1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ነዋሪዎች አስተያየት

ዓርብ፣ መጋቢት 16 2014

የኢትዮጵያ መንግስት በጦርነት አካባቢዎች በምግብ እጥረት ለተጎዱ ወገኖች አርዳታ እንዲደርስ  የተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉ ትክክለኛ እርምጃ ነው ሲሉ አንዳንድ የአማራ ክልል ነዋሪ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ።ሌሎች ደግሞ ውሳኔውን ነቅፈዋል፣ ውሳኔው ተግባራዊ ሊሆን መቻሉን ያስቀመጡም አሉ፡፡

https://p.dw.com/p/492nj
Äthiopien IDPs in der Region Amhara
ምስል Alemenw Mekonnen/DW

ስለግጭት የማቆም ውሳኔ የአማራ ክልል ነዋሪዎች አስተያየት

የኢትዮጵያ መንግስት በጦርነት አካባቢዎች በምግብ እጥረት ለተጎዱ ወገኖች አርዳታ እንዲደርስ  የተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉ ትክክለኛ እርምጃ ነው ሲሉ አንዳንድ የአማራ ክልል ነዋሪ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ፣ ሌሎች ደግሞ ውሳኔውን ነቅፈዋል፣ ውሳኔው ተግባራዊ ሊሆን መቻሉን ያስቀመጡም አሉ፡፡ ዶይቼ ቬሌ የመተማን፣ የደሴን፣ የቆቦን፣ የጉና ቤጌምድርንና የጋዝጊብላ ነዋሪዎችን አስተያየት ጠይቋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራና የትግራይ ህዝቦች አንድነትና ወንድማማችነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ትናንት በባሕር ዳር የተጀመረው የአማራ ክልል ምክር ቤት አመልክቷል፡፡
ካለፈው ጥቅምት 2013 ዓም ጀምሮ በኢትዮጵያ መንግስትና በትግራይ ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ሚሊዮኖች ለእንግልትና ለመፈናቀል ተዳርገዋል፣ ብዙዎች ለከፋ የምግብ እጥረትም  ተጋልጠዋል፡፡ በምግብ ለተጎዱ አካባቢዎች እርዳታ ማድረስ ይቻል ዘንድ የኢትዮጵያ መንግስት የተኩስ አቁም ማድረጉን ትናንት አስታውቋል፡፡ በውሳኔው ዙሪያ በአማራ ክልል የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አስተያየት ጠይቀናል፡፡ አቶ መከተ ካሳው የደሴ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ውሳኔውን በበጎ ከተመለከቱት መካከል አንዱ ናቸው፤ ሆኖም መንግስት ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ህወሓት ይቀበላል የሚል እምንት የላቸውም፡፡ 
በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የጋዝጊብላ ወረዳ ነዋሪው አቶ ገብረስላሴ ጌታሁን በበኩላቸው ውሳኔው መልካም ቢሆንም ዘላቂ መፍትሔ ግን አያመጣም ባይ ናቸው፡፡ 
የተላለፈው ውሳኔ ለዘላቂ ሰላም መንገድ ይከፍታል፣ ግን ውሳኔውን ህወሓት ይቀበለዋል የሚል እምነት እንደሌላቸው የነገሩን ደግሞ በሰሜን ወሎ ዞን የቆቦ ከተማ ነዋሪው አቶ አሌ በላይ ናቸው፡፡ 
ውሳኔውን ህወሓት አመስግኖም ቢሆን ይቀበላዋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬሌ የሰጡት በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሀ ነዋሪው አቶ ሙሉጌታ ዓለምነህ ናቸው፤ የመንግስትን ውሳኔ የዘገየ ነው ቢሉትም አድንቀውታል፡፡ በደቡብ ጎንደር ዞን የጉና ቤጌምድር ነዋሪ አቶ ሁነኛው ያለው ግን የተለየ አስተያየት አንፀባርቀዋል፣ የመንግስትን ውሳኔ አይቀበሉትም፣ እርዳታ ለተቸገሩ ወገኖች ለማድረስ አማራጩ ጦርነቱን በድል ማጠናቀቅ ብቻ ነው ይላሉ፡፡ 
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት በተጀመረው የአማራ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ንግገር ያደረጉት የምክርቤቱ አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ የአማራና የትግራይ ህዝቦች አንድነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡ ጦርነቱን ተከትሎ በተፈጠረ ሰብአዊ ቀውስ በአማራ ክልል ብቻ ከ11 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጋለጠ መሆኑን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡ 

Äthiopien IDPs in der Region Amhara
ምስል Alemenw Mekonnen/DW

ዓለምነው መኮንን 
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ