1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለምርጫው የድሬዳዋ ነዋሪዎች አስተያየት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 15 2013

ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ለክልል ምክር ቤት እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምጣት የነበረባቸው የምርጫ ወረቀቶች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቻ የመጡበት አጋጣሚ እንደነበረም ተገልጧል። እንዲያም ኾኖ ትናንት ምሽት ሦስት ሰዓት ድረስ የተካሄደው ምርጫ በተሳካ መልኩ ተጠናቆ የቆጠራ ውጤቶች በየምርጫ ጣቢያዎች ተለጥፈዋል።

https://p.dw.com/p/3vNEK
ምስል M.Teklu/DW

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቻ የመጡበት አጋጣሚ ነበር

ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ለክልል ምክር ቤት እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምጣት የነበረባቸው የምርጫ ወረቀቶች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቻ የመጡበት አጋጣሚ እንደነበረም ተገልጧል። እንዲያም ኾኖ ግን ትናንት ምሽት ሦስት ሰዓት ድረስ ድሬደዋ ከተማ ውስጥ የተካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ መልኩ ተጠናቆ የቆጠራ ውጤቶች በየምርጫ ጣቢያዎች መለጠፋቸውን በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዐስታውቋል፡፡ በጊዜያዊ ውጤቶቹ ላይ የተለያዩ አስተያየቶችም ተሰጥተዋል፡፡

 የድምፅ  አሰጣጡ መጠናቀቅን ተከትሎ መግለጫ የሰጡት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድሬደዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ዚያድ ያሲን በምርጫ ወረቀቶች ስህተት ሳቢያ በሶስት ምርጫ ጣቢያዎች የፌደራል ምክር ቤት እንዲሁም በአንድ ምርጫ ጣቢያ የፌደራልም ሆነ የአስተዳደር ምክር ቤት ምርጫ አለመካሄዱን ገልፀዋል፡፡ ያጋጠመውን ጉዳይ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርደ ማስታወቃቸውንና በቀጣይ ቦርዱ በሚያስቀምጠው የመፍትሄ አቅጣጫ መሰረት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

እስከ ትናንት ምሽት ሶስት ሰዓት ድረስ ሲካሄድ ያመሸውን የምርጫ ሂደት ተከትሎ የድምፅ ቆጠራው ሌሊቱን መጀመሩን በእንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች ተገኝቼ ተመለክቻለሁ ፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ዛሬ ጠዋት ጀምሮ ጊዜያዊ ውጤቶች በየምርጫ ጣቢያዎች በመለጠፍ ላይ ናቸው፡፡በነዚህ ጣቢያዎች ውጤት ሲመለከቱ ከነበሩ ነዋሪዎች አቶ በጅሮንድ ዮሀንስ እና አስር አለቃ አፈወርቅ ሲሳይ ውጤቱ ትክክለኛ ነው ብለዋል፡፡

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድሬደዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ዚያድ ያሲን
ምስል Mesay Tekelu/DW

በሌላ በኩል በተወዳደሩበት ምርጫ ጣቢያ የተለጠፈው ውጤት ትክክል አይደልም የሚል አስተያየት የሰጡት በድሬደዋ የመላው የኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት እጩ ቅሬታቸውን ለምርጫ ቦርድ እንደሚያስገቡ ተናግረዋል፡፡ የምርጫውን መጠናቀቅ ተከትሎ መግለጫ የሰጡት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድሬደዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ዚያድ ያሲን አስካሁን ከውጤት ጋር የተያያዘ ምንም ዓይነት ቅሬታ አለመቅረቡን ገልፀው የምርጫው አጠቃላይ ውጤት በአምስት ቀናት ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በትናንትናው ምርጫ የአፍሪካ ህብረት ፣ የምስራቅ አፍሪካ ስታንድባይ ፎርስ ፤ ድሬ የተቀናጀ የማህበረሰብ ሲቪክ ማህበር እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የህዝብ ታዛቢዎች ተገኝተዋል፡፡

መሳይ ተክሉ

ሸዋዬ ለገሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ