1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ቴክኒክአፍሪቃ

ስለ ቲክ ቶክ አፕሊኬሽን (መተግበሪያ) ምን ማወቅ አለብን?

ዓርብ፣ መስከረም 8 2013

የቲክ ቶክ አፕሊኬሽን ወይም መተግበሪያ በአሁኑ ሰዓት እጅግ ዝነኛው የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ነው ማለት ይቻላል። ከሌሎቹ ማህበራዊ መገናኛዎች ለየት የሚያደርገው ደግሞ አጫጭርና እንዲያዝናኑ የታሰቡት ቪዲዮዎች የሚቀርቡበት መሆኑ ነው። አብዛኞቹ ታዳሚያን ወጣቶች ቢሆኑም በርካታ እድሜያቸው አስራ ቤት ያልደረሱ ታዳጊዎች ሳይቀሩ ሲሳተፉበት ይስተዋላል።

https://p.dw.com/p/3ig9A
USA TikTok Bürogebäude in Kalifornien
ምስል Getty Images/M. Tama

ቲክ ቶክ ደንበኞች ያለ ምንም ክፍያ መጠቀም የሚችሉት መተግበሪያ ነው። ከአራት አመት በፊት ቻይና ውስጥ ይፋ የሆነው ይህ መተግበሪያ ዶዊን (DouYin)  የሚል መጠሪያ አለው። ከባለቤቷ ቻይና ውጪ በተቀሩት ሀገራት ግን ቲክ ቶክ በሚለው ስሙ ይበልጥ ይታወቃል። ተጠቃሚዎቹ አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች እና ህፃናት ሲሆኑ ራሳቸውን በድርጊት ላይ የሚያሳይ ቪዲዮ ቀርፀው ጓደኞቻቸው ወይም ሁሉም ሰው እንዲያየው በዚሁ የኢንተርኔት መድረክ ላይ ያጋራሉ። አብዛኛውን ጊዜ ተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ ሲደንሱ ወይም ከሚሰማው ድምጽ ጋር የአፋቸውን እንቅስቃሴ አመሳስለው ሲናገሩ ወይም ሲዘፍኑ ይታያሉ።
ተመልካቾቹ ቪዲዮው ካስደሰታቸው እዛው ላይ ያለውን የልብ ምልዕክት በመጫን አድናቆታቸውን መግለፅ ወይም የፁሁፍ አስተያየት መስጠት አልያም ቪዲዮውን እንደ ኃትስዓፕ ያሉ ሌሎች የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ለሌሎች ማጋራት ይችላሉ። ኢትዮጵያዊው  ወጣት በረከት አብ በየነ  እንደዚሁ ጎደኞቹ አጋርተውት ነበር  ለመጀመሪያ ጊዜ ከቲክ ቶክ ጋር የተዋወቀው፤ « ትምህርት ነክ የሆነ ቪዲዮ ቲክ ቶክ ላይ አለ ብለውኝ » በዚህ አጋጣሚ ነው መጠቀም የጀመርሙት የሚለው የ17 ዓመቱ ወጣት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነው። ቲክ ቶክ ሲጠቀም  አምስት ወሩ ሲሆን የግሉ የሆነ ገፅ ወይም አካውንትም ከፍቷል። ይሁንና የራሱ የሆነ ቪዲዮ እስካሁን አልቀረፀም። 
ምንም እንኳን በረከት አብ ከበስተ ጀርባ ሆኖ ቲክ ቶክ የሚጠቀም ወጣት ቢሆንም፤ መፈለጊያው ላይ ኢትዮጵያ ወይም ሀበሻ ብሎ ቁልፍ ቃላት የሰጠ ሰው በርካታ በኢትዮጵያውያን ወይም ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተሰሩ የግለሰብ ቪዲዎችን ያገኛል። ከጀማሪ እስከ ዝነኛ፤ ከልጅ እስከ አዋቂ ሁሉም ተሳታፊ ናቸው። ኢንታግራም ላይ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሏት ተዋናይት ሰላም ተስፋዬም ቲክ ቶክን በቅርቡ ተቀላቅላለች፤ «ብዙ ታሌንት የሚታይበት ነው። ከኛ ሙያ ጋር የተገናኘ ብዙ ነገር አለው።» ስትል ቲክ ቶክን ለየት የሚያደርገው ምን እንደሆነ ትገልፃለች። 
ሰላም ቲክ ቶክ ላይ ገና ጀማሪ ብትሆንም ከሌሎቹ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጋር ስታነፃጽር ፈጣን ነው የምትለው ነገርም አግኝታበታለች። « እንደ ዮ ቲውብ ወይም ኢንስታግራም ብዙ ቪዲዮ አልሰራሁበትም። ነገር ግን በጣም ፈጣን ነው። ሰው በጣም ያየዋል። ተዋናይቷ ቲክ ቶክ ላይ የለጠፈቻቸው ቪዲዮዎች በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተመልካች ያገኘም ቪዲዮ አላት። 
ሰላም ብዙ አይነት አስተያየት ቢደርሳትም እሷን የሚያሳስባት በስሟ የሚከፈቱት ገፆች ናቸው። ቲክ ቶክ ላይም በእሷ ስም እና ፎቶ ቢያንስ ሁለት ገፆች ይገኛሉ። አንደኛው ከ53 ሺ በላይ ተከታይ ያሉት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከ 42ሺ በላይ ተከታዮች አሉት። እሷ የኔ ነው የምትለው ሁለተኛውን ነው። « ትክክለኛውን አድራሻዬን ከዮቲውብ ቻናሌ ጋር ያገናኘሁት ነው» ትላለች።
 ምንም እንኳን ቲክ ቶክ ላይ የሚለቀቁት ተንቀሳቃሽ ምስሎች አጫጭር ቢሆኑም እዚህ መተግበሪያ ላይ ብዙ ሰዓት ማጥፋት በተለይ ለወጣቶች ቀላል ነው። አባል የሚሆኑትን ወጣቶች ትክክለኛ እድሜ የሚቆጣጠር ስለሌለም ህፃናትም የግል ገፅ ሊከፍቱ ስለሚችሉ ወላጆች የልጆቻቸውን ስልክ እንዲቆጣጠሩ ባለሙያዎች ይመክራሉ። በተለይ በኮሮና ምክንያት ትምህርት ተቋርጦ ተማሪዎች እቤት በሚውሉበት ጊዜ የቲክ ቶክ አባላት ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንደጨመረ ይነገራል።
Sensor Tower እንደተባለው ድርጅት ከሆነ የቲክ ቶክ መተግበሪያ ከ ሁለት ቢሊዮን በላይ ዳውን ሎድ ተደርጓል ወይም ተጠቃሚዎች መተግበሪያውን ስልካቸው ላይ ጭነዋል። ይሁንና በፍጥነት በማደግ ላይ ያለው መተግበሪያ እጅጉን አነጋጋሪም ሆኗል። በተለይ በህንድ እና በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥታት ዘንድ። ህንድ ቲክ ቶክን ጨምሮ 59 የቻይና መተግበሪያዎችን በቅርቡ ከማገዷ በፊት ቲክ ቶክን ህንድ ውስጥ ብቻ 200 ሚሊዮን  ገደማ ሰዎች ይጠቀሙ ነበር።  የህንድ መንግሥት መተግበሪያውን ያገደው የቻይናው ድርጅት ለህዝቡ  ሉዓላዊነት እና ታማኝነት የለውም። ከዚህም ባለፈ ለመከላከያና ለብሔራዊው ደህንነት እንዲሁም ለህዝቡ ሰላም ጎጂ የሆነ ተግባራት ውስጥ ቲክ ቶክ ተሳትፏል በሚል ነው። የህንድ ጎረቤት ሀገር ባንግላጅሽም ይህንን መተግበሪያ ያገደች ሌላኛዋ ሀገር ናት። የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም ቢሆኑ ቲክ ቶክን ከዩናይትድ ስቴትስ ለማገድ በተደጋጋሚ ያደረጉት ዛቻ ዛሬ እውን ሆኗል። ከመጪው እሁድ አንስቶ የቲክ ቶክ መተግበሪያን  ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ስልክ ላይ መጫን አይቻልም። እጎአ ከህዳር 12 ቀን 2020 ዓም አንስቶ ደግሞ ቲክ ቶክ ሙሉ በሙሉ በሀገሪቱ የማይሰራ ይሆናል ተብሏል።

Tik Tok
ምስል picture-alliance/F. May
Bildkombo Ägypten Influencerinnen Haneen Hossam und Mowada al-Adham
የግብፅ የቲክ ቶክ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ምስል AFP/K. Desouki

ቲክ ቶክ 18 አመት ካልሞላቸው ወጣቶች በህገ ወጥ መንገድ መረጃ ሰብስቧል በሚል ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የ 5,7 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ተፈርዶበት ነበር። ከዚህም ክስ በተጨማሪ የቻይናው ባይትዳንስ የተባለው ድርጅት እድሜያቸው ከ 13 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ምንም አይነት መረጃ እንዳይሰበስብ መስማማት ነበረበት።  የገንዘብ ቅጣቱ ግን ግዙፍ ለሆነው ቲክ ቶክ ምንም ማለት አይደለም። እንደ ብሉምበርግ የዜና ምንጭ ከሆነ ድርጅቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ገቢውን ከ 7,4 ቢሊዮን ወደ 17 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍ ለማድረግ ችሏል። 
ቲክ ቶክ ዮናይትድ ስቴትስ ውስጥ በመከልከሉ በተለይ በአለም አቀፍ ዘንድ ዝና ያተረፉ እና የቲክ ቶክ ኢንፍሎንሰር ወይም ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባሉት በአንድ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮቻቸውን ያጣሉ። በአለም አቀፍ መዘርዝር ከአንድ እስከ አምስት የተቀመጡት አራቱ አሜሪካዊ ሲሆኑ አምስተኛው ደግሞ ከህንድ ነው። ቀዳሚዋ ከ 87 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሏት የ 16 ዓመቷ አሜሪካዊት ወጣት ቻርሊ ዴ አሚሊዮ ናት። አምስተኛውን ስፍራ የያዘው ህንዳዊ ደግሞ የ 17 ዓመቱ ሪያዝ አልይ ከ 43 ሚሊዮን በላይ አድናቂዎች አሉት። እነዚህ ወጣቶች አድናቂዎች እና ዝና ብቻ ሳይሆን ያተረፉት በቲክ ቶክ ተሳትፎዋቸው ከሌሎች ትላልቅ ኩባንያዎች ጋር ውል ለመፈራረም እና ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለማግኘት በቅተዋል።  ይህም በርካታ ወጣቶችንን እንደነሱ ታዋቂ ለመሆን አልያም በቲክ ቶክ ገንዘብ ለማግኘት ማነቃቃቱ አልቀረም።
ቲክ ቶክ ላይ ቀልድ እና ማዝናናት ብቻ ሳይሆን ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን የሚያጋሩ ተሳታፊዎችም አሉ። ስለ ኮሮና ተህዋሲ ጠቃሚ  ይሆናሉ የሚሏቸውን መረጃዎች ሀኪሞች እና ነርሶች ይለግሳሉ። ፖለቲከኞች ወጣቱ ያለበት ሄደው መራጮችን ለመሳብ ሲሰሩ ይስተዋላሉ። ጠበቆች ለሚቀርብላቸው ጥያቄ ምላሽ ይሰጣሉ ሌላም ሌላም።
 

ልደት አበበ 

አዜብ ታደሰ