1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስልጣን የለቀቁት ባለሥልጣናት፤ የድሬደዋ ነገር፤ ደማቁ የጥምቀት

ዓርብ፣ ጥር 12 2015

«ከኃላፊነታቸው መነሳት መልቀቅ ብቻ ሳይሆን የነበራቸው ኃላፊነት ላይም ላጎደሉት የፍትህ ስርዓት ሁሉ የድርሻቸውን መጠየቅ አለባቸው። ፍትህ ሳይረጋገጥ ዘላቂ ሰላም አይታሰብም።» «ድሬዳዋ ራሷን ችላ መካለል አለባት እንጂ ወደየትኛውም ክልል መካለል የለባትም።»«እንኳን ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፍቅር ሰላም አንድነት የኢትዮጵያን ይሁን»

https://p.dw.com/p/4MW7q
Äthiopien Rücktritt Meaza Ashenafi Präsidentin des Bundesgerichtshofs und Stellvertreter Solomon Areda Waktolla
ምስል Office Prime Minister Ethiopia

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

 

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው “በፍቃዳቸው ከስራቸው መልቀቃቸው” እና በምትካቸዉ አዲስ ሹመት መሰጠቱ፤  የድሬዳዋ ከተማ የፓርላማ ተወካዮች ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀረቡት ጥያቄ እና በድምቀት የተከበረዉ የዘንድሮዉ ጥምቀት በዓል፤ በሚሉ ርዕሶች ስር የተሰጡ አስተያየቶችን  በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅንት ዝግጅታችን አአናብረን ይዘናል።

Störung | WhatsApp, Facebook und Instagram
ምስል Ercin Erturk/AA/picture alliance

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የነበሩት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ እና ምክትላቸው አቶ ሰለሞን አረዳ በገዛ ፍቃዳቸው ከስራ መልቀቃቸው በዚህ የሳምንቱ አበይት ርዕስ ነዉ። ባለስልጣናቱ የስልጣን መልቀቅያ ማስገባታቸዉ የተገለጸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ባለፈዉ ማክሰኞ ጥር 9 ቀን እያካሄደ ባለው መደበኛ ስብሰባ ላይ ነበር። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ምትክ፤ አቶ ቴዎድሮስ ምህረትን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፤ ወ/ሮ አበባ እምቢአለ መንግስቴን ደግሞ፤ ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጎ ሾሟል።

አንዷለም ብሩ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ፤ በካድሬነት እና ባለሞያነት፤ ልዩነቱ ይህ ይመስለኛል። ሞያችሁን እና ክብራችሁን ስላስቀደማችሁ እናመሰግናለን። በነፃነት መስራት ካልቻላችሁ፤ ሽፋን ከመስጠት፤ በግልፅ አስቻይ ሁኔታ እንደሌለ፤ በመልቀቅ ስላስመሰከራችሁ፤ ፍትህ ራሷ ታመሰግናለች።» ሲሉ ጽፈዋል።

Äthiopien Dire Dawa
ድሬደዋምስል Amanuel Sileshi/AFP

መስፍን ታየ የተባሉ ሌላ ተከታታይ በበኩላቸዉ «ከኃላፊነታቸው መነሳት መልቀቅ ብቻ ሳይሆን የነበራቸው ኃላፊነት ላይም ላጎደሉት የፍትህ ስርዓት ሁሉ የድርሻቸውን መጠየቅ አለባቸው። ፍትህ ሳይረጋገጥ ዘላቂ ሰላም አይታሰብም ፤ ሲሉ በአራት ነጥብ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።  ዉለታዉ አባይ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ በአስተያየታቸዉ፤ በፈቃደኝነት ለምን ለቀቁ? ሲሉ ይጠይቃሉ ። በፈቃደኝነት ለምን ለቀቁ?  ስርዓቱ ስለማያሰራ ወይስ በግል ችግር⁈ ሲሉ የጥያቄ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

ኦስማን አልያ ሼ ኑሬ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ በአስተያየታቸዉ ፤ መልካም ሹመት ለተሻምዎች ሲሉ መልካም ምኞታቸዉን በማስተላለፍ ለቀድሞዎቹ ባለስልጣናት መልክት አስቀምጠዋል። ቀድሞ ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት፤ ኃላፊነትን በመተማመን፤ በራስ ፈቃድ መልቀቃቻው፤ ለሀገራችን መልካም አዲስ ወግ ያስተማሩ ትልቅ ሰዎች ናቸው። ምስጋና ይገበቻዋል ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል። መልካም የዳኝነት ስነ ምግባር የነበራቸው ወ/ሮ ማዓዛ አሸናፊ በፍትህ ላይ እየተፈፀመ ያለውን አፈና በመቃወም ነው ሥራቸውን በፍላጎታቸው የለቀቁት፤ አዳድሶቹም ለፍትህ ጥብቅና እንደሚቆሙ ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ አስተያየታቸዉን ያስቀመጡት ደግሞ ናደዉ ገብረፃድቅ ናቸዉ።

Facebook Logo
ፌስቡክምስል Jakub Porzycki/imago images/NurPhoto

የድሬደዋ ከተማ ጉዳይን ወደ ሚያነሳዉ ርዕስ ስናልፍ  ደግሞ

የድሬዳዋ ከተማ የፓርላማ ተወካዮች ከተማዋ ራሷን የቻለች ክልል እንድትሆን አልያም ከኦሮሚያ ወይም ከሱማሌ ክልል ስር እንድትጠቃለል ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድላት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለፌደሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ አቅርበናል ማለታቸው ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያ በርካታ ኢትዮጵያዉያን ከተነጋገሩባቸዉ ርዕሶች መካከል አንዱ ነዉ። ጥያቄው የቀረበው፣ ድሬዳዋ አሁን ባላት አደረጃጀት ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ተጠቃሚ ባለመሆኗ በዕድገት ኋላ ቀርታለች በሚል ተወካዮቹ ይህን ጥያቄ ለማቅረብ መወሰናቸዉን መናገራቸው ተዘግቧል። ሱማሌና ኦሮሚያ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባት ድሬዳዋ ፣ የምትተዳደረው  በሁለቱ ክልሎች ጥምር አስተዳደር መሆኑም ይታወቃል።

የድሬደዋ ልጅ ነኝ ሲሉ አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት ኤሊሳ ደሳለኝ ፤ የድሬዳዋ ተወላጅ ነኝ። ድሬዳዋ ራሷን ችላ መካለል አለባት እንጂ ወደየትኛውም ክልል መካለል የለባትም። ለነዋሪዎቿ የሚበቃ ገቢ ያላት ከተማ ናት ብዙ ፋብሪካዎችም አሏት። በመሆኑም የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ከተማ ስለሆነች በራሷ ልትካለል ይገባል፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል። ድሬ የፍቅር ከተማ ነች ለራስዋ ትበቃለች ፤ በግድ እምቢ ብለዉ ካልወስድዋት በስተቀረ ሲሉ አጠር ያለ አስተያየት የጻፉት ደግሞ ዺርድዋ 1001አድማሱ መንገሻ ናቸዉ። ነጋሽ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ በበኩላቸዉ የባጀት ችግር ከሆነ ለምን የፌደራሉ መንግስት ባጀት አይጨምርም? ሲሉ በጥያቄ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

የጥምቀት ክብረ በዓል በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች በድምቀት ተከብሯል። በትግራይ ክልል መቀሌ በየዓመቱ በአደባባይ ይከበር የነበረው ጥምቀት፤ ዘንድሮም እንዳለፉት ሁለት ዓመታት ሁሉ በአብያተ ክርስትያናት ተወስኖ ነዉ ተከብሮ የዋለዉ። ከመቐለ ከተማ ውጭ ግን በተለያዩ የትግራይ ከተሞች የጥምቀት በዓል በአደባባይ በድምቀት መከበሩን ዘግበናል። በአዲስ አበባ ጃን ሜዳው በተከናወነው የጥምቀት በዓል መጠናቀቂያ እለት በነበረዉ ስነሥርዓት ላይ ፖለቲከኞች ቤተ ክርስቲያንን ያለአግባብ መጠቀሚያ እንዳያደርጉ ጥሪ ተላልፏል። የዘንድሮዉ የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከብሮ በሰላማዊ መንገድ በመጠናቀቁ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም አወንታዊ ምላሽ ተሰጥቶበታል።

Äthiopien Bahirdar Timket Feier
የጥምቀት በዓል አከባበር በባህር ዳርምስል Alemnew Mekonnen/DW

ያሬድ ጥላሁን የተባሉ ተጠቃሚ፤ ብርሃነ ጥምቀቱ በአንድነትና በህብረት የምንደምቅበት በዓል ነው። እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሰን፤ መልካም በዓል ብለዋል። ተስፋዬ ባሳ ሺርኮ፤ በበኩላቸዉ ፤ ጥምቀት ኢትዮጵያ ሰላም ወዳድና ሃይማኖተኛ ሀገር መሆኗን ለዓለም የሚያሳይ መንፈሳዊ በዓል በመሆኑ ደስ ይለናል፤ ሲሉ ደስታቸዉን በአስተያየት ገልፀዋል።

ቡልቻ አባሚልኪ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ፤ እኛ ኢትዮጽያዊያን የምያምርብን አንድነታችን እና ትብብራችን፤ እንዲሁም መተሳሰባችን ነዉና ሁላችንም ጥላቻንና ዘረኝነትን አርቀን በአብሮት እንቁም ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል። እነሆ ከበሮ ደምቆ ሲሰማ፣ ዘፈን ጨዋታው ሲደምቅ፣ በዚህ ዕለት ወጣት ከሽማግሌው፣ ልጅ ከአዋቂው፣ ኮረዳዋም ከጉብሉ በአንድ ይውላሉ ሲሉ አስተያየታቸዉን ያስቀመጡት በለዉ ተስፋዬ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸዉ። ማህደር መሃሪ የተባሉ አስተየያየት ሰጭ ፤ ባህላዊ ሃይማኖታዊ እሴት የሆነው የጥምቀት በአል ፤በሰላማዊ ደስ በሚል ሁኔታ አክብረናል።  ክብርት ከንቲባችን ከጎናችን ስለሆንሽ እናመሰግናለን ብለዋል።

Social Media Apps | WhatsApp Facebook Twitter Instagram
ምስል Nasir Kachroo/ZUMA Press/imago images

ሰላም ኢትዮጵያ የሚል ስም ያላቸዉ ተጠቃሚ፤ ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ የሚለውን አባባል በፍቅር ፤በመከባበር፤በአንድነት በሰላም እንድናሳልፍ ስለ አደረጋችሁን እናመሰግናለን ሲሉ አስተያየት ሰተዋል። ዲንሳ አበበ የተባሉ በበኩላቸዉ በአብሮነታችን ለዘላቂ ሰላማችን  እንትጋ ፤ በፍቅራችንና መከባበራችን ኢትዮጵያን እናፅና ፤በትብብራችንና በጠንካራ ስራችን ኢትዮጵያን ከፍ እናድርግ። መልካም የጥምቀት በዓል ብለዋል። ትዝታ ለሚ የተባሉ በበኩላቸዉ፤ የማይዳሰሱ ድንቅ የዓለም ቅርስ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የጥምቀት በዓል ነውና እንኳን አደረሳችሁ። ፈጣሪ አምላክ ይጠብካችሁ። በመላው ኢትዮጵያ የምትገኙ በያላችበት ሰላማችሁ ይብዛ። በዓሉ የደስታ፤ ተጠምቃችሁ የምትድኑበት መልካም በዓል ይሁንላችሁዲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። 

እንኳን ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፍቅር ሰላም አንድነት የኢትዮጵያን ይሁን!

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ