1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስምንቱ የብልፅግና ፓርቲ መሥራቾች  ተፈራረሙ

እሑድ፣ ኅዳር 21 2012

ዐቢይ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ባደረጉት ንግግር የኢሕአዴግ ውህደትን የተቃወሙ ወገኖች በስም ባይጠቅሱም መልስ ሰጥተዋል።ኢሕአዴግ «ባለፉት አመታት የታመመ ድርጅት ነው» ያሉት ዐቢይ ግንባሩን በእንቁላል መስለው «በጊዜ ባንሰብረው ኖሮ ሕይወት ሊወጣው በፍጹም አይቻለውም» ብለዋል። ሌሎች ፓርቲዎችን በመደራደር በአባልነት እንደሚቀበል ተገልጿል

https://p.dw.com/p/3U3fl
Äthiopien EPRDF
ምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

ሶስት የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች እና አምስቱ የግንባሩ አጋር ድርጅቶች የብልፅግና ፓርቲን የሚመሰርቱበትን ስምምነት ተፈራረሙ። መሥራቹ ህወሓትን ጥሎ የኢሕአዴግ አባሎችን እና አጋሮችን በማዋሐድ በመቋቋም ላይ የሚገኘው የብልፅግና ፓርቲ «ኢትዮጵያን ካለችበት ሁኔታ ወደ ብልፅግና ጎዳና የሚያሸጋግር የአስር አመት ዕቅድ» እንደተዘጋጀለት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ተናግረዋል።

በህወሓት እና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ ለማ መገርሳ ተቃውሞ የቀረበበት የኢሕአዴግ ውህደት የሚፈጥረው ብልፅግና ፓርቲ መቼ የመሥራች ጉባኤ እንደሚያካሒድ እና በይፋ እንደሚመዘገብ እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም። ፓርቲው ሌሎችን በአባልነት ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል።

«የእኛ ፕሮግራም ኢትዮጵያን የሚያሻግር መሆኑን ካመናችሁ እና ጥያቄ ካቀረባችሁ፤ አሁን አገር በመምራት ላይ ካለን ድርጅቶች በተጨማሪ ሌሎች ድርጅቶች ከእኛ ጋር በመሆን ለመታገል ፍላጎት ካላቸው እንደከዚህ ቀደሙ በራችን ዝግ ያልሆነ መሆኑን እና በመደራደር ማንም ድርጅት ከእኛ ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን እንዲያሻግር ፍላጎት ያለን መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ።»

ጠቅላይ ምኒስትሩ የስምንቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊቃነ-መናብርት ስምምነቱን ከፈረሙ በኋላ «ብልፅግና በእውነት እና በእውቀት ላይ ተንተርሶ ኢትዮጵያን ካለችበት ሁኔታ የሚያሸጋግራት ጠንካራ፣ አስተማማኝ በፍቅር የደረጀ ድልድይ ነው» ሲሉ ተናግረዋል።

Äthiopien EPRDF
ምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

«በስሜት እና በምኞት የሚማልሉ ኃይሎች የተለያየ ሐሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ። ብልፅግናዎች እውቀት እና እውነትን መያዝ ምኞት እና ስሜትን መቀነስ ይጠበቅብናል» ሲሉ ዐቢይ ጥሪ አቅርበዋል። «በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ባዶ ምኞት እና ያልተገራ ስሜት ችግር» እየፈጠረ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

ኢሕአዴግ «ባለፉት ጥቂት አመታት የታመመ ድርጅት ነው» ያሉት ዐቢይ ግንባሩን በእንቁላል መስለው «በጊዜ ባንሰብረው ኖሮ አንዳንዶች እንደሚሉት ብንዘገይ ኖሮ ሕይወት ሊወጣው በፍጹም አይቻለውም» ሲሉ ውህደቱን ለተቃወሙ ምላሽ ሰጥተዋል።

የኢሕአዴግ ውህደት ከግንባሩ መሥራች ህወሓት ባሻገር ከኦዲፒ ምክትል ሊቀ-መንበር እና የመከላከያ ምኒስትር ለማ መገርሳ የጠነከረ ትችት ገጥሞታል። አቶ ለማ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የኢሕአዴግ ውህደት «ትክክል አይደለም፤ ትክክል ቢሆን እንኳ ጊዜው አይደለም» ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። የጠቅላይ ምኒስትሩ የቅርብ አጋር የሆኑት አቶ ለማ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከኦሮሞ ሕዝብ ተቀብሏል ያሉትን ጥያቄ ሳይመልስ ውህደት መፈጸም «እምነት ማጉደል ይሆናል» ብለዋል።

«ይኸን ፓርቲ ማዋሀድ ጊዜው አይደለም። ብዙ አደጋ አለው» ሲሉ ማስጠንቀቂያ ጭምር ሰጥተዋል። ለማ «የሽግግር» ባሉት ጊዜ የአገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እና ምጣኔ ሐብታዊ ችግሮች ከኢሕአዴግ ውህደት በፊት ቅድሚያ ሊሰጧቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን አንስተዋል።

Lemma Megersa Verteidigunsminister Äthiopien
ምስል picture-alliance/AA/M. W. Hailu

ዐቢይ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ባደረጉት ንግግር የኢሕአዴግ ውህደትን የተቃወሙ ወገኖች በስም ባይጠቅሱም መልስ ሰጥተዋል። ኢሕአዴግ «ሕይወት ኖሮት ይቺን አገር ተሸክሞ ማሻገር እንዲችል ዘመኑን የሚመጥን ብቃት፤ ዘመኑን የሚመጥን ራዕይ እና አደረጃጀት ያስፈልገው ነበር» ያሉት ዐቢይ «ዛሬ ይኸ ያልገባቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች ቢኖሩ ነገ በኢትዮጵያ ብልፅግና ላይ በጋራ ቆመን ወደ ኋላ ስንመለከት ይኸ ውሳኔ በእውቀት እና በእውነት ላይ የተመሠረተ፤ በልብ እና በአዕምሮ ትስስር ላይ እየተመሠረተ ይቺን ታሪካዊ እና ድንቅ አገር ወደሚገባት ቦታ የሚያደርሳት መሆኑን ሁሉም የሚያምነው እና የሚያየው ይሆናል» ሲሉ ተናግረዋል።

ከኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) ሊቀ-መንበር ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሊቀ-መንበር ምክትል ጠቅላይ ምኒስትር ደመቀ መኮንን እና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሊቀ-መንበር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ስምምነቱን መፈረማቸውን የጠቅላይ ምኒስትሩ ፅህፈት ቤት ይፋ ያደረጋቸው ምስሎች አሳይተዋል።

የኢሕአዴግ ዋና መሥራች የሆነው እና በማዕከላዊ እና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ውህደቱን አጥብቆ የተቃወመው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሊቀ-መንበር ደብረ ጺዮን ገብረ ሚካኤል ከፈራሚዎቹ መካከል አልተገኙም።

የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ) ሊቀ-መንበር አቶ ኦርዲን በድሪ፤ የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶዴፓ) ሊቀ-መንበር አቶ አሕመድ ሽዴ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤህጉዴፓ) ሊቀ-መንበር አቶ አድጎ አምሳያ፤ የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋሕአዴን) ሊቀመንበር ኡሙድ ኡጁሉ እና የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ሊቀ-መንበር አይሻ መሐመድ ኢሕአዴግ አጋር ሲላቸው የቆያቸውን ፓርቲዎች ወክለው ሲፈርሙ ታይቷል። አምስቱ ፓርቲዎች የሐረሪ፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ እና አፋር ክልሎችን እያስተዳደሩ ያሉ ናቸው።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ «ብዙዎች ብልፅግናን የሚቃወሙት እና የሚጠሉት በግልፅ ቋንቋ ሌብነት ጥዩፍ ነው። የማይሰራ፣ የማይተጋ ሰነፍ ከእኛ ጋር መቀጠል አይችልም» የሚል አቋም በመያዙ መሆኑን ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ