የሁለትዮሽ ግንኙነት እና ጫና የማሳደር አቅማችን ናቸዉ ቅርሶቹን የመመለስ ዉጤታማነት የሚወስኑት። እነዚህን ሁሉ ግምት ዉስጥ አስገብተን የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነዉ። በነዚህ ጥረቶች ወደዉጭ ተዘርፈዉ አልያም ተሰርቀዉ ከሄዱት ቅርሶቻችን ቁጥር ጋር ሲነጻፀር በፍፁም ሊያረካን በሚችል ደረጃ ባይሆንም በየዓመቱ በጣት የሚቆጠሩ ቅርሶችን የማስመለስ ሁኔታዎች አሉ።»           

ከኦክስፎርድ ዩንቨርስቲ ጋር በመተባበብር በወጣቶች ላይ ጥናት በማካሄድ ላይ ያለዉን «ያንግ ላይቭስ ፕሮጀክት»የሚመሩት የታዋቂዉ የታሪክ ተመራማሪ የሪቻርድ ፓንክረስት ልጅ አሉላ ፓንክረስት በበኩላቸዉ፤ በታላቅዋ ብሪታንያ ሙዚየም የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ቅርስ እጅግ ብዙ ነዉ። የአዉሮጳ መንግሥታት በቅኝ ግዛት ዘመን ከሌሎች አፍሪቃ ሃገራት የወሰድዋቸዉ ቅርሶች ግን ከኢትዮጵያዉ ሁሉ ሳይበልጥ እንደማይቀር ይገልፃሉ። 

Raubkunst? Die Bronzen aus Benin Ausstellung Hamburg
ምስል Michaela Hille

«የተዘረፉ አልያም ተሰርቀዉ የወጡ የኢትዮጵያ ቅርሶች ከሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ጋር ሲነፃፀር ያን ያህል ላይሆን ይችላል ። ምክንያቱም አንዳንድ የቅኝ ገዢ ሃገሮች  እንጊሊዝም ፈረንሳይም ከሌሎች አፍሪቃ ሃገራት ዝርፍያቸዉ በጣም የላቀ ሊሆን ይችላል። ግን ቢሆንም እንጊሊዞች በመቅደላ አፄ ቴዮድሮስን ለመማረክ ሲሞክሩ እና አፄ ቴዮድሮስ ያሰባሰቡዋቸዉን ቅርሶች ሲወስዱ በጣም በርካታ ቅርሶች ነዉ ወደ እንጊሊዝ ሃገር ተዘፈዉ የተወሰዱት። በተለይ የተለያዩ የቤተ-ክርስትያን መገልገያ እቃዎች የብራና ጽሑፎች መዘረፋቸ ምንም አያጠራጥርም።  እንጊሊዞቹ መቅደላን ካቃጠሉ በኋላ ቅርሶቹን በጨረታ ለወታደሮቹ ሲሸጡ ነበር። አልባሳት፤ ዘዉዶች፤ የብራና ጽሑፎች ፤ ታቦታት የመሳሰሉ ወደ 500 የሚጠጉ የኢትዮጵያ ቅርሶች ተወስደዉ በብሪታንያ ሙዚየሞች ይገኛሉ። ዝርፍያዉ ቀላል አልነበረም። በፋሽስት ወረራም ጊዜ ብዙ ቅርሶች ተወስደዋል። በዚህ ወረራ የተወሰደ ተብሎ በጣም የሚነሳዉ አክሱም ሐዉልት እንዲሁም አንበሳዉ ሐዉልት ቢሆንም ፤ ከነዚህ ቅርሶች ሌላ ብዙ ቅርሶችም ተወስደዋል። ሞሶሎኒ በተማረከበት ወቅት አራት ዘዉዶችን መዉሰዱን በተማረከ ወቅት የተነሳዉ ፎቶግራፍ ላይ ዘዉዶቹ መታየታቸዉ አንዱ ማስረጃ ነዉ።  እነዚህ ዘዉዶች እስካሁን የደረሱበት አይታወቅም። ፈረንሳይም በጎርጎረሳዉያኑ 1932 ብዙ ቅርሶችን ወስዳለች። ስለዚህ በፈረንሳይ፤ በጀርመን፤ በጣልያን ሃገር በተለያየ ጊዜ ከኢትዮጵያ የተወሰዱት ቅርሶች በተለያዩ ቤተ- መዘክሮቻቸዉ ይገኛሉ። እና በአሁኑ ወቅት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት አማኑኤል ማክሮ ከአፍሪቃ ሃገራት የተዘረፉት ቅርሶች ይመለሳሉ በሚል የጀመረዉ እንቅስቃሴ እንደ ፈር ቀዳጅ ርምጃ የሚታይ ነዉ። ፕሬዚዳንቱ ይህን ሃሳብ ሲያቀርቡና በአምስት ዓመት ዉስጥ ተግባራዊ እናደርገዋለን ብለዉ ቃል ሲገቡ ይህን ፈለግ ሌሎች የአዉሮጳ ሃገራት መከተል ይገባቸዋል።  እዚህ ላይ እንጊሊን በምሳሌ ብንወስድ የመቅደላ ጦርነት 150ኛ ዓመት ሲታሰብ በለንደን የሚገኘዉ ቪክቶርያ  እና አልበርት ሙዚየም ከመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶችን ለተመልካች ለእይታ አቅርቦ ነበር። በዚያ ወቅት የሙዚየሙ ዳይሬክተር ቅርሶቹን ለኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ በዉሰት መልክ እንሰጣለን ማለቱ ይታወሳል። ነገር ግን እነዚህ ቅርሶች የኢትዮጵያ ሃብቶች ናቸዉ፤ ብዙዎችቹን ቅርሶች አፄ-ቴዮድሮስ ያሰባሰቡዋቸዉ ናቸዉ። በዚህም ቅርሶቹ በዉሰት ሳይሆን በቋሚ መልክ ለኢትዮጵያ መመለስ ይኖርባቸዋል። ይህ ድርድር የሚጠይቅ ነገር ሳይሆን የመብት ጉዳይ ነዉ። እንጊሊዝ የዘረፈቻቸዉን እነዚህን ቅርሶች ደረጃ በደረጃ ልትመልስ ትችላለች። ወሳኝ የሚባሉት ቅርሶች ለምሳሌ የሐይማኖት ነክ ቁሳቁሶች በመጀመርያ ሊመለሱ ይችላሉ። በመቀጠል ቀስ በቀስ የነገስታቱ አልባሳት እና ዘዉዶች በሁለተኛ ደረጃ ሊመለሱ ይችላሉ። ይህ የሕልዉና እና የባለቤትነት ጉዳይ ነዉ።»          

Das Victoria und Albert Museum, in dem äthiopische Raubschätze ausgestellt wurden, feiert den äthiopischen Tag
ምስል DW/H.Demissie

በመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶቻችንን ያስታወሱት በኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዩናስ ደስታ ቅርሶች ከሃገር እንዳይወጡ ቁጥጥር ቡደረግም አሁን ቅርሶች ተሰርቀዉ ሾልከዉ የሚወጡበት አጋጣሚ አለ።

የአፍሪቃን ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶች የዘረፉት የአዉሮጳ ሃገራት ቅርሶቹ በጥንቃቄ ላይያዙ ይችላሉ በሚል መልሰዉ ዘራፊዎቹ አዉሮጳዉያኑ ሃገራት ላለማስረከብ የሚያነሱት መከራከርያ ነጥብ መሆኑን አቶ ዩናስ አክለዋል።

Das Victoria und Albert Museum, in dem äthiopische Raubschätze ausgestellt wurden, feiert den äthiopischen Tag
ምስል DW/H.Demissie

«ቅርሶቻችንን የማስመለስ ጉዳይ የህልዉና ጉዳይ ነዉ ያሉት ተባባሪ ፕሮፊሰር አሉላ ፓንክረስት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት አማኑኤል ማክሮ ፈርቀዳጅ ሥራን ይዘን ሌሎችም የአዉሮጳ ሃገራት እዚህ ዉሳኔ ላይ እንዲመጡ የመወትወቻ ጊዜ አሁን ነዉ ብለዋል። »

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት አማኑኤል ማክሮ ከአፍሪቃዉያን ሃገራት የተዘረፉትን ቅርሶች ለመመለስ አልያም በዉሰት ለረጅም ጊዜ የመስጠት እንቅስቃሴ በአምስት ዓመት ዉስጥ ተግባራዊ እንደሚደረግ መናገራቸዉ ተዘግቦአል። ከአፍሪቃ የተዘረፉት ጥንታዊና ባህላዊ ቅርሶች 90 % የሚገኘዉ በአዉሮጳ ሃገራት ዉስጥ መሆኑ ተመልክቶአል። ፈረንሳይ ከአፍሪቃ የዘረፈችዉን ቅርስ ለመመለስ በምታደርገዉ አዲስ የማሻሻያ ሕግ ረቂቅ ምን ይሆን? የቅርስ እና የታሪክ ምሁራኑ እንተናገሩት «ለረጅም ጊዜ ዉሰጥ» በሚል ኢትዮጵያ ለተዘረፉት ቅርሶቿ መመለስ ምንም አይነት ድርድር አትገባም።   

ሙሉ ጥንቅሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።      

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ