1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለ «ማይካድራ» ጭፍጨፋ የዐይን ምስክሮች

ረቡዕ፣ ኅዳር 2 2013

በምዕራባዊ ትግራይ ሁመራ አቅራቢያ «ማይካድራ» በተባለው አካባቢ የትግራይ ልዩ ኃይል ባልታጠቁ የአማራ ተወላጆች ላይ በሌሊት አሰቃቂ ግድያ መፈፀሙን ከሞት ያመለጠ የዐይን እማኝ ገለፀ። ጥቃቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ሲል ደግሞ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ዐስታውቋል።

https://p.dw.com/p/3lA2s
Karte Äthiopien Region Tigray DE

«ከሌሊቱ 9 ሰዓት ጀምሮ በየቤታቸው እየገባ በግፍ መጨፍጨፉን...»

በምዕራባዊ ትግራይ ሁመራ አቅራቢያ «ማይካድራ» በተባለው አካባቢ የትግራይ ልዩ ኃይል ባልታጠቁ የአማራ ተወላጆች ላይ በሌሊት አሰቃቂ ግድያ መፈፀሙን ከሞት ያመለጠ የዐይን እማኝ ገለፀ። ጥቃቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ሲል ደግሞ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ዐስታውቋል። ድርጊቱ የተጀመረውን ሕግ የማስከበር ሂደት ህወሓት ወደ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲቀየር የዘየደው መላ ነውም ብሎታል። አንዳንድ የአማራ ክልል ነዋሪዎች የህወሓት የተስፋ መቊረጥ ስሜት ነው፤ ኅብረተሰቡ ህወሓት በዘየደው የብቀላ ሂደት እንዳይገባ አሳስበዋል። 

የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ሰሞኑን ሁመራን ከተቆጣጠረ በኋላ ግስጋሴውን ወደ ማይካድራ ባደረገበት ወቅት ህዳር 1 ቀን፣ 2013 ዓ.ም አነጋጉ ላይ የትግራይ ልዩ ኃይል አካባቢውን በኃይል ተገፍቶ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከመልቀቁ በፊት በአካባቢው የነበሩ የአማራ ተወላጅ በሆኑ ነዋሪዎችንና የቀን ሠራተኞችን በእለቱ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ጀምሮ በየቤታቸው እየገባ በግፍ መጨፍጨፉን ከጥቃቱ አምልጦ አሁን አብደራፊ በተባለ ቦታ የሚገኝ የዓይን እማኝ ለዶይቼ ቬለ (DW) በስልክ ተናግሯል፡፡ 
ጥቃቱን ተከትሎ «እየሞትንም ቢሆን እናሸንፋለ» በሚል መግለጫ ያወጣው የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ እንዳለው «በማይካድራ የተፈፀመው ጭፍጨፋ አማራን መሰረት ያደረገ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው» ብሎታል፡፡ 

ድርጊቱ አሁን በትግራይ ክልል ሕግ ለማስከበር የሚደረገውን ትግል የእርስ በርስ ለማስመሰል ያደረገው ስልት ነው ሲልም ከስሷል፡፡ ፓርቲው ለአማራ ክልል ህዝብ ባስተላለፈው መልዕክት «…በተለመደው አስተዋይ ባህሪህ ምስኪኑ የትግራይን ህዝብ እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም ከየትኛውም ጥቃት ጥላ ከለላ ሆነህ ይህን ጊዜ እንድታሳልፈው ይሁን» ብሏል፡፡ 
አንድ የደብረማርቆስ ነዋሪ እንዳሉት ህወሓት ድርጊቱን የፈፀመው በአማራ ክልል በሚኖሩ የትግራይ ወንድሞችና እህቶች ላይ በቀል እርምጃ እንዲወሰድ ያዘጋጀው «ወጥመድ» እንደሆነና የእርስበርስ ግጭት ለመፍጠር እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ 

የእንጅባራ ከተማ ነዋሪውም ቢሆኑ ጥቃቱ የህግ ማስከበሩን ተግባር ወደ የእርስ በርስ ግጭት ለመግፋት የተደረገ ሴራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡  የደሴ ከተማ ነዋሪ እንዳሉት ደግሞ ህብረተሰቡ ራሱን ከስሜት ነፃ አድርጎ ህግ የማስከበሩን ሂደት በጥንቃቄ መከታተል አንዳለበት ጠቁመው ከበቀልና ከጥላቻ እንዲቆጠብ ጠይቀዋል፡፡ 
የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ደጀኔ በስልክ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ህብረተሰቡን ወደ ብስጭት በማስገባት አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡ 

«የአማራና የትግራ ህዝብ ታሪክ የሰራ የተዋለደና ተመሳሳይ ስነልቦና ያለው ህብረተሰብ ነው» ያሉት አቶ ጥላሁን «ትግሉ ህገወጥ ቡድን» ካሉት አካል ጋር እንደሆነ አሰተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በስፍራው የሚገኘው የአማራ ቴሌቪዝን ዘጋቢ ከ100 በላይ የተገደሉ ሰዎችን አስከሬን መመልከቱን ለቴሌቪዥን ጣቢያው ዘግቧል፡፡ 

ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ