1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሱዳን፦ ዕዳ፣ የዋጋ ግሽበት እና ፖለቲካዊ ሽግግር

ረቡዕ፣ ሐምሌ 21 2013

የጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ መንግሥት እስከ 60 ቢሊዮን ዶላር ከሚደርሰው የሱዳን ዕዳ የተወሰነውን ለማስረዝ ለተቀረው የመክፈያ ጊዜ እፎይታ ለማግኘት ሥምምነቶች ፈጽሟል። የሱዳን መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በገባው ውል ተግባራዊ የሚያደርጋቸው ማሻሻያዎች የአገሪቱን የመገበያያ ገንዘብ እያዳከመ የዋጋ ግሽበትም እያስከተለ ነው

https://p.dw.com/p/3yCfU
Sudan Khartum | Anti-Regierungsproteste
ምስል Ashraf Shazly/AFP/Getty Images

ከኤኮኖሚው ዓለም ሱዳን፦ ዕዳ፣ የዋጋ ግሽበት እና ፖለቲካዊ ሽግግር

ከ30 አመታት የኦማር አል-በሺር አምባገነናዊ አገዛዝ በኋላ የሱዳን ሲቪል ፖለቲከኞች በአገራቸው ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ውሳኔዎች የሚሳተፉበት ዕድል አገኙ። ሲቪሎቹ ከወታደሮቹ ፊት ለፊት ተቀምጠው በመደራደር የሽግግር መንግሥቱን ሥልጣን ተካፈሉ። ለወራት አል-በሺርን የተቃወሙ ለውጡ ተስፋ የሚጥሉበት ነበር። ከሱዳን ርቃ የምትኖረው አሲል ዲያብ በዚህ ጊዜ ወደ ትውልድ አገሯ ተመልሳ ተስፋ ጠባቂዎቹን ተቀላቀለች። ኦማር አል-በሺር፣ ፓርቲያቸው እና መንግሥታቸው ላይመለሱ ቢሰናበቱም ሥልጣን ላይ በነበሩ አመታት ለተፈጠሩ ምስቅልቅሎች መልስ ከሚጠብቁት እንዷ አሲል ነበረች። በተለይ ሶስት አስርት አመታት ሥልጣን ላይ በቆየው መንግሥት ሕይወታቸውን ያጡ የሱዳን ዜጎች ጉዳይ ለበርካቶች አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

አሲል ዲያብ "ሰማዕታቱ ዛሬም ፍትኅ እየጠበቁ ነው። በርካታ የሰማዕታት ቤተሰቦችን አነጋግሪያለሁ። ሁሉም የሚሉት ተመሳሳይ ነገር ነው። ፍትኅ የለም። እንዴት እና መቼ ፍትኅ እንደሚያገኙ ከመንግሥት ማብራሪያ አልተሰጣቸውም። ነገሩ ሁሉ ድፍንፍን ያለ ነው። አብዛኞቹ ቤተሰቦች ተስፋ ቆርጠዋል። ከሁለት አመት በኋላ እንኳ መንግሥት ለሰማዕታቱ ቤተሰቦች በዚህ ቀን ምስክርነታችሁን እንሰማለን፤ ወይም በዚህ መንገድ ካሳ ታገኛላችሁ አልተባሉም" በማለት ከለውጡ በኋላ የተፈጠረውን የተስፋ መቁረጥ ስሜት ታስረዳለች። 

ይኸ አሲል ዲያብ የጠቀሰችውን የፍትኅ ጥያቄ ጨምሮ በሱዳናውያን ዘንድ የበረታ ቅሬታ ባለፈው ሰኔ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በኻርቱም ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ዜጎች የሽግግር መንግሥቱ ሥልጣን እንዲለቅ እስከ መጠየቅ አድርሷቸዋል። ከተቃዋሚዎቹ አንዱ የሆነው መሐመድ አሕመድ አል-ሐጅ የኤኮኖሚ ባለሙያው አብደላ ሐምዶክ የሚመሩት መንግሥት የፈየደው ነገር የለም ሲል ይወቅሳል።  

Sudan Omdurman | Anti-Regierungsproteste
የሱዳን ተቃዋሚዎቹ ካነሷቸው የፍትኅ እና የፖለቲካ ጥያቄዎች ባሻገር በሺር ከሥልጣን ካወረዱ ምክንያቶች አንዱ የሆነው የሱዳን ኤኮኖሚ ጉዳይ ይገኝበታል። ምስል Enbrahim Hamid/AFP/Getty Images

መሐመድ አሕመድ አል-ሐጅ "የመጀመሪያው ጥያቄያችን የሐምዶክን [ጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ] መንግሥት ከሥልጣን ማውረድ ነው። ምክንያቱም መንግሥቱ ከተመሰረተ ጀምሮ ፈተና እንጂ ምንም የተረፈን ነገር የለም። በየቀኑ ካለፈው የበለጠ እንሰቃያለን። የመጀመሪያው ዓላማችን የሐምዶክን መንግሥት ማውረድ ነው። ዛሬ ለተቃውሞ ወጥተናል፤ ነገም ከነገ ወዲያም የሐምዶክ መንግሥት እስኪወድቅ ይኸንንው እናደርጋለን" በማለት ተናግሯል። 

ተቃዋሚዎቹ ካነሷቸው የፍትኅ እና የፖለቲካ ጥያቄዎች ባሻገር በሺርን ከሥልጣን ካወረዱ ምክንያቶች አንዱ የሆነው የሱዳን ኤኮኖሚ ጉዳይ ይገኝበታል። በተለይ ኤኮኖሚውን ለመታደግ የሽግግር መንግሥቱ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በተስማማው መሠረት ተግባራዊ ያደረጋቸው ማሻሻያዎች የዋጋ ግሽበት ማስከተላቸው አመል አብደላን የመሳሰሉ ዜጎች የሚቀበሉት አይደለም። 

"መጀመሪያ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትን ፖሊሲ እንቃወማለን። ምክንያቱም መንግሥት ዋጋ እየጨመረ በመሆኑ ዜጎች ሊቋቋሙት አልቻሉም" የምትለው  አመል አብደላ "ሁለተኛ ነፃነት፣ ሰላም እና ፍትኅን ማረጋገጥ እንፈልጋለን። እስካሁን አንዳቸውንም አላየንም። እየተደረገ ያለው ነገር ሕዝቡን ዝም ማሰኘት ብቻ ነው" እያለች የሽግግር መንግሥቱን ትወቅሳለች።  

የሱዳን ዕዳ እና ፋታ ፍለጋ

እነ አመል አብደላ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡበት ሳምንት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለሱዳን 2.5 ቢሊዮን ዶላር ወይም 2.1 ቢሊዮን ዩሮ ብድር የፈቀደበት ነበር። ለ39 ወራት በሚዘልቀው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተራዘመ የብድር አቅርቦት (Extended Credit Facility) መርሐ-ግብር ሱዳን 1.4 ቢሊዮን ዶላር አፋጣኝ የገንዘብ አቅርቦት እንድታገኝ ያግዛታል። 

ውሳኔው የተላለፈው ሱዳን ያለባትን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 1.4 ቢሊዮን ዶላር ውዝፍ ዕዳ ከከፈለች በኋላ ነው። በዚህም በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በኩል እና በዓለም ባንክ ከፍተኛ ብድር የበረታባቸው አገራት እገዛ መርሐ-ግብር (Heavily Indebted Poor Countries Initiative) የዕዳ ክፍያ ፋታ ታገኛለች። በተለይ የዓለም ባንክ መርሐ-ግብር 56.6 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚገመተውን የውጭ ብድር በሶስት አመታት ውስጥ ወደ 6 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ለማድረግ እንደሚረዳት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለፈው ሰኔ መጨረሻ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል። 

ሱዳን ያለባትን ዕዳ በመክፈል ረገድ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከፍ ያለ ሚና ተጫውቷል። ወደ 22 የሚጠጉ አባላት ያሉት የፓሪስ ክለብ አበዳሪዎች ሱዳን ካለባት 23.5 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ውስጥ 14.1 ቢሊዮን ዶላር ሰርዘዋል። የፓሪስ ክለብ አበዳሪዎች ኃላፊ እና የፈረንሳይ ግምዣ ቤት ዳይሬክተር ኤማኑዌል ሙሊን እንዳሉት የተቀረውን 9.4 ቢሊዮን ዶላር ለመክፈል ሱዳን የእፎይታ ጊዜ አግኝታለች። የፓሪስ ክለብ አበዳሪዎች ባወጣው መግለጫ ሱዳን ባላት ውስን የመክፈል አቅም ምክንያት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የሚደገፉ መርሐ-ግብሮችን በቅጡ ተግባራዊ ማድረጓን ከቀጠለች እስከ ሕዳር 2017 ዓ.ም. ድረስ ክፍያ አይጠበቅባትም።  ይሁንና የመክፈያ ጊዜ ማስተካከያ የተደረገበት ቀሪ ብድርም ቢሆን ወደፊት ሊሰረዝ እንደሚችል ኤማኑዌል ሙሊን ጥቆማ ሰጥተዋል።

በግንቦት ወር ሱዳን በይፋ ወደ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መቀላቀሏን ለማብሰር ኮንፈረንስ ያዘጋጀችው ፈረንሳይ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የመሸጋገሪያ ብድር ለመስጠት ፈቃደኛነቷን ገልጻለች። ጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ በተሳተፉበት በዚህ ኮንፈረንስ ፕሬዝዳንት ኤማኑዌል ማክሮ ሱዳን ያለባትን 5 ቢሊዮን ዶላር የፈረንሳይ ዕዳ አገራቸው መሰረዟንም ይፋ አድርገዋል። አሜሪካ እና ብሪታኒያን ጨምሮ በኮንፈረንሱ የታደሙ ሌሎች አገራትም ሱዳን ያለባትን የዓለም የገንዘብ ድርጅት ውዝፍ ዕዳ ለመሰረዝ ተስማምተዋል። 

Sudann Khartum Soldaten Protest
አል በሺር፣ ፓርቲያቸው እና የቅርብ ሰዎቻቸውን ከሥልጣን ያወረደው የሱዳን ለውጥ በአገሪቱ ዜጎች ዘንድ ተጨባጭ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካው መሻሻል እንዲያመጣ ይጠበቃል።ምስል Reuters

ይኸ ግን እስከ 60 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል የሚባለውን የሱዳን ዕዳ ለማቃለል በቂ አይመስልም። የናጠጡ የባሕረ ሰላጤው የአረብ አገራት ካበደሯት 30 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብ እስከ 60 በመቶ የሚሆነውን እንዲሰርዙ ትፈልጋለች። የሱዳን የፋይናንስ ምኒስትር ገብርየል ኢብራሒም አገራቸው ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ኩዌት ያበደሯትን ገንዘብ የመክፈያ ጊዜ ለተጨማሪ አስራ ስድስት አመታት እንዲያራዝሙ እንደምትጠይቅ ተናግረዋል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የአሜሪካ ሹማምንት ሱዳን ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በገባችው ውል መሠረት ገቢራዊ ያደረገቻቸውን ኤኮኖሚ ማሻሻያዎች በተደጋጋሚ ሲያበረታቱ ታይተዋል። የጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ሐይኮ ማስ አገራቸው ከጅማሮው ድጋፍ ማድረጓን ባሳወቁበት መግለጫ "የተጀመረው ፖለቲካዊ እና የኤኮኖሚ ማሻሻያ አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ለሱዳን ሕዝቦች ሰላም፣ ኤኮኖሚያዊ መሻሻል እና ነፃነት ታሪካዊ ዕድል ተስፋ ፈንጥቋል" ብለዋል። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኤማኑዌል ማክሮ "ፈተናዎች ቢኖሩም የቀደመው ሥርዓት ከወደቀ በኋላ ትርጉም ያለው መሻሻል ተደርጓል" በማለት ጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ በሚመሩት የሽግግር መንግሥት ተስፋ መሰነቃቸውን ጠቁመዋል። የዓለም የገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ክሪታሊና ጂዮርጂዬቫም ሱዳን እና ታይተዋል ያሏቸውን መሻሻሎች ከማድነቅ አላፈገፈጉም። 

ክሪታሊና ጂዮርጂዬቫ "ሱዳንን ካለፈው መንግሥት ከተቀበለችው ግዙፍ የዕዳ ጫና ነፃ ማውጣት እና መጪውን ጊዜ ለመገንባት ከልማት አጋሮች አዲስ ገንዘብ ማግኘት ትልቅ ስኬት ነው። እዚህ የደረስንው በጋራ ነው። ሱዳን ቁልፍ የኤኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ስታደርግ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ብድር ያለባቸው አገራት ዕገዛ መርሐ-ግብር ይፋ ከሆነ ወዲህ ከፍተኛ የሆነውን የዕዳ ማስተካከያውን በመደገፍ ሰርተዋል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከሱዳን ሕዝቦች በተለይ የአገራቸውን ታሪካዊ ሽግግር የመሩት ወጣቶች እና ሴቶች ርዕይ በተጣጣመ መንገድ ለሱዳን የኤኮኖሚ መነቃቃት ሰርተናል፤ መስራታችንንም እንቀጥላለን" ሲሉ ተናግረዋል። 

የሱዳን ኤኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ጣጣ

ይኸ የጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የልማት አጋሮቹ ጋር የጀመረው የኤኮኖሚ ማሻሻያ ግን ጣጣ ማስከተሉ አልቀረም። በግንቦት ወር 378.79% የነበረው የዋጋ ግሽበት በሰኔ ወደ 412.75% ከፍ ማለቱን የጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ መንግሥት ይፋ አድርጓል። የምግብ ግብዓቶችን ጨምሮ የሸቀጦች ዋጋ በተጠቀሰው ጊዜ ጭማሪ እንዳሳዩ የሱዳን መንግሥት የሚቆጣጠረው የዜና ወኪል ዘግቧል። የዋጋ ግሽበቱ በሚያዝያ ወር 363% ነበር። 

አገሪቱ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በገባችው ግዴታ መሠረት የመገበያያ ገንዘቧ የምንዛሪ ተመን በተከታታይ እየተዳከመ ነው። የሱዳን የፋይናንስ ሚኒስቴር ባለፈው ወር መጀመሪያ ለቤንዚን እና ነዳጅ ግብይት የሚደረገውን ድጎማ ማቆሙንም አስታውቋል። እነዚህ ተደማምረው የሱዳን ምጣኔ ሐብታዊ ሁኔታ የአገሪቱ ዜጎች ትከሻ ከሚሸከመው በላይ ሆኗል። በሺር በሥልጣን በነበሩባቸው ረዥም አመታት ተጥለውባት በነበሩ ማዕቀቦች ሳቢያ ኤኮኖሚው ቀድሞም በኃይል ተጎድቷል።

ሱዳን የተጣለባት ማዕቀብ ተነስቶ ወደ ዓለም አቀፉ ገበያ በይፋ ብትቀላቀልም ትሩፋቱ ለተራው ሱዳናዊ ለመድረስ እጅግ የዘገየ ይመስላል። በዚያ ላይ የኮሮና ወረርሽኝ በአገሪቱ ላይ ብርቱ ጫና አሳድሯል። አሲል ዲያብ እንደምትለው "ሰዉ ሰልችቶታል።" አሲል ዲያብ "ግማሽ ቀን ኤሌክትሪክ ይቋረጣል፤ ለመኪኖች ነዳጅ የለም፤ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ መኖር ሰዉ ሰልችቶታል። ተስፋ የተጣለበት ለውጥ ከመጣ ብዙ ጊዜ አለፈ። ስለዚህ ተስፋ ያስቆርጣል" ብላለች። 

የሱዳን ሽግግር የሲቪል መንግሥቱን በሚመሩት ጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ እና በሉዓላዊ ምክር ቤቱ ሊቃነ-መናብርት እጅ ይገኛል። የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀ-መንበር ሉቴናንት ጄኔራል አብዱል ፋታኅ አል-ቡርኻን እና ምክትላቸው ሉቴናንት ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ምርጫ እስኪካሔድ በመንግሥቱ ውስጥ የቁልፍ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው። ከሶስት አመታት በፊት ወታደራዊ ባለሥልጣናቱ እና ሲቪል ፖለቲከኞች በደረሱበት ሥምምነት መሠረት የሽግግር መንግሥቱ ሥልጣን ከመጠናቀቁ በፊት የሱዳንን የምርጫ ሥርዓት እና መንግሥት ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት የሚደነግግ ቋሚ ሕገ-መንግሥት መዘጋጀት ይኖርበታል። ከዚያ በጎርጎሮሳዊው 2022 መገባደጃ ምርጫ ይካሔዳል።

Südsudan Juba | Sudan und Rebellengruppe unterzeichnen Abkommen zur Trennung von Religion und Staat
የሱዳን የሽግግር መንግሥት በጁባ የፈረመው የሰላም ሥምምነት አብደልአዚዝ አል ሒሉን ከመሳሰሉ የተቃውሞ መሪዎች ጋር የተፈጸመ ነው። ምስል Jok Solomun/REUTERS

የፖለቲካ ተንታኞችም ሆኑ የኻርቱም ፖለቲካን በአይነ ቁራኛ የሚከታተሉ ምዕራባውያን አገሮች ሽግግሩ ከታሰበው ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ሳይደርስ እንዳይንገራገጭ ሥጋት አላቸው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ  "ሱዳን የዴሞክራሲ ሽግግሯን እንድታጠናክር፤ ኤኮኖሚዋን መልሳ እንድትገነባ፣ ለመላ ሕዝቧ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን እንድታረጋግጥ የማገዝ ኃላፊነት አለብን። አስቸጋሪ የኤኮኖሚ ማሻሻያዎች ገቢራዊ በማድረጉ የሱዳን መንግሥትን አደንቃለሁ። እነዚህ ለአገሪቱ ብርታት እና መሻሻል ጅማሮ ናቸው። የሱዳን ሕዝቦች ለረዥም አመታት ተሰቃይተዋል። የጁባ የሰላም ስምምነትን ከፈረሙ እና ካልፈረሙ ወገኖች ጋር ሰላም ለማውረድ የሚያደርገውን ጥረት፤ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ባለው ቁርጠኝነት እና የሲቪክ ምህዳሩን በማስፋቱ እንዲሁም ለዜጎቹ አካታችነትን በማረጋገጡ ጭምር የሱዳንን መንግሥት ማድነቅ እፈልጋለሁ" ሲሉ ተናግረዋል። 

ዋና ጸሐፊው "ሱዳን በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ያለባትን ውዝፍ ዕዳ እንድታሰርዝ ዕገዛ ያደረጉ አገሮችን አመሰግናለሁ። ከሱዳን ወዳጆች እና አጋሮች ቀጣይ እገዛ አስፈላጊ ነው። የገንዘብ እገዛ እና መዋዕለ ንዋይ ለሱዳን ካልደረሱ ችግር ውስጥ የወደቀው ኤኮኖሚያዊ ሁኔታ የአገሪቱ ሽግግር ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ይኸ በሱዳን በቀጣናው እና ከዚያም ባሻገር በሰላም እና መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል" የሚል ማስጠንቀቂያም ሰጥተዋል። 

እሸቴ በቀለ 
ሸዋዬ ለገሰ