1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለትናንቱ የጋምቤላ እና ምዕራብ ኦሮሚያ ፀጥታ ችግር የመንግስት ምላሽ

ረቡዕ፣ ሰኔ 8 2014

ዶ/ር ለገሰ በምእራብ ኦሮሚያም በተመሳሳይ መንግስት የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ መውሰዱን ነው የገለጹት፡

https://p.dw.com/p/4Ckqh
Äthiopien | Dr. Legesse Tulu - Kommunikationsminister
ምስል Seyoum Getu/DW

ስለትናንቱ የጋምቤላ እና ምዕራብ ኦሮሚያ ፀጥታ ችግር የመንግስት ምላሽ

በትናንትናው እለት የፀጥታ ችግር በተስተዋለባቸው ጋምቤላ ክልል እና ምዕራብ ኦሮሚያ ዛሬ በተረጋጋ ሁኔታ መዋላቸውን መንግስት አስታወቀ፡፡

አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ታጣቂዎቹ በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ቅንጅት ተመተው አከባቢዎቹን መልቀቃቸውን ነው የገለጹት፡፡ታጣቂዎቹ በፊናቸው በጋምቤላ ያለሙትን ውጥን ስለማሳካታቸው እየገለጹ ነው፡፡

ትናንት በጋምቤላ ከተማ እና በምእራብ ኦሮሚያ ቄለም ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማ እንዲሁም ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ከተማ አከባቢ የኢትዮጵያ መንግስትና የአማፂያን ኃይላት ሲዋጉ እንደዋሉ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ገልጸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ኦነግ ሸኔ የሚለዉና የጋምቤላ ነፃ አዉጪ ግንባር (ጋነግ) ሸማቂዎች ትናንት ማለዳዉን በከተማይቱ ላይ በቅንጅት ጥቃት ከፍተዉ እንደነበርም የጋምቤላ ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በፌስ ቡክ ገፁ ትናንት ዘግቧል። ይሁንና በዛሬው እለት የጋምቤላ ከተማን ጨምሮ ከፍተኛ የቶክስ ልውውጥ ተስተውሎባቸዋል በተባሉ አከባቢዎች መረጋጋት መኖሩ ነው የተገለጸው፡፡ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹት የታጣቂዎቹ የሽምቅ ውጊያ ስልት መከተል ለትናንትናው ፀጥታ መደፍረስ መፈጠር በምክኒያትነት ጠቅሰዋል፡፡ “ሸኔ ከተለያዩ የመሃል ኦሮሚያ አከባቢዎች በመንግስት ፀጥታ ኃይሎች ተቀጥቅጦ በመውጣቱ በሽምቅ ሰርጎ በመግባት በጠረፍ አከባቢዎች የሽብር ጥቃት እንዲያደርስ አድርጎታል” ነው ያሉት ዶ/ር ለገሰ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት ለህ/ተ/ም/ቤት አባላት ማብራሪያ ሲሰጡ ሸኔ ያሉት በኦሮሚያ የሚንቀሳቀስ ታጣቂ ቡድን በከፍተኛ ደረጃ ተመቶ መዳከሙን አንስተው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንትናው ማብራሪያቸው ለሁለት ወራት ገደማ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ተወስዷል ባሉት ዘመቻ ከአንድ ሺህ በላይ የሸማቂው ቡድን ታጣቂዎች መገደላቸውን እና በብዙ ሺዎች ሚቆጠሩ መማረካቸውን በመግለጽ ውጤታማ ያሉት ስራ መከወኑን አንስተዋል፡፡

ዶ/ር ለገሰ በምእራብ ኦሮሚያም በተመሳሳይ መንግስት የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ መውሰዱን ነው የገለጹት፡፡ ይሁንና ትናንት በቲዊተር የመረጃ ማሰራጫ የጻፉት መንግስት ሸኔ ሲል የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ጦር ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ በጋምቤላ ጦራቸው የተፈለገው እላማ አሳክቶ መውጣቱን እና በምእራብ ኦሮሚያ ውጊያው መቀጠሉን አውስተዋል፡፡ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ግን ታጣቂዎቹ ተመተው መውጣታቸውን ነው የሚገልጹት፡፡ ዶ/ር ለገሰ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ላይ “መጠነኛ” ያሉት ጉዳት ደርሷል ከማለት ውጭ በቁጥር ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል፡፡

መንግስት ከህወሓት ጋር ለመደራደር ኮሚቴ ማዋቀሩን መግለጹን ተከትሎ ኦሮሚያን ጨምሮ በተለያዩ አከባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በዚህ የመካተት እድላቸው ምን ያህል ነው የተባሉት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገለግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ይህንንም ጉዳይ ለድርድር የተዋቀረው ኮሚቴ በጥናት ሚመልሰው ይሆናል ብለዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

ሽዋዬ ለገሰ