1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሱዳን የውጭ ኃይሎች የትንቅንቅ አውድማ?

ሰኞ፣ ሚያዝያ 28 2011

የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት ከአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት በኩል ሥልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር እንዲያስረክብ ጫና ሲበረታበት ከሳዑዲ አረቢያ እና ከየተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በኩል ድጋፍ አግኝቷል። የዩናይትድ አረብ ኤሚሬቶች ጋዜጦች የሽግግር ምክር ቤቱን የሚመሩ ወታደራዊ ሹማምንትን የሚያሞካሹ ዘገባዎች ያቀርቡ ይዘዋል።

https://p.dw.com/p/3I1FA
Sudan | Protest | Militär in Khartoum
ምስል Reuters/U. Bektas

ወታደራዊው የሽግግር ምክር ቤት ከተቃዋሚዎች ድርድር ላይ ነው

የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት ከአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት በኩል ሥልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር እንዲያስረክብ ጫና ሲበረታበት ከሳዑዲ አረቢያ እና ከየተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በኩል ድጋፍ አግኝቷል። ከሱዳን የተቃውሞ አስተባባሪዎች ጋር ድርድር በማድረግ ላይ የሚገኘው ምክር ቤቱ በነዳጅ ዘይት ከናጠጡት የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት 3 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎለታል። በየመን በጀመሩት ጦርነት የሱዳን ወታደሮችን ከጎናቸው ያሰለፉት እነ ሳዑዲ አረቢያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለሚያንገዳግደው የሱዳን ምጣኔ ሐብት 500 ሚሊዮን ዶላር በፍጥነት ከመስጠታቸው ባሻገር ርካሽ ነዳጅ፣ መድሐኒት እና ምግብ ለማቅረብ ቃል ገብተዋል።

አል-በሽር ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ አቡ ዳቢ ነፍጥ ያነገቡ የሱዳን ተቃዋሚዎች ጭምር የተሳተፉበት እና በአገሪቱ መጪ እጣፈንታ ላይ የሚመክር ውይይት አስተናግዳለች። የዩናይትድ አረብ ኤሚሬቶች ጋዜጦች የሽግግር ምክር ቤቱን የሚመሩ ወታደራዊ ሹማምንትን የሚያሞካሹ ዘገባዎች ያቀርቡ ይዘዋል። ተንታኞች ይኸ ከእነ ሳዑዲ አረቢያ በተቃራኒ የቆሙት ኳታር እና ቱርክ እጃቸውን በሱዳን ጉዳይ እንዲያስገቡ ይጋብዛቸዋል የሚል ሥጋት አላቸው። የከፋው ግን ወታደራዊው የሽግግር ምክር ቤት ሥልጣኑን ለማስረከብ አሻፈረኝ ቢልስ የሚለው ጥያቄ ነው። የብራስልሱ የዶይቼ ቬለ ወኪል ገበያው ንጉሴ ተጨማሪ ዘገባ አለው።

ገበያው ንጉሴ
ነጋሽ መሐመድ