1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ታኅሣስ 13 ቀን፣ 2012 ዓ.ም

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 13 2012

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቸልሲ ከቶትንሀም ሆትስፐር ጋር ባደረገው ድንቅ ጨዋታ ለድል በቅቷል። በእለቱ የዘረኝነት ስድብ ከደጋፊዎች በመሰማቱ ጨዋታው ለጥቂት ጊዜ ተቋርጦ ነበር። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን ሲያንሰራራ ቦሩስያ ዶርትሙንድ መዋዠቅ ታይቶበታል። የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ንጉሥ በተሰኘ በመንፈቁ ሊቨርፑል የዓለም ዋንጫን አንስቷል።

https://p.dw.com/p/3VHBB
Fußball UK Burnley vs. Manchester City
ምስል Getty Images/A. Livesey

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቸልሲ ከቶትንሀም ሆትስፐር ጋር ባደረገው ድንቅ ጨዋታ ለድል በቅቷል። በእለቱ የዘረኝነት ስድብ ከደጋፊዎች በመሰማቱ ጨዋታው ለጥቂት ጊዜ ተቋርጦ ነበር። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ባየር ሙይንሽን ዳግም ሲያንሰራራ ቦሩስያ ዶርትሙንድ መዋዠቅ ታይቶበታል። የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ንጉሥ በተሰኘ በመንፈቁ ሊቨርፑል የዓለም ዋንጫን አንስቷል።

ፕሬሚየ ርሊግ

ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ በእርግጥም ቃላቸውን ጠብቀዋል የዛሬ አምስት ዓመት ግድም ዓመት ሊቨርፑልን ሲረከቡ ጥቂት ዓመታትን ጠብቁኝ አሉ፤ ቡድኑን ወደ ቀድሞ አቋሙ ለመመለስ። ወደ ቀድሞ አቋሙ መመለስ ብቻም አይደል በዓለማችን የእግር ኳስ ቡድኖች የሚመኙትን የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ዋንጫ ሊቨርፑል እንዲጨብጥ አድርገው ደጋፊዎቹን አስፈንድቀዋል።

ይኸው ከስድስት ወራት በኋላ ደግሞ ዳግም ሌላ ዋንጫን በእጃቸው አድርገዋል። ኳታር መዲና ዶሃ ውስጥ በተከናወነው የዓለም ቡድኖች የእግር ኳስ የፍጻሜ ግጥሚያ ፍላሚንጎ ሪዮ ዴ ጄኔሮን 1 ለ0 ድል አድርገው ለቡድናቸው ሌላ ዋንጫ አስገብተዋል። 90 ደቂቃው ተጠናቆ በተጨመረው 9ኛ ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ በብራዚሏ ከተማ ሪዮ ዴ ጄኔሮ ስም የተሰየመው ቡድን ላይ ያስቆጠረው ብራዚሊያዊው ሮቤርቶ ፊርሚኖ ነው። የዓለም የእግር ኳስ ቡድኖች ዋንጫን ሊቨርፑል ሲያሸንፍም በታሪኩ የመጀመሪያው ነው።

Club World Cup - Final - Liverpool v Flamengo | Pokalsieger
ምስል Reuters/K. Pfaffenbach

ያም ብቻም አይደለም በፕሬሚየር ሊጉ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሊቨርፑል ከተከታዩ ላይስተር ሲቲ በሙሉ ዐሥር ነጥብ ልቆ ከላይ ጉብ ብሏል። 16ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ዌስትሀም ዩናይትድ ጋር የሚያደርገውን ተስተካካይ ጨዋታ ካሸነፈ ሊቨርፑል ነጥቡን 52 አድርሶ የዋንጫ ዕድሉን ያሰፋል ማለት ነው። በዚሁ ከቀጠለም ሊቨርፑል ከ30 ዓመታት ወዲህ የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን ይወስዳል። ዘንድሮ በሻምፒዮንስ ሊጉም ሊቨርፑል ዋንጫውን ለማንሳት እድሉ ካላቸው ቡድኖች በቀዳሚነት ይሰለፋል።

ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ የገና ሰሞንን በድርብርብ ድል እና ፌሽታ ሲያሳልፉ፤ የሀገራቸው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ እና የቸልሲ ተከላካይ አንድ ተጨዋች ግን በቅሬታ መዋጡ አልቀረም። የጀርመን ተከላካዩ አንቶኒዮ ሩዲገር ትናንት ቡድኑ ቸልሲ ቶትንሀም ሆትስፐርን 2 ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ ከቶትንሃም ደጋፊዎች የዘረኝነት ስድብ ደርሶበታል። ስታዲየም ውስጥ የታደሙ የቶትንሃም በርካታ ደጋፊዎች አንቶኒዮ ሩዲገር ላይ እንደ ዝንጀሮ ድምጽ በማውጣት በዘረኝነት ሰድበውታል፤ ጨዋታውም ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጧል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ደቡብ ኮሪያዊው ሶን ሆይንግ ሚን የማይገባ ጥፋት ፈጽሞ በቀይ ካርድ ከሜዳ መሰናበቱ ነው። ነገሩ የኾነው እንዲህ ነው።

ሶን በ61ኛው ደቂቃ ከሩዲገር ጋር ይጋጭና ሜዳው ላይ ይወድቃል። እናም በጀርባው መሬት ላይ እንዳለ ተንጠራርቶ ኹለት እግሮቹን ከፍ በማድረግ በታኬታው መርገጫ የሩዲገር ጎንን ነካ ያደርጋል። አንቶኒ ሩዲገር አጋጣሚውን በመጠቀም መሬት ላይ ዘሎ በመውደቅ ይንከባለላል። ጨዋታው ይቋረጥና ዳኛው የቪዲዮ ምስል ርዳትን በመታገዝ ውሳኔ ይዘው ይመለሳሉ። በዚያም ሶን ጥፋተኛ ኾኖ በመገኘቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ይሰናበታል። ሶን ዘንድሮ ከሜዳ በቀይ ሲሰናበት ለሦስተኛ ጊዜው ነው።

እናም ደጋፊዎች ከዚያን በኋላ አንቶኒ ሩዲገርን መተነኳኮስ እና በዘረኝነት ስድብ መዝለፍ ይጀምራሉ። አንቶኒ ሩዲገር ለቡድኑ አምበል በመንገር ቅሬታው ዳኛው ጋር በመድረሱም ጨዋታው ይቋረጥ እና በስታዲየሙ ውስጥ ድምጽ ማጉያ ዘረኝነትን የሚቃወም ማስታወቂያ ይተላለፋል። በፊፋ አዲስ ሕግ መሠረት ስታዲየም ውስጥ ለሦስት ጊዜያት ዘረኝነትን የሚቃወም ማስታወቂያ እንዲነገር ይላል። በመጀመሪያው ጨዋታው ይቋረጥና በማስጠንቀቂያ ይጀምራል። በኹለተኛው ተጨዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ ይደረጋል። በሦስተኛው ማስጠንቀቂያ የዘረኝነት ዘለፋው የማይቋረጥ ከኾነ ጨዋታው ይሰረዛል። በትናንቱ አሳፋሪ የዘረኝነት ድርጊት የአሸናፊው ቡድን ቸልሲው አሰልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድ እፍረት እንደተሰማው አልሸሸገም። የቶትንሃም አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ የዘረኝነት ድርጊቱን ዳኛው አጠገባቸው መጥቶ እስኪናገራቸው ድረስ እንዳላወቁ፤ ጨዋታው በመቋረጡ ቅሬታ ተሰምቷቸው እንደነበር ተናግረዋል።

International Champions Cup: FC Arsenal - FC Chelsea | Antonio Rüdiger
ምስል picture-alliance/dpa/PA wire/N. Carson

በሌላ የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ፦ ማንቸስተር ሲቲ ላይስተር ሲቲን 3 ለ1 ድል አድርጎ ወደ ሊቨርፑል የነበረውን ግስጋሴ ገትቶበታል። ከተቀናቃኙ ጋር የነበረውን ነጥብ ግን ወደ አንድ ዝቅ አድርጓል። ላይስተር ሲቲ 39 ነጥብ አለው። ቶትንሀምን ያሸነፈው ቸልሲ ነጥቡን 32 አድርሶ ደረጃውን ወደ አራት ከፍ አድርጓል።

ትናንት ማንቸስተር ዩናይትድ ከታች ባደገው ዋትፎርድ ቡድን 2 ለ0 መሸነፉ ደጋፊዎቹን አሳዝኗል። 12 ነጥብ ብቻ ያለው ዋትፎርድ ከምድቡ መጨረሻ 20ኛ ላይ ነው የሚገኘው። ቅዳሜ ዕለት ከኤቨርተን ጋር ያለምንም ግብ የተለያየው አርሰናል 23 ነጥብ ይዞ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  ኤቨርተን እና አርሰናል አዲስ አሰልጣኞች ቀጥረዋል።

አርሰናል ሚኬል አርቴታን አዲሱ አሰልጣኙ አድርጎ በተሰማበት ጊዜ ጋቦናዊው አጥቂ ፒየር ኤመሪክ አውባማያንግ አርሰናልን ጥሎ ሊሄድ እንደኾነ እየተነገረ ነው።  ኤቨርተን ደግሞ ካርሎ አንቼሎቲን ወደ ሜርሲ ሳይድ ቡድን ኤቨርተን ጠርቷል። አንቼሎቲ ቀደም ሲል የቸልሲ እንዲሁም ወደ ኤቨርተን ከመምጣታቸው በፊት የጣሊያኑ ናፖሊ አሰልጣኝ ነበሩ።

ቸልሲ በኤደን ሐዛርድ ቦታ ለመተካት የቦሩስያ ዶርትሙንዱ የክንፍ ተጨዋች ጃዶን ሳንቾን በ140 ሚሊዮን ዩሮ ሊያስመጣ እንደኾነ ተነግሯል። እንደ ዘ ሰን ጋዜጣ ዘገባ ወደ ሪያል ማድሪድ ባቀናው ኤደን ሐዛርድ ቦታ የሳንቾ መምጣት ወሳኝ መኾኑን የቸልሲ አሰልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድ ገልጧል። እንግሊዛዊው የ19 ዓመት ወጣት ተጨዋችን ሊቨርፑልን ጨምሮ ብዙ ቡድኖች ዐይናቸውን ጥለውበታል።

ቡንደስሊጋ

በጎርጎሪዮሱ የቀን ቀመር ለሚያሰሉ አዲስ ዓመት እና የገና በአል ከመግባቱ በፊት የመጨረሻው ሳምንት ውድድሮች ተከናውነዋል። ከዚህ በኋላ የቡንደስሊጋው ጨዋታዎች እስከ ጥር 8 ድረስ አይኖርም፤ ለ25 ቀን ግድም ረፍት ነው።

ቡንደስሊጋው አሁን በ17ኛ ዙር ግሚያ ውጤት መሠረት መጀመሪያ በ6ኛው እና በ7ኛው ዙር አካባቢ እንደነበረው ቡድኖች ዳግም በነጥብ እጅግ ተቀራርበዋል። በቡንደስሊጋው ላይፕሲሽ በ37 ነጥብ ይመራል። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በ35 ነጥብ ይከተካል። ባየር ሙይንሽን በበኩሉ በተከታታይ ማሸነፍ በመቻሉ 33 ነጥብ ሰብስቦ ከታች ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል ዶርትሙንድን በ3 ነጥብ ይበልጠዋል። 30 ነጥብ ያለው ሻልከ በቦሩስያ ዶርትሙንድ በግብ ክፍያ ብቻ ተበልጦ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ዶርትሙንድ በሆፈንሃይም የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። ባየር ሙይንሽን ቮልፍስቡርግን 2 ለ0 ረትቷል። ላይፕሲሽ አወስቡርግን 3 ለ1 አሸንፏል።

ባለፈው ሳምንት ከላይፕሲሽ ጋር 3 እኩል የወጣው ዶርትሙንድ በሂፈንሃይም መሸነፉ አስደንቋል። ጨዋትውን ተቆጣጥረው የነበሩት ዶርትሙንዶች በስተመጨረሻ መፍዘዛቸው ጉድ አድርጓቸዋል። በ87ኛው ደቂቃ ላይ ክሮሺያዊው አንድሬ ክራማሪች ከአዳምያን የተሻገረለትን ኳስ በጭንቅላት ገጭቶ ከመረብ አሳርፏል። አቻ የምታደርገውን ግብ በ79ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው አዳማያን ነበር። ማሪዮ ጎይትሰ ለዶርትሙንድ ብቸኝዋን ግብ 17ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጣሯል። የዶርትሙንድ አምበል ሮይስ በጡንቻ መበለዝ ጉዳት አልተሰለፈም። በሱ ምትክ ጎይትሰ ተሰልፏል።

Fußball Bundesliga - Borussia Dortmund v RB Leipzig Fans
ምስል Reuters/L. Kuegeler

ሆፈንሃይም 27 ነጥብ ይዞ ከሌቨርኩሰን ቀጥሎ 7ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። ሌቨርኩሰን በ28 ነጥብ 6ኛ፤ እንዲሁም ሻልከ በ30 ነጥብ አምስተኝ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዶርትሙንድ ከሻልከ የሚበልጠው በግብ ክፍያ ብቻ ነው።

ቮልፍስቡርግን 2 ለ0 የረታው ባየር ሙይንሽን በጨዋታው 70 በመቶ ብልጫ ነበረው። 83ኛ ደቂቃ ላይ በኮቲንሆ ተቀይሮ የገባው ዚርካዚ 85ኛ ደቂቃ ላይ የመጀመሪያዋን ግብ አስቆጥሯል። ኹለተኛዋን ደግሞ ግናብሬ በ89ኝ ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፏል። ቀጣዩ ጨዋታ እሁድ ጃንዋሪ 19 ከሔርታ ቤርሊን ጋር ይኾናል።

የባየር ሙይንሽኑ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ «ቢያንስ» የዘንድሮው የቡንደስሊጋ የጨዋታ ክፍለጊዜ እስኪጠናቀቅ ድረስ ዋና አሰልጣኝ ኾነው እንደሚዘልቁ ባየርሙይንሽን ይፋ አድርጓል።

ኅዳር ወር ላይ የቀድሞው አሰልጣኝ ኒኮ ኮቫች ከተሰናበቱ ወዲህ የ54 ዓመቱ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ጥሩ የሚባሉ ውጤቶችን አስመዝግበዋል። በሻምፒዮንስ ሊግ፦ ኦሊምፒያኮስ ፒሮይስን 2 ለ0፤ እንዲሁም በቡንደስሉጋው ዋና ተፎካካሪያቸው ቢሩስያ ቾርትሙንድን 4 ለ0 ደል ያደረጉበት ጨዋታ በዋናነት ይጠቀስላቸዋል።

እስከ ሰኔ መጨረሻ 2013 ለረዳት አሰልጣኝነት ውል ፈርመው የነበረው ዲተር እሁድ ዕለት ይፋ በኾነው መረጃ መሰረት ዘንድሮ እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ ዋና አሰልጣኝ ናቸው ተብሏል። ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ኾነው 10 ጨዋታዎችን አከናውነዋል። ከነዚህም መካከል በቡንደስሊጋው አምስት ጊዜ እሸንፈው፤ ኹለቴ ሽንፈት ገሟቸዋል። 21 ኳሶችን ከመረብ አሳርፈዋል፤ ስድስት ግብ አስተናግደዋል።

Bundesliga Borussia Mönchengladbach gegen Bayern München
ምስል Imago/J. Huebner

በሻምፒዮንስ ሊግ ሦስት ጨዋታዎችን አከናውነው በኹሉም አሸንፈዋል። ቡድናቸው ባየር ሙይንሽን 11 ግብ አስቆጥሮ 1 ብቻ ተቆጥሮበታል። ከመሪው ላይፕሲሽም በ4 ነጥብ ብቻ ተራርቀዋል።

እሳቸው ቡድኑን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ የተከላከይ መስመሩ የነበረው ድክመት ተወግዶ መረጋጋት የታይበታል። ሲያጠቁ በኅብረት ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ቀና ባሕሪያቸው በቡድኑ ውስጥ ጥምረትን ፈጥሯል፤ ያም እጅግ ተወዶላቸዋል። በተረጋጋ አንደበታቸውም «ባየርሙይንሽን በዋና አሰልጣኝነቱም አመኔታውን በስጦታ ስለሰጠኝ አመሰግናለሁ» ብለዋል። ያው ሰሞኑን የገና ስጦታ የሚሰጥበት ጊዜ በመኾኑ ነው ስጦታ ሲሉ በንግግራቸው ያያዙት።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ውድድር ኢትዮጵያ ቡና አዲስ አበባ ውስጥ ሀዋሳ ከተማን 4 ለ1 አሸንፏል። በውድድሩ ወቅት የኦንላይን ቲኬት መሸጫ እንከን በመፈጠሩ ትኬት ያልገዙ ደጋፊዎች በነጻ እንዲገቡ መደረጉም ተዘግቧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ