1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስርቆትና ዘረፋ በኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር

ዓርብ፣ ኅዳር 30 2015

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አ.ማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አብዲ ዘነበ ድርጅቱ አገልግሎት ከሚሰጥባቸው መስመሮች ከፍተኛ ችግር ይፈጠርበት ነበር ባሉት 12 ኪ.ሜ በሚሸፍነው የድሬደዋ ክልል ከፍተኛ ለውጥ መታየቱን ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4KjMa
Äthiopische Eisenbahngesellschaft | Dr. Abdi Zenebe
ምስል Mesay Tekelu/DW

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ሐብት ንብረቱ ስለሚሰረቅና ስለሚዘረፍ  ተገቢውን አገልግሎት መስጠት አለመቻሉን አስታወቀ።የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማሕበር እንደሚለዉ የተሰረቁና የተበላሹ መሳሪያዎችን ለመጠገንና ለመተካት ከፍተኛ የዉጪ ምንዛሪ ለማዉጣት ይገደዳል።ማሕበሩ  ከፍተኛ ንብረት ይሰረቅበት ነበር ያለዉ የድሬዳዋ አካባቢ ለዉጥ ማምጣቱን አስታዉቋል።የሚሰረቀዉን ንብረት ዓይነትና ብዛትና ለመተኪያና መጠገኚያ የሚያወጣዉን ገንዘብ መጠን ግን በዉል አልገለፀም።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አ.ማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አብዲ ዘነበ ድርጅቱ አገልግሎት ከሚሰጥባቸው መስመሮች ከፍተኛ ችግር ይፈጠርበት ነበር ባሉት 12 ኪ.ሜ በሚሸፍነው የድሬደዋ ክልል ከፍተኛ ለውጥ መታየቱን ተናግረዋል።ዋና ስራ አስፈፃሚው የባቡር መስመሩ ህብረተሰቡ ከሚኖርባቸው ነባር አካባቢዎች የራቀ መሆኑ እና ለህብረተሰቡ በሚያበረክተው የስራ እድል ፈጠራ ዙርያ ስለሚነሱ ቅሬታዎች ምላሽ ሰተዋል።

 የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚንስትር ዲኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ በበኩላቸው ተመሳሳይ ይዘት አላቸው ባሏቸው ችግሮች ሳቢያ ባቡሩ ተገቢውን አገልግሎት እንዳይሰጥ እየተደረገ ከመሆኑ በላይ መልሶ ለመጠገን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማውጣት መገደዱን አንስተዋል።

 የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚንስትር ደኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ
 የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚንስትር ደኤታ አቶ ደንጌ ቦሩምስል Mesay Tekelu/DW

በእነዚህ ሁሉ ችግሮች ውስጥም ቢሆን ድርጅቱ በመንገደኞች ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሁም የሀገሪቱን የወጪ እና ገቢ  ንግድ እቃዎችን በማጓጓዝ ውጤታማ ስራ መስራቱን ገልጠዋል።

ድርጅቱ ድሬደዋን ጨምሮ የባቡር መስመሩ በሚያልፍባቸው ክልሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ጋር በድርጅቱ ንብረት እና አገልግሎት ላይ በሚያጋጥሙ ችግሮች እና መፍትሄዎች ላይ ውይይት አካሂዷል። 

ከድሬደዋ ውጭ ባሉ አካባቢዎች አሁንም ስርቆት ፣ የባቡር ማስቆም እና ሌሎች ችግሮች እየተፈፀሙ ስለመሆናቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

መሳይ ተክሉ

አዜብ ታደሰ