1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ሰኔ  24 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ ሰኔ 24 2011

በዓለም የሴቶች እግር ኳስ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በሩብ ፍጻሜው ከውድድሩ ተሰናብቷል። እድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች የኾኑ ተጨዋቾች በሚሳተፉበት ፍልሚያም ጀርመን ትናንት ለጥቂት ዋንጫ አጥታለች። የአፍሪቃ የእግር ኳስ ዋንጫ የምድብ ግጥሚያ እንደቀጠለ ነው። በዳያመንድ ሊግ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት ውጤት አስመዝግበዋል።

https://p.dw.com/p/3LQ00
UEFA U-21-Europameisterschaft Finale | Spanien vs. Deutschland | Niederlage
ምስል picture-alliance/dpa/C. De Luca

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የዓለም የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያ

በዓለም የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫን ፍጻሜ አሸናፊ ሊኾኑ ይችላሉ ተብለው ከተጠበቁ ቡድኖች መካከል አንዱ የኾነው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በሩብ ፍጻሜው ከውድድሩ ተሰናብቷል። እድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች የኾኑ ተጨዋቾች በሚሳተፉበት ፍልሚያም ጀርመን ትናንት ለጥቂት ዋንጫ አጥታለች። የአፍሪቃ የእግር ኳስ ዋንጫ የምድብ ግጥሚያ እንደቀጠለ ነው። በዳያመንድ ሊግ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት ውጤት አስመዝግበዋል። የተጨዋቾች ዝውውር በተጧጧፈበት በአሁኑ ወቅት የክፍያ ክብረ-ወሰንን የሚሰብር ዜና ተሰምቷል። ክፍያው እውን ከኾነ ፓሪስ ሳን ጄርሜን ኪሊያን ምባፔን ወደ ማድሪድ ለማዞር 230 ሚሊዮን ዩሮ  አዘጋጅቷል።

በእግር ኳስ ዓለም ኃያል ኾኖ እስከ ወዲያኛው በብቸኝነት መዝለቅ እንደማይቻል አስመስክሯል የትናንቱ ግጥሚያ። የዛሬ ሁለት ዓመት ድሉ የጀርመን ነበር። ስፔኖች ቀን ጠብቀው ትናንት ተበቅለዋል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2017 ጀርመን ስፔንን በፍጻሜው የረታችው 1 ለ0 ነበር። ዕድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች የእግር ኳስ ተጨዋቾች በሚሳተፉበት የአውሮጳ ግጥሚያ ስፔን ዘንድሮ የጀርመን ቡድንን 2 ለ 1 አሸንፎ በተራው ዋንጫ በማንሳት ከአገጩ ቀና ብሎ ተኩራርቷል። የሚቀጥለው ውጤት ምን ይዞ እንደሚመጣ ባይታወቅም ማለት ነው።  

FIFA Frauen-WM 2019 | Deutschland vs. Schweden | Dzsenifer Marozsan
የዓለም የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ​​​​​​​ ግጥሚያ፤ የጀርመን ብሔራዊ ቡድንምስል Imago Images/Bildbyran

ሐሙስ ዕለት ቦሎኛ ውስጥ፦ በግማሽ ፍጻሜው፦ ጀርመን ሩማንያን 4 ለ2 ስፔን ፍረንሳይን 4 ለ1 አሸንፈው ነበር ለዋንጫ ፍጻሜው የደረሱት። የአየር ሙቀቱ 38 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እና ከዚያ በላይ እየኾነ ቢያስጨንቅም ጨዋታዎቹን ለመታደም ግን በርካታ ሰዎች ስታዲየም ተገኝተዋል።

ከ21 ዓመት በታች የአውሮጳ እግር ኳስ ግጥሚያ

የጀርመን ከ21 ዓመት በታች ብሔራዊ የግር ኳስ ቡድን ከ2009 እና ከ2017 ወዲህ ለዋንጫ ሲደርስ ትናንት ለሦስተኝ ጊዜ ነበር። እንደብዙዎች ምኞት እና ተስፋ ግን እንደለመደው ማሸነፍ አልተሳካለትም። «ደስ የሚለው ነገር ሜሲ እንኳን ቢሰለፍ ቡድናችን ስፔንን እንደሚያሸንፍ ዐሳይቷል» በማለት ነበር የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዪርገን ክሎፕ በሀገራቸው ቡድን እምነት ጥለው የነበሩት። «ለጀርመን ቡድን ከምንም በላይ ወሳኙ ከልብ መጫወት ነው» ሲሉም አክለው ነበር አሁን የበጋ ረፍት ላየ ያሉት ዬርገን ክሎፕ ከፍጻሜው ጨዋታ በፊት በሰጡት አስተያየት። በእርግጥ የጀርመን ቡድን ከልቡ ተጫውቷል ማለት ይቻላል። 

UEFA U-21-Europameisterschaft Finale | Spanien vs. Deutschland | 1. TOR Spanien
ከ21 ዓመት በታች የአውሮጳ እግር ኳስ ግጥሚያ፤ የዋንጫው ባለድል ስፔንምስል Reuters/A. Lingria

ስፔኖች እንደ ሁልጊዜው በመሀል ጨዋታቸው ተመስርተው ወደ ሜዳ በመግባት ልቀው ተገኝተዋል። ከመሀል በአግድሞሽ የሚላኩ ኳሶችን በመጠቀምም ስኬታማ ኾነዋል። አሌክሳንደር ኑቤልን የሚያህል ተስፋ የሚጣልበት ግብ ጠባቂ በሠራው ስህተት ደግሞ ሁለተኛዋን ግብ አስቆጥረው የጀርመኖችን ተስፋ ውኃ ቸልሰውበታል። ግብ ጠባቂው በርካታ ተከላካዮች በአቅራቢያው ባሉበት የተመታበትን ኳስ አጥብቆ ባለመያዙ ተጨናግፋ ስትመለስ የመረብ ሲሳይ ከመኾን አልተረፈችም። በርካቶችን ያሳዘነ አሌክሳንደርን ከጨዋታው በኋላ በእንባ ያሳጠበ ክስተት።

በዕለቱ ኡዲኔ ስታዲዮ ፍሪውሊ ስታዲየም ውስጥ የፍጻሜ ጨዋታውን ለመመልከት የተጓዙ በርካታ ደጋፊዎች ከጀርመን ወደ ጣሊያን አቅንተው ነበር። ስፔን ጀርመንን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ በእንባ ተውጠው ከመመልከት ውጪ ግን አልተረፉም። ስፔኖች በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ተሽለው ተገኝተዋል። የጀርመን ቡድን አስልጣኝ ሽቴፋን ኩንት፦ «የመጀመሪያው አጋማሽ ስፔኖች የተሻሉ ነበሩ ማለቱ ተገቢ ነው» ብለዋል ከጨዋታው በኋላ ስታዲየም ውስጥ ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ። የጀርመን ቡድን ባለፉት ጨዋታዎች ያሳየው ብቃትን አድንቀውም ለተጨዋቶቹ፦ «ባርኔጣዪን አነሳላቸዋለሁ፤ እንደአሰልጣኝ ክብር ይሰማኛል» ብለዋል። ዛሬ ጠዋት ቡድኑ ጀርመን ገብቶ ማታ ተጨዋቾች ወደ የቤታቸው እንደሚሄዱ፤ የፈለጉ የበጋ ረፍታቸውን እንደሚወስዱ ብሎም ያሻቸውን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።  

UEFA U-21-Europameisterschaft Finale | Spanien vs. Deutschland | Niederlage
ከ21 ዓመት በታች የአውሮጳ እግር ኳስ ግጥሚያ፤ በስፔን የተሸነፈው የጀርመን ብሔራዊ ቡድንምስል picture-alliance/GES/M. Ciambelli

ጀርመን እና ስፔን ባለፉት 6 ግጥሚያዎች ተገናኝተው፦ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥተዋል፤ አንድ እኩልና ያለምንም ግብ። ሁለቱም አንድ አንድ ጊዜ 1ለ0 ተሸናንፈዋል። ጀርመን በ2017 ስፔንን በፍጻሜው 1 ለ0 ነበር የረታችው፤ በ2013 ስፔን ጀርመንን 1 ለ0 ረትታለች። ከሁለት ዓመት በኋላ ሁለቱ ቡድኖች ትናንት ለፍጻሜው ዳግም ተገናኝተው ድሉ የስፔን ኾኗል።

ዕድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች የእግር ኳስ ተጨዋቾች በሚሳተፉበት የአውሮጳ 21 ግጥሚያዎች 78 ግቦች ተቆጥረው ክብርወሰን ተብሎ ተመዝግቧል።

የዓለም የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ላይ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎባቸው ከነበሩ ቡድኖች መካከል አንዱ የኾነው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በሩብ ፍጻሜው መሰናበቱ ደጋፊዎቹን አሳዝኗል። አዘጋጇ ፈረንሳይም ከውድድሩ የተሰናበተችው ከጀርመን አንድ ቀን ቀደም ብላ ነበር።

የአፍሪቃ የእግር ኳስ ዋንጫ

Africa Cup 2019 | Nigeria v Guinea
የአፍሪቃ የእግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያ፤ ግብጽምስል picturealliance/empics/M. Ntombela

በአፍሪቃ ዋንጫ የምድብ ግጥሚያዎች ትናንት ግብጽ ኡጋንዳን 2 ለ0 አሸንፋለች። የመጀመሪያዋን ግብ በ36ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው የሊቨርፑሉ ኮከብ አጥቂ ሞሐመድ ሣላኅ ነው። ሁለተኛ ግብ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመረው አንድ ደቂቃ ላይ በአህመድ ኤልሞሐማዲ ተቆጥሯል። የዚምባብዌ ብሔራዊ ቡድን በትናንትናው ግጥሚያ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ቡድን የ4 ለ0 ብርቱ ቅጣት ደርሶበታል። የምድብ ውድድሮቹ ቀጥለው ዛሬ ምሽት፦ደቡብ አፍሪቃ ከሞሮኮ፤ ናሚቢያ ከአይቮሪኮስት ጋር ይጋጠማሉ። ታንዛኒያ ከአልጄሪያ እንዲሁም ጎረቤት ሀገር ኬንያ ከምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሴኔጋል ጋር የሚፋለሙት ዛሬ ምሽት ነው። ነገ ከሚከናወኑ አራት ግጥሚያዎች በኋላ የሩብ ፍጻሜ አላፊዎች በአጠቃላይ ይታወቃሉ። እስካሁን ግብጽ፣ ናይጀሪያ፣ አልጀሪያ፤ ኡጋንዳ እና ማዳጋስካር ወደ ሩብ ፍጻሜው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ ተፋላሚዎቻቸውን ይጠብቃሉ።

አትሌቲክስ

ዩናይትድ ስቴትስ ዩጂን ስታንፎርድ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የዳያመንድ ሊግ አትሌቲክስ ፉክክር በ3 ሺህ ሜርት ሩጫ ትውልደ-ኢትዮጵያዊት ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሐሰን አሸናፊ ኾናለች። ሲፋን ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 8:18.49 ነው። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ጀርመናዊቷ አትሌት ኮንስታንስ ክሎተርሃልፈንን ተከትላ ሦስተኛ ወጥታለች። የገባችበት የ8:20.27 ሰከንድ የራሷን ሰአት ያሻሻለችበት ሲኾን፤ ሁለተኛ ከወጣችው ጀርመናዊት የተቀደመችው በ20 ማይክሮ ሰከንድ ብቻ ነው።  በትናንቱ የዳያመንድ ሊግ ፉክክር  ገንዘቤ ዲባባ አራተኛ፣ ፋንቱ ወርቁ ዘጠነኛ፤ ሰንበሬ ተፈሪ ዐሥራ አንደኛ፤ ሐዊ ፈይሳ ዐሥራ ሦስተኛ እንዲሁም አልማዝ አያና 18ኛ ወጥተዋል። የኤርትራ አትሌቷ ወይኒ ፍሬዝጊ ዐሥራ ሰባተኛ ደረጃን አግኝታለች።

Diamond-League-Meeting in Stanford
ጀርመናዊቷ አትሌት ኮንስታንስ ክሎተርሃልፈን፤ በዳያመንድ ሊግ 3000 ሜትር ሁለተኛ ወጥታምስል picture-alliance/dpa/G. Glendinning

በ1500 ሜትር ፉክክር ጉዳፍ ጸጋዬ አራተኛ፤ ለምለም ኃይሉ ዘጠነኛ እንዲሁም አኲሱማዪት እምባዬ ዐሥራ ሦስተኛ ደረጃን አግኝተዋል። በውድድሩ ኬንያዊቷ ፋይዝ ቼፕንጌቲች ነው ያሸነፈችው። ሐብታም ዓለሙ በ800 ሜትር ሩጫ የአምስተኛ ደረጃን አግኝታለች። በወንዶች የ2 ማይል ፉክክር ሰለሞን ባረጋ 200 ሜትር ሲቀረው በኡጋንዳው አትሌት ጆሹዋ ኪፕሩይ ቼፕቴጋይ እና የዩናይትድ ስቴትሱ ፖል ኪፕኬሞይ ለጥቂት ተቀድሞ ሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል። ቀጣይ የዳያመንድ ሊግ ውድድር ከአራት ቀናት በኋላ ላውዛኔ ውስጥ ይከናወናል።

የተጨዋቾች ዝውውር

ፖል ፖግባ ከማንቸስተር መልቀቅ እንደሚፈልግ ካሳወቀ በኋላ ማድሪድ 167 ሚሊዮን ዩሮ ማለትም 150 ሚሊዮን ፓውንድ ለመክፈል ዝግጁ መኾኑን ሚረር ትናንት ዘግቦ ነበር። ጁቬንቱስም በቀድሞ አማካዩ ላይ ፍላጎት እንዳለው ማሳየቱን ኮሪዬሬ ዴሎ ስፖርት ዘግቧል።

Frisur Pogba Fußballspieler
የማንቸስተሩ ፖል ፖግባምስል Imago Images

በነገራችን ላይ ማድሪድ ለሉካ ጆቪች እና ኤደን ሐዛርድ ከ250 ሚሊዮን ዩሮ በላይ አውጥቷል፤ ግን አሁንም ተጨማሪ መክፈል ይፈልጋል። ፖል ፖግባ በ2016 ማንቸስተር የገባው በ105 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ነበር። አሁን ማንቸስተር ዩናይትድ በፖል ፖግባ 180 ሚሊዮን ዩሮ ይፈልጋል።

የስፔኑ ማይካ ጋዜጣ እንደዘገበው ከኾነ ፓሪስ ሳን ጄርሜን ኪሊያን ምባፔን ወደ ማድሪድ ለማዞር 230 ሚሊዮን ዩሮ መጠየቁን ዘግቧል። ክፍያው እውን ከኾነ የተጨዋች ዝውውር ከፍተኛ ክፍያ በመኾን ክብርወሰን ያስመዘግባል። እስካሁን ከፍተኛው የዝውውር ክፍያ የብራዚሉ ኮከብ ኔይማር እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2017 ከባርሴሎና ወደ ፓሪስ ሴንጄርሜን የተዘዋወረበት የ222 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ ነው።  

የሪያል ማድሪዱ የ23 ዓመት ማርኮ አሴንሲዮ ወደ ሊቨርፑል ሊያቀና እንደኾነ የእንግሊዙ ኤክስፕሬስ ዘግቧል። ማርኮን ለማግኘት ግን ማድሪድ በለውጡ ሳዲዮ ማኔን ይፈልጋል።  የባርሴሎናው ፊሊፕ ኮቲንሆም ወደቀድሞው ቡድኑ ሊቨርፑል ሊመለስ እንደኾነ ተዘግቧል። ፊሊፕ ኮቲንሆ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በፊት ወደ ባርሳ የተዘዋወረው በ145 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ ነበር። 

Copa America 2019 | Luis Suarez, Uruguay
በኮፓ አሜሪካ ፍጹም ቅጣት ምት የሳተው፤ ሉዊስ ሱዋሬዝምስል picture-alliance/AP Photo/E. Vara

ሉዊስ ሱዋሬዝ ፍጹም ቅጣት ምት በሳተበት የኮፓ አሜሪካ የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ ኡራጓይ በፔሩ 5 ለ4 ተሸንፋ ከውድድሩ ወጥታለች። ብራዚል ፓራጓይን 4 ለ3 አሸንፋ ለግማሽ ፍጻሜ ደርሳለች። ቬኔዙዌላን 2 ለ0 ከረታችው አርጀንቲና ጋር ነው ረቡዕ ዕለት የምትፋለመው።  ኮሎምቢያን 5 ለ4 ያሸነፈችው ቺሊ ሐሙስ ዕለት ፔሩን ትገጥማለች።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ