1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደት ያልገታው የቲዎድሮስ ለገሠ የጥበብ ጉዞ

ሰኞ፣ ኅዳር 27 2014

የጥበብ ሰው ቴዎድሮስ ለገሠ፤ከሀገሩ ቢርቅም በጥበብ ስራዎቹ ግን ለሀገሩ ቅርብ ነው።ለጥቂት አመታት በቆየባት ደቡብ አፍሪቃ እንዲሁም አሁን በሚኖርበት አሜሪካን ሀገር የቴሌቪዝን ድራማዎችን፣ የመድረክ ቲያትሮችን እንዲሁም ፊልሞችን ይፅፋል፣ ያዘጋጃል ይተውናልም።ቲዎደሮስ በአሜሪካን ሀገር የ2021 የበጎ አድራጎት ስራ ተሽላሚም ነው።

https://p.dw.com/p/43rSq
Tewodros Legesse I Äthiopischer Künstler
ምስል privat

ስደት ያልገታው የተዋናይ ቲዎድሮስ ለገሠ የጥበብ ጉዞ


ተዋናይ ቲዎድሮስ ለገሠ የጥበብ መንገዱን የጀመረው ተወልዶ ባደገባት አዲስ አበባ ከተማ ገና የ11ኛ ክፍል ተማሪ እያለ በአማተር የቲያትር ክበቦች ነው።ቆይቶም ከጥበብ ጓደኞቹ ጋር«ፋቡላ»የተሰኘ የቲያትር ክበብ በመመስረት የልብ እሳት የመድረክ ትያትርን ለዕይታ አበቃ። ይህ ቲያትር ለአምስት አመታት ያህል በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ከታዬ በኋላ እዚያው ተቀጥሮ መስራት ጀመረ። በዚህ ሁኔታ የተጀመረው የጥበብ መንገድ ቀጠለና ከቲያትር የጣር ሳቅ ፤የልብ እሳት፣ ዲያስፖራ፣ከፊልም  አጋፔ፣ ያየ ይፍረደው፣ሰርግ ከአሜሪካ ፣የፌስቡክ አርበኞች፣እንዲሁም በአሜሪካን ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ላይ ያተኮረ  ሰንሰለት ተከታታይ የቴሌቪዥ ድራማ፤በበርካታ  የመድረክ ቲያትሮች ፣ፊልሞች እንዲሁም ተከታታይ የቴሌቪዝን ድራማዎች ላይ ሰርቷል። የትወና ብቃቱንም አሳይቷል።
መኖሪያውን  አሜሪካን ሀገር ያደረገው  የጥበብ ሰው ቴድሮስ ለገሠ፤  ከሀገሩ ቢርቅም በጥበብ ስራዎቹ ግን ለሀገሩ ቅርብ ነው።ለጥቂት አመታት ከቆየባት ደቡብ አፍሪቃ እንዲሁም በአሁኑ ስዓት  ከሚኖርበት አሜሪካን ሀገር ሆኖ ተከታታይ የቴሌቪዝን ድራማዎችን፣ የመድረክ ቲያትሮችን እንዲሁም ፊልሞችን ይፅፋል፣ ያዘጋጃል ይተውናልም።
በቅርቡም ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን «ዜማ ፍለጋ» በሚል የሙዚቃ ተሰጦ ያላቸውን ወጣቶች ለማበረታት የቴሌቪዥን የሙዚቃ ውድድር  በማዘጋጀት ላይ ይገኛል።በአሜሪካን ሀገር በየሁለት ወሩ የሚታተም መዝናኛ መፅሄትም ያዘጋጃል።የሬዲዮ የመዝናኛ ዝግጅት ላይም ይሰራል።  
 
ከጥበብ ስራው በተጨማሪ  በተለያዩ  የበጎ አድራጎት ስራዎችም የሚሳተፈው ተዋናይ ቲዎድሮስ ለገሠ ፤በዚህ ስራውም  በአሜሪካን ሀገር «DDEA Humaniterian Award » ከተባለ  ድርጅት የ 2021 የበጎ አድራጎት ስራ ተሸላሚ ሆኗል።በጎ ገፀ ባህሪያትን ወክሎ መጫወት የሚመርጠው ቲዎድሮስ ፤የገፀ ባህሪ ምርጫው ከሚሰራው የበጎ አድራጎት ስራ ጋር  ይያያዝ ይሆን?ያነሳንለት ጥያቄ ነበር።

Tewodros Legesse I Äthiopischer Künstler
ምስል privat
Tewodros Legesse I Äthiopischer Künstler
ምስል privat

መልካም በመሆን የምናጣው ነገር የለም የሚለው ተዎድሮስ ፤ "አቅሜ በፈቀደ መጠን ሰዎችን መርዳት እና ማገዝ ያስደስተኛል።ነግር ግን ገፀ ባህሪ ስመርጥ እኔ በጎ ስለሆንኩ በጎ ብቻ ልስራ አልልም።ያገኘሁትን እሰራለሁ።ያው ተፅዕኖ ያመጣል።የምትሰሪው ስራ እና በውስጥሽ ያለው የተፈጥሮ ነገር በተወሰነ ደረጃ መቀራረብ ይፈጥራል።"በማለት ገልጿል።

 


ሙሉ ዝግጀቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ፀሀይ ጫኔ

ነጋስ መሀመድ