1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሱዳን ከአሸባሪዎች መዝገብ በይፋ የመሰረዟ ፋይዳ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 10 2013

ከፍረጃው በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ በሱዳን ላይ የጣለችው የኤኮኖሚ ማዕቀብና የወሰደቻቸው ልዩ ልዩ አግላይ እርምጃዎች የሱዳንን ኤኮኖሚ ጎድተዋል። ከመካከላቸው በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ላይ ያሳደረው ከፍተኛ ተጽእኖ አንዱ ነበር። የሰኞው ውሳኔም ሃምዶክ እንዳሉት ሃገሪቱን እንዳትራመድ ላደረጋት ለዚህ ችግር መፍትሄ አስገኝቷል። 

https://p.dw.com/p/3mwUX
Sudan Khartum US-Außenminister Pompeo und Abdalla Hamdok
ምስል Sudanese Government/Saudi Press Agency/picture-alliance

ሱዳን ከአሸባሪዎች መዝገብ በይፋ የመሰረዟ ፋይዳ

ዩናይትድ ስቴትስ በዚህ ሳምንት ሰኞ፣ ሱዳንን አሸባሪዎችን ከሚደግፉ መንግሥታት ዝርዝር ውስጥ በይፋ መሰረዟ የሱዳን መንግሥትንና ህዝቡን አስደስቷል።ውሳኔው እንቅፋት በበዛበት የፖለቲካ ሽግግር ውስጥ ለምትገኘው ለሱዳን ትልቅ እፎይታ አስገኝቷል። ዩናይትድ ስቴትስ ሱዳንን ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በአሸባሪዎች መዝገብ በመስፈሯ ሃገሪቱ ከዓለም ተገላ ቆይታለች። የዛሬ 27 ዓመት ለሱዳን «የሰይጣን ዛቢያ» መነኻሪያ ብላ ስም ያወጣችላት  አሜሪካን ከሱዳን ጋር መወዳጀት የጀመረችው ፣በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸው የቀድሞው የሱዳን መሪ ኦማር አልበሽር በህዝባዊው አብዮት ከሥልጣን ከወረዱና ከታሰሩ በኋላ ነው። ከአብዮቱ በኋላ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አብደላ ሃምዶክ ውሳኔውን፣ በሱዳን እስከዛሬ የነበረውን ሁኔታ የሚቀይርና የተለየና አዲስ ሁኔታ የሚፈጥር ሲሉ አወድሰውታል። ዋነኛ ጠቀሜታዎቹን በመግለጽም ውሳኔውን ሱዳንን ከመገለሏ በፊት ወደነበረችበት ሁኔታ የሚመልስ ብለውታል።
« ውሳኔው ወደ ዓለም አቀፍ የባንክ ስርዓት ውስጥ መመለስን ያካትታል።በዚህ ጊዜ ከዓለም ተገለን ነበር።በመላ ሃገሪቱ ዓለም አቀፍ ግንኙነት የነበረው ባንክ አንድ ብቻ ነበር።አሁን እየተመለስን ነው።ይህ በሌለበት ከ60 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሱዳንን የእዳ ችግር መፍታት አልቻልንም።»
ሃምዶክ እንዳሉት ከዚህ ከጎርጎሮሳዊው 1993 ቱ የዩናይትድ ስቴትስ እርምጃ በፊት ሱዳን ለረዥም ጊዜ ምንም ዓይነት እርዳታም ሆነ ስጦታ የማያስፈልጋት ሃብታም ሃገር ናት ተብሎ ነበር የሚታሰበው።ይሁንና ከፍረጃው በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ በሱዳን ላይ የጣለችው የኤኮኖሚ ማዕቀብና የወሰደቻቸው ልዩ ልዩ አግላይ እርምጃዎች የሱዳንን ኤኮኖሚ ጎድተዋል።
ከመካከላቸው በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ላይ ያሳደረው ከፍተኛ ተጽእኖ አንዱ ነበር። የሰኞው ውሳኔም ሃምዶክ እንዳሉት ሃገሪቱን እንዳትራመድ ላደረጋት ለዚህ ችግር መፍትሄ አስገኝቷል። 
«ይህ እርምጃ ኢንቬስትመንትን ወደ ሃገሪቱ መልሶ ለማምጣት በሩን ይከፍታል።የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችም ወደ ሌላው ዓለም እንዲሄዱ፤ቴክኖሎጂም እንዲገባ ያስችላል።ከሁሉም በላይ ውሳኔው እኛን፣ ከህዝባዊው አብዮት በኋላ ለብዙ ዘመናት በውጭ ከሚኖሩ ሱዳናውያን ጋር እንድንገናኝ ያስችለናል። እነርሱ እርዳታ በመስጠትና ለሱዳን ህዝብ ማድረግ የሚችሉትን በማድረግ ሊረዱን ሞክረዋል።በፍረጃው ምክንያት ግን የተከማቸውን በርካታ ሃብታቸውን ወደ ሃገር ቤት ለማምጣት ያደረግናቸው ሙከራዎች አልተሳኩም።» 
አሜሪካን ሱዳንን ከአሸባሪነት ዝርዝር ማስወጣቷ ለሃገሪቱ ኤኮኖሚያዊ ጥቅም ብቻ አይደለም የሚያመጣው ።ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል መኮንን በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር እንደተናገሩት ሱዳን ከኤኮኖሚው በተጨማሪ በፖለቲካውና በዲፕሎማሲው መስክም ብዙ ታተርፋለች።በርሳቸው አስተያየት ጥቅሙ ለሱዳን ብቻም  አይደለም።
ዋሽንግተን ሱዳንን ከአሸባሪነት መዝገብ እንደምትሰርዛት ካሳወቀች ከ45 ቀናት በኋላ ነው በይፋ ከዝርዝሩ እንድትወጣ ያደረገችው።በሁለቱ ሃገራት ስምምነት መሰረት ሱዳን ከአሸባሪነት መዝገብ  እንድትፋቅ 335 ሚሊዮን ዶላር ከፍላለች።ሰኞ እንዳሳወቀችው በጎርጎሮሳዊው 1998 ናይሮቢ ኬንያና ዳሬሳሌም ታንዛኒያ በሚገኙ የዩናይትድስቴትስ ኤምባሲዎች በተጣሉ ጥቃቶች ለተገደሉ ቤተሰቦች ካሳ ይሰጣል የተባለውን ይህን ገንዘብም ባንክ አስገብታለች።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደፈለጉትም ለእስራኤል እውቅና ሰጥታለች።ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል እንደሚሉት በእነዚህ የሱዳን እርምጃዎች ዩናይትድ ስቴትስና እሥራኤልም ተጠቃሚ ሆነዋል። 
የአሜሪካን ውሳኔ ሱዳናውያንን አስደስቷል።ውሳኔው ለሃገራቸው  ኤኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያስገኝ ብቻ ሳይሆን እርምጃው በህዝቡ ላይ ያሳደረውን ስሜት በመቀየር ረገድም ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ያምናሉ።ለስፖርት ጋዜጠኛው አሊ አደም ሃመድ አቡና ኤኮኖሚያዊው ጥቅም ይጎላል።     
«እንደ ሱዳናዊ ጥሩ ነገር ነው የተሰማኝ። ውሳኔው የሱዳንን ኤኮኖሚ ለማሳደግ ይረዳል።ሱዳንን አሸባሪዎችን ከሚደግፉ ሃገራት ዝርዝር ውስጥ በማውጣት ብዙ ውረታዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ እና ከዚህ ቀደም ሱዳን ውስጥ መሥራት የማይችሉ በርካታ የአሜሪካንና የሌሎች ሃገራት ኩባንያዎች እዚህ መሥራት ይችላሉ።የሱዳን ኤኮኖሚም፣ በኩባንያዎቹ እዚህ መግባት ይጠቀማል።»
መካኒካል መሀንዲሱ አል ቡሻሪ ሙሳ በውሳኔው ቢደሰትም ኤኮኖሚውን የማነቃቃቱ ድርሻ ግን የሱዳን ህዝብ ነው ይላል።
«በርግጥ ዩናይትድ ስቴትስ ሱዳንን አሸባሪዎችን ከሚረዱ ሃገራት ዝርዝር ውስጥ ማስወጣቷ ለማንም ሱዳናዊም ሆነ ለሃገሩቱ መልካሙን ሁሉ ለሚመኝ የደስታ ምክንያት ነው።ሆኖም የኔ አመለካከት የተለየ ነው።እንደሚመስለኝ ኤኮኖሚውን የመቀየር አቅሙ በሱዳን ህዝቦች እጅ ውስጥ ነው ያለው።አሁን እድሉ እጃችን ገብቷል።»
ለህክምና ተማሪዋ ሱሃ አናስ ደግሞ ትልቁ ነገር የሃገርዋ ከአሸባሪነት ዝርዝር መሰረዝ ሌሎች ስለ ርስዋ ያላቸውን አመለካከት በመቀየር ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ነው 
«እንደሚመስለኝ ከአሁን ወዲያ ሰዎች እኔን ቢያንስ አሸባሪ ናት ብለው አያስቡም።ምክንያቱም እኔ ሌሌችም ነገሮች ነኝ።ሙስሊም ነኝ እንደዚያ ነው የሚመለከቱን ።እኔ ከየትም ልምጣ ሃይማኖት ይኑረኝም አይኑረኝ በሰብዓዊነት  ነው የማምነው ።»
ሱዳን ፣ዩናይትድ ስቴትስን 335 ሚሊዮን ዶላር ክሳ ለእስራኤልም እውቅና ሰጥታ ዓለም አቀፉ ግንኙነቷን ማሻሻሏ ለሰላምና  መረጋጋትዋ እንዲሁም ለወደፊት እድገቷ ዋስትና ይሆን? የተሻሻለው የሱዳንና የእስራኤል ግንኙነትስ ለሱዳን ፋይዳ አለው። ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል መኮንን
ሱዳን ከዩናይትድ ስቴትስ የአሸባሪዎች መዝገብ በይፋ የመሰረዟን ፋይዳ ያስቃኘን የዛሬው ትኩረት በአፍሪቃ በዚሁ አብቅቷል።
ኂሩት መለሰ

Fahnen Israel - Sudan NAH
ምስል Jack Guez/AFP/Getty Images
Sudan Premierminister Abdalla Hamdok
ምስል Hannibal Hanschke/Reuters
USA | Sudan-Israel-Beziehung | US-Präsident Donald Trump
ምስል Alex Edelman/AFP/Getty Images

ልደት አበበ