1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለፌዴራል መንግሥቱ ሹም ሽር የህወሓት መግለጫ

ሐሙስ፣ ጥር 14 2012

በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት የተለያዩ የስራ ኃላፊነት ላይ የነበሩ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎችን ከኃላፊነታቸው ማንሳት «ተቀባይነት የለውም» ሲል ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ አወገዘ። ህወሓት አባላቶቹና ደጋፊዎቹ ከፌደራል መንግስትና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች መነሳታቸውን ተገቢነት የሌለውና መረን የለቀቀ ብሎታል።

https://p.dw.com/p/3Wimq
Emblem der Tigray People's Libration Font (TPLF)

ሕወኃት በመግለጫው የፌዴራልን ድርጊት አውግዟል

በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት የተለያዩ የስራ ኃላፊነት ላይ የነበሩ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎችን ከኃላፊነታቸው ማንሳት «ተቀባይነት የለውም» ሲል ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ አወገዘ። የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ትናንት ማምሻው ባወጣው መግለጫ እንደጠቆመው በአሁኑ ጊዜ «የህወሓት አመራሮችና አባላት በመሆናቸው ብቻ» ከኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስትና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ቦታዎች እንዲነሱ እየተደረገ ይገኛል ብሏል። ህወሓት አባላቶቹና ደጋፊዎቹ ከፌደራል መንግስትና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች መነሳታቸውን ተገቢነት የሌለውና መረን የለቀቀ ተግባር ሲል ገልፆታል፡፡
"በመሆኑም ይህ ሆነ ተብሎ እየተፈፀመ ያለው እና ከዚህ ቀደም የተፈፀመ መረን የለቀቀ ተግባር ሊታረም ይገባል" ያለው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ማእከላይ ኮሚቴ መግለጫ "ካልሆነ ግን ይህንን ተከትሎ ለሚፈጠር ሁኔታ ሀላፊነት የሚወስደው ይህ ህገ-ወጥ ተግባር እየፈፀመ ያለው አካል መሆኑን ግልፅ ሊሆን ይገባል" ሲል አክሏል፡፡በትላንትናው ዕለት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ንግድና ኢንዳስትሪ ሚኒስቴር ሆነው ሲሰሩ የቆዩት የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ከሀላፊነታቸው ተነስተው በርሳቸው ቦታ አቶ መላኩ አለበት መሾማቸው ተገልፆ ነበር፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ ግዜያት በአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የስራ ሐላፊነቶች ላይ የቆዩ የህወሓት አባላት ከስራቸው እየተሰናበቱ መሆኑ ይገልፃሉ፡፡ህወሓት በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የተመሰረተው አዲሱ ውሁድ ብልፅግና ፓርቲ ያልተቀላቀለ ብቸኛ የግንባሩ አባል ፓርቲ ነው፡፡

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ