1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለ ወሎ ቀውስ፤ ስለ መቐለ የአየር ድብደባ እና የቦረና ድርቅ ምን ተባለ?

ዓርብ፣ ጥቅምት 12 2014

በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የፈጸማቸው የአየር ድብደባዎች፤ ውጊያ በበረታበት የአማራ ክልል የሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞን የተቀሰቀሰው ሰብዓዊ ቀውስ እና የቦረና ድርቅ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሣምንቱ መነጋገሪያ ከሆኑ መካከል ይገኙበታል።

https://p.dw.com/p/42054
Äthiopien | Erneuter Luftangriff auf Hauptstadt von Tigray
ምስል UGC/AP/dpa/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል የጸጥታ አስከባሪዎች ከትግራይ ኃይሎች ጋር የሚያደርጉት ውጊያ ወደ ወሎ ዘልቆ ከገባ በኋላ የተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ለማኅበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚዎች አሳሳቢ እና መነጋገሪያ ሆኗል። በደቡብ ወሎ ዞን በምትገኘው ኮምቦልቻ ነዋሪ የሆኑት አብዱሰላም ሺፋው የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ያጋሩት ምስል እና የጻፉት አጭር ሐተታ በአካባቢው የበረታውን ቀውስ በጥቂቱም ቢሆን የሚያሳይ ነው።

በፎቶግራፎቹ አንዲት ዕድሜያቸው የገፋ እናት አይኑ የታመመ አዳጊ ታቅፈው ይታያሉ። አብዱሰላም "ከቤታቸው ከወጡ ሶስት ወር እየሆናቸው ነው። አገራቸው ሀሮ ሲሆን ከወራት በፊት ወደ ድሌሮቃ ተፈናቅለው ከሌሎች ወገኖቻቸው ጋር ጫካ ከረሙ። ሁለተኛው ስደታቸው ወደ ኮምቦልቻ ነበር እና ኮምቦልቻ ለመድረስ ያዩትን ስቃይ ሲነግሩኝ አለማልቀስ አልቻልኩም" ይላሉ በምስሉ ስለሚታዩ እናት እና አዳጊ በጻፉት አጭር ሐተታ።

"በረንዳ ላይ ማደር ከጀመሩ ዛሬ [ረቡዕ ጥቅምት 10 ቀን 2014 ዓ.ም] አራተኛ ቀናቸው ነው። የታቀፉት የልጅ ልጃቸው ሲሆን ደረቅ ጡታቸውን አጥብተው እንዳሳደጉትና አባቱ ሳይወለድ እናቱ ደግሞ በሰባት ወሩ እንደሞቱበት ነግረውኛል" ይላሉ አብዱሰላም።

"ዛሬ ከብርዱም ከረሃቡም በላይ የሚያስጨንቃቸው የልጅ ልጃቸው በአይን እና ሌሎችም ህመሞች እየተሰቃየ መሆኑ ሲሆን ቀንም ሌሊትም እንዲህ አቅፈው እየየ እያሉ ነው። ያገኘናቸው ከመሸ ስለነበር ልጃቸውን ነገ እንደምናሳክም ቃል ገብተን፤ አይዟችሁ ብለን ተመልሰናል" ያሉት አብዱሰላም ሺፋው "እየሆነብን ያለው ነገር ምን ቃል ይገልጸው ይሆን? ይህስ ስቃይ መቆሚያው መቸ ይሆን?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ጨቅላዎችን ጨምሮ ሕፃናት የያዙ እናቶች ፎቶግራፎች ይዘዋወራሉ። በውጊያው ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ለመንከራተት መገደዳቸውን የሚገልጹ መረጃዎች በተለይ እርዳታ ለማሰባሰሰብ ጥረት በሚያደርጉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች በስፋት ይታያሉ።

ኑረዲን ነስሮ ባለፈው ረቡዕ በፌስቡክ ገጻቸው "በዛሬው ውሏችን አንዲትን እናት ተመለከትን። ባሏ ጦር ሜዳ ቀርቶባት 6 ጨቅላ ህፃናት ታቅፋ በእድሜ የገፉ ወላጅ እናቷን አስከትላ በኮምቦልቻ ቀዲዳ ትምህርት ቤት መጠለያ ተገኘች። ልጆቿን ረሀብ አጎሳቁሏቸው፤ አቅመ ደካማ እናቷን በሽታ ተጭኗቸው ነበር። ከልጆቿ ውስጥ አንዱ ከተወለደ ገና 1 ወር ከ15 ቀን በቅጡ እንኳን አልሞላውም። አይኖቹ በሞራ ተጋርደዋል። ታዲያ በፍጥነት ካልደረስንለት በለጋ ዕድሜው የአይን ብርሃኑን የሚያጣ ይሆናል" የሚል መረጃ አስፍረዋል።

Karte Äthiopien Amhara ETH
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል የጸጥታ አስከባሪዎች ከትግራይ ኃይሎች ጋር የሚያደርጉት ውጊያ ወደ ወሎ ዘልቆ ከገባ በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች ተፈናቅሏል።

ይኸው መረጃ በሰፈረበት የኑረዲን የፌስቡክ ገጽ አይኑ የታመመ ጨቅላ ልጅ እና የእናቱ ፎቶግራፍ ይገኛል። ኑረዲን ጨቅላው ሕጻን "ከነቤተሰቡ እንዲህ መሰቃየቱ ሳያንሰው በበሽታው ምክንያት አይኖቹ ሊጠፉ ነው። እዚህ ትምህርት ቤት ከተሰበሰቡት በርካቶች በእንዲህ ያለ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ያሉ በመሆናቸው እንደተለመደው ሁላችንም በምንችለው መልኩ የአቅማችንን ድጋፍ ልናደርግላቸው፤ እንደ ወገን ድምፅ ልንሆናቸው እና በፀሎት ልናስባቸው ዘንድ ግድ ይለናል" የሚል ጥሪ አቅርበዋል።

ከዕለት ወደ ዕለት እየበረታ የመጣው የወሎ ቀውስ እንዴት መፍትሔ ሊያገኝ እንደሚችል አይታወቅም። የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚቀባበሉት እና የጥብቅና ባለሙያው መንግሥቱ ዘገየ መሆኑ የተገለጸ ግጥም የወሎን ነባራዊ ሁኔታ በሚያስተውሉ ሰዎች ዘንድ የተፈጠረውን ስሜት ይገልጸው ይሆናል።

"እነርሱ ፎክረው፤

እነርሱ ሸልለው፣

እነርሱው አቅራርተው፣

ጋቢያቸውን ለብሰው፣ አሉ ከቤታቸው፣

የአብርሃም በግ ሆኖ በየበራበሩ ከርታታው ወሎየ እየሞተላቸው" ይላል ግጥሙ።

አቡሐኒፋ ሙሀመድ ሰዒድ በሚል የፌስቡክ ገጽ የሰፈረ አጭር ትዝብት "መንግሥት የእናቶች ዱዓ አለኝ እንደሚለው የእናቶች እንባስ አያስፈራውም ይሆን?" እያለ ይጠይቃል።  "ወሎ ዋጋ እንዲከፍል እየተደረገ ይገኛል" የሚለው ይኸው አቡሐኒፋ ሙሀመድ ሰዒድ በተባለ የፌስቡክ ገጽ የሰፈረ ጽሁፍ "ይህ ጉዳት፣ ስብራት፣ ሃዘን፣ ቁጭትና ትካዜ ከዚህ በፊት ይጎበኘናል ብለው ያልጠበቁት እኒህ የወሎ እናቶች በሚያነቡት እንባ የደረሰባቸውን መከራ ይገልፃሉ። በማያባራውና በማያቋርጠው ጦርነት አርሶና ለፍቶ የሚኖረው አቅመ ደካማው ህዝብ ጉዳቱ ይበልጥ ደቁሶታል። ጦርነቱን ሆን ተብሎ በወሎ ምድር ላይ እንዲበረታ ተደርጓል። እለት እለት ይሻላል ቢባልም ጉዳቱ ግን እየበረታ ይታያል" ይላል።

Äthiopien | Luftangriff auf der äthiopische Armee auf Mekelle
የኢትዮጵያ መንግሥት የአየር ድብደባዎቹ "ዒላማ ያደረጉት የህወሓት የጦር መሣሪያ ማምረቻ እና የጦር ትጥቅ ጥገና ጣቢያዎችን ብቻ ነው" ቢልም ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን የትግራይ ቴሌቭዥን ዘግቧል። ምስል Million Haileselassie/DW

በመቐለ ስለተፈጸሙ የአየር ድብደባዎች ምን ተባለ?

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በመቐለ ከተማ እና አካባቢው የፈጸማቸው የአየር ድብደባዎች በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ኹነኛ መነጋገሪያ ሆነው ታይተዋል። የመጀመሪያው የአየር ድብደባ የተፈጸመው ባለፈው ሰኞ ሲሆን የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ለገሰ ቱሉ "መንግሥት ለምን የራሱን ከተማ ያጠቃል? መቐለ የኢትዮጵያ ከተማ ነች" ሲሉ አስተባብለው ነበር። ዘግየት ብሎ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት በእርግጥም ድብደባው መፈጸሙን አረጋግጧል። 

የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ የተባለው እና የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያስተዳድረው የፌስቡክ ገጽ ከትናንት በስቲያ ረቡዕ "መከላከያ ሠራዊት ያካሄዳቸው የአየር ድብደባዎች ዒላማ ያደረጉት የህወሓት የጦር መሣሪያ ማምረቻ እና የጦር ትጥቅ ጥገና ጣቢያዎችን ብቻ ነው" ብሎ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚለው "የመከላከያ ሠራዊት የሚያከውናቸው እነዚህ ሥራዎች የሽብር ድርጅቱ ከባድ የጦር መሣሪያዎችን እና ሌሎች ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎችን ለመሸሸግ የሚጠቀምባቸውን እና ወደ ወታደራዊ መገልገያነት የቀየራቸውን የተወሰኑ ቦታዎች ከጥቅም ውጭ ለማድረግ ያለመ ነው።" 

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ትዊተር ላይ ካሰፈሯቸው አጫጭር ጽሁፎች በአንዱ የአየር ድብደባዎቹ የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በውጊያ ደርሶበታል ያሉትን ኪሳራ ለማካካስ በመቶዎች ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኙ ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ አድርጓል ሲሉ ከሰዋል። የትግራይ ቴሌቭዥን ጣቢያ በመቐለ እና አካባቢው በተፈጸሙ የአየር ድብደባዎች ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን በፌስቡክ ገጹ የተጎጂዎችን ምስል ጭምር በማካተት ባሰራጨው ዘገባ አትቷል። በመቐለ ከተማ የሚገኘው አይደር ሆስፒታል ባለሥልጣናትም በአየር ድብደባዎቹ ሰዎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን ለዶይቼ ቬለ ዘጋቢ አረጋግጠዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት የአየር ድብደባዎቹን ባረጋገጠበት ጽሁፍ ሥር ጋሹ ድረስ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "ግንባር ላይ መደብደብ ያልቻለ አየር ኃይል መቀሌ ሂዶ መስክ ላይ ቦምብ ለምን ይጥላል?" ሲሉ ጠይቀዋል። በጉዳዩ ላይ የፌስቡክ እና የትዊተር ተጠቃሚዎች የሚሰጧቸው አስተያየቶች ኢትዮጵያውያን የገቡበትን ጥልቅ መከፋፈል የሚያሳዩ ናቸው። የአየር ድብደባው "ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥትንም "ጥሩ ውሳኔ ነው በርቱ" ያሉ የመኖራቸውን ያክል ውግዘቱም ብርቱ ነው። 

አሮን በሪሁ "መቐለ በኢትዮጵያ መንግሥት ጨካኝ ጥቃት እየተፈጸመባት ነው። ላለፉት አስራ አንድ ወራት ንጹሀን ሰላማዊ ሰዎች ያለ ርኅራሔ የጥቃት ዒላማ ሲሆኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዴት ዝም ይላል?" ሲሉ ጠይቀዋል።  አሮን በትግራይ ክልል በረራ እንዲከለከል የሚጠይቀውን መልዕክት በእንግሊዘኛ በትዊተር ባሰፈሩት አስተያየት አጋርተዋል። የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች በትግራይ በረራ እንዲከለከል ግፊት ሲያደርጉ ታይተዋል። 

ታሜ ጅግሳ ዋሪ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ በአየር ድብደባው የተቃጠሉ ንብረቶች የሚያሳይ ፎቶግራፍ አስደግፈው "ጦርነት ከሚያስከትላቸው መዘዞች የአእምሮ ጤና ላይ የሚያሳድረው ተጽኖ በጣም አስከፊ ነው። በዚህም ህጻናት፣ ሴቶች፣ እናቶች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች የበለጠ ይጎዳሉ። የጦርነትን አስከፊነት ከኔ የበለጠ የሰላም ኖቤል ተሸላሚው ያውቀዋል" በማለት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጠቀስ ያደረገ አስተያየት አስፍረዋል። 

አብርሐም መገርሳ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "ደርግ የመጨረሻ ዕድሉን በአየር ኃይሉ ሲሞክር ገበሬው ለጄኔራሎቹ
"በእግር አልሆን ሲለው መጣ በሰማይ
መሬት ከለቀቀ መንግሥት አለወይ?"
ብሎ እንደተቀኘ ጠቅሰው "ወይ የኛ የታሪክ መመሳ…ሰ…ል አንድ አይነት?" ሲሉ ጠይቀዋል።

 የቦረና ድርቅ እና የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ውትወታ

Südostäthiopien | Dürre in Borena
በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ ትኩረት እንዲያገኝ በሳምንቱ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ውትወታ ሲደረግ ነበርምስል Seyoum Getu/DW

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ ትኩረት እንዲያገኝ በሳምንቱ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ውትወታ ሲደረግ ነበር። በኢትዮጵያ እና የተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ሰዎች ለተቸገሩ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ዕርዳታ ለማሰባሰብ ጥረት ሲያደርጉም ታይተዋል።

ኪያ ገብረወልድ "ፖለቲካው ይደርሳል ህዝብ ሲኖር ነው ሀገርን እንደ ሀገር ማስቀጠል የሚቻለው። ደጉ የቦረና ህዝብ ተፈጥሮ ፊቷን አዙራባቸው እርዳታችንን ይሻሉ። በእርግጥ አሁን ካለው መንግሥት እርዳታን አንጠብቅም። የተቻለንን ግን በመርዳት ከጎናቸው እንሁን" የሚል ተማጽኖ አቅርበዋል።

ሐላቄ ጀልዴሳ በትዊተር ከአንዲት ሕይወቷ ካለፈ ላም አጠገብ ተክዞ ጭንቅላቱን የደገፈ ወጣት ምስል የሚታይበት ፎቶ አጋርተው "ለቦረና ሕዝብ ላሞች ያላቸውን ዋጋ የሚረዳ ይኸን አሳዛኝ ምስል ተመልክቶ እንባውን ለመቆጣጠር ይቸገራል" ሲሉ የችግሩን ጥልቀት ሊገልጹ ሞክረዋል።

ነጋሳ ያደሳ ደግሞ "በቂ ውኃ ማግኘት ሰብዓዊ መብት ነው። ለማኅበረሰቦች በቂ ውኃ ማቅረብ የመንግሥት ኃላፊነት ነው። በደቡብ ኦሮሚያ የቦረና ዞን በቂ የከርሰምድር ውኃ ቢኖረውም በድርቅ ተቸግሯል" ሲሉ ትኩረት እንዲሰጥ ወትውተዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት በኦሮሚያ ክልል ቦረና እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ለተፈጠረው ብርቱ የውኃ እና የምግብ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት በአካባቢው የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች እንደሚገኙ በትዊተር ገልጿል። ምግብ፣ የእንስሳት መኖ የግብርና፣ የጤና እና የንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶች ለተቸገሩ መቅረቡን የገለጸው ድርጅቱ ነገር ግን ከዚህ በላይ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስቧል።

በቦረና ዞን ዳስ ወረዳ የእንስሳት ሐብት ቢሮ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ፍራኦል ዋቆ በድርቁ ምክንያት በቦረና ከ9 ሺሕ በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸውን በዚህ ሳምንት ለዶይቼ ቬለ ተናግረው ነበር። ዶክተር ፍራኦል እንዳሉት 21 ሺሕ ገደማ ከብቶች ያለ ሰው ድጋፍ መንቀሳቀስ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ዶክተር ፍራኦል የዞኑን መረጃ ጠቅሰው እስከ 500 ሺሕ የሚደርስ ሰው የውኃ፣ 17 ሺሕ ገደማ ደግሞ የምግብ እጥረት እንደገጠመው ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ