1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሳንካ የበዛበት የሶማሊያና የኬንያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 8 2013

ሶማሊያ መንግሥት ከጎረቤት ሀገር ኬንያ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት ማቋረጡን በማስታወቂያ ሚንስትሩ በኩል አስታውቋል።ይህንን ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት ናይሮቢ የሚገኙ ዲፕሎማቶቹ ኬንያ ለቀው እንዲወጡ በሞቃዲሹ የሚገኙ የኬንያ ዲፕሎማቶችም አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የሰባት ቀናት ቀነ ገደብ ተቀምጧል

https://p.dw.com/p/3mpB5
Flagge Somalia
ምስል AFP/Getty Images/Y. Chiba

በደቡባዊ ምስራቅ ሶማሊያ ጁብላን ተብሎ በሚጠራው አውራጃ የቆየ ችግር አለባቸው

።የፖለቲካ ተችዎች ግን ከአልሸባብ ጋር በሚደረገው ትግልና በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የሶማሊያ መንግሥት ከጎረቤት ሀገር ኬንያ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲ ግንኙነት ማቋረጡን በዚህ ሳምንት አስታውቋል።ይህንን ተከትሎ  ሁለቱም መንግስታት ዲፕሎማቶቻቸው ሀገር ለቀው እንዲወጡ ጥሪ አድርገዋል። የማስታወቂያ ምንስቴር ኦስማን አቡካር እንደገለፁት ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መቋረጥ መንስኤው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነው።በዚህ የተነሳ የሶማሊያ መንግስት  ሉዓላዊነትን ለማስከበር እንዲሁም አንድነትና መረጋጋትን ለማስጠበቅ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱን ገልፀዋል።
አለመግባባቱ በሰሚናዊ ሶማሌ  ራሷን እንደ ራስ ገዝ በምትቆጥረው የሶማሌላንድ  ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በናይሮቢ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነውም ተብሏል።
በሌላ በኩልም የኬንያ አዋሳኝ  የሆነችው እና የሶማሊያ ዋናውን ወደብ ኪስማዮን ያካተተው የሶማሊያ ደቡባዊ ግዛት፤  ለጁብላን  ፕሬዝዳንት  አሕመድ ማዶቤ ኬንያ  ድጋፍ ትሰጣለች በሚል  ሶማሊያ  ለረጅም ጊዜ ስትቃወም ቆይታለች።ይህም ለሁለቱ ሀገራት ቁርሾ ሌላው ምክንያት መሆኑን የሁለቱን ሀገሮች ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተሉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ይገልፃሉ።
«ሶማሊያና ኬንያ በተለይ በደቡባዊ ምስራቅ ሶማሊያ  ጁብላን ተብሎ በሚጠራው   አውራጃ  የቆየ ችግር  አለባቸው።ዋና ከተማው ሞቃዲሾ የጁብላንን አስተዳደር አይደግፍም።አንዳንድ ጌዜም አስተዳደሩን ለማጣጣል ይሞክራሉ።የጁብላን ጊዜያዊ ዋና ከተማ ኪስማዮ በጁብላን ሀይሎችና በኬንያ ወታደሮች ነው ጥበቃ የሚደረግለት።የኬንያ ወታደሮች በአፍሪቃ ህብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ አሚሶም ስር ቢሆኑም  በኬንያና በሶማሊያ መካከል ያለው የፖለቲካ ልዩነት ለክርክር አስቸጋሪ ነው።»
ባለፈው ወርም ሶማሊያ የኬንያን አምባሳደር  ከሀገሯ እንዲወጡ አድርጋ የነበረ ሲሆን ያቀረቡት ምክንያትም ከሶማሊያ አምስት ራስ ገዞች ውስጥ አንዷ በሆነችው ጁብላንድ  የምርጫ ሂደት ላይ ኬንያ ጣልቃ ገብታለች የሚል ነበር። የፖለቲካ ተንታኙ ግን ለሁለቱ ሀገሮች አለመግባባት ጁብላን አንዱ እንጅ ብቸኛው ምክንያት አይደለም ይላሉ።
«እንደሚመስለኝ የችግሩ ምንጭ ጁብላን ብቻ አይደለም። ችግሩ በአጠቃላይ ፕሬዚዳንት ፎርማጆ ከሚመሩት ከአሁኑ የሶማሊያ መንግስት   ጋር የተያያዘ ነው።ከአራት አመታት በኋላ የሶማሊያ መንግስት አልሸባብን በመዋጋት ረገድ የሰራው ስራ በጣም ትንሽ ነው።አጠቃላይ ሁኔታዎች እንደሚያሳዩትም የሶማሊያ መንግስት አልሸባብን የመዋጋት ፍላጎትም ሆነ  ቁርጠኝነት ያለው አይመስልም።»
ኬንያ በአፍሪካ ህብረት ለሚመራው ጦር ወታደሮችን በማዋጣት አልሸባብን ለመዋጋት በሚደረገው ዘመቻ የሶማሊያን መንግስት እያገዘች ቢሆንም በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ውጥረት ግን እያደረ መባባሱን የፖለቲካ ተችዎች ይገልፃሉ።ይህም ለአፍሪቃ ቀንድ ስጋት የሆነውን አልሸባብ እንዲጠናከር መንገድ የሚከፍት ነው። በሁለቱ አጎራባች ሀገር ህዝቦች እንቅስቃሴ ላይም የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። 
«በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን የህዝቦች እንቅስቃሴና  ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል።እንደያዙት የፓስፖርት አይነት  ጉዞ  አስቸጋሪ ይሆናል።ከጉዞ  ጋር የተያያዙ ፍተሻዎችና ቢሮክራሲ እንዲጨምር ያደርጋል።ይህም በድንበር አካባቢ የሌላ ሀገር ዜጎችና ሌላ  የጎሳ ማንነት ያላቸው ሰዎች በማንነታቸውና በመጡበት አካባቢ  ሊገለሉ ይችላሉ።» 
በሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች መካከል ከቅርብ ጊዜው ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ በተጨማሪ ቀደም ሲል በጎርጎሪያኑ የካቲት 2019 ዓ/ም ሞቃዲሾ ዘይትና ጋዝ በጨረታ ለመሸጥ መወሰኗን ተከትሎ ኬንያ አምባሳደሯን ከሞቃዲሾ በማስወጣት ግንኙነታቸው ተቋርጦ ነበር። በዚህ ሁኔታ ተቋርጦ የነበረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እንደገና የታደሰው ያለፈው ዓመት ህዳር ነበር።

Somalia Tabda|  Kenianische Soldaten | Militäroffensive
ምስል Ben Curtis/AP Photo/picture alliance
Russland Sochi | Präsident Somalia | Mohamed Abdullahi Mohamed
ምስል Vladimir Smirnov/Imago Images

ከጎርጎሪያኑ 1990 ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ለሞቃዲሾ መንግስት  በአፍሪካ ህብረት ከሚመራው የሰላም አስከባሪ ኃይል ድጋፍ  በተጨማሪ  700 የአሜሪካ ወታደሮች ድጋፍ በማድረግ አልሸባብን ሲዋጉ ቆይተዋል።ከሰሞኑ ግን የአሜሪካ መንግስት ጦሩን ከሶማሊያ ለማስወጣት ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ ማለቱ ይታወሳል።


ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀል