1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ፖለቲካዊ ቀዉስና የዉጪዉ ኃይል

ሰኞ፣ ሰኔ 24 2011

ከኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር እስከ ዩናይትድ ስቴትሱ ረዳት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የሞከሩት ሽምግልና ቢያንስ እስካሁን ገቢር ያልሆነዉ በተቃዋሚዎቹ ሳይሆን በጦር ጄኔራሎቹ እንቢተኝነት ነዉ።«የጄኔራሎቹ አላማ ሰበብ አስባብ እየፈጠሩ በስልጣን ላይ መቆየት ነዉ።»

https://p.dw.com/p/3LQ7a
Sudan Khartum Massenproteste der Opposition
ምስል AFP

ሱዳን፣ ቱኒዚያን ትሆን ወይስ ሊቢያን?

የቀድሞዉ የሱዳን ፕሬዝደንት ዑመር ሐሰን አል በሽር በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙበትን 30ኛ ዓመት ኮባር እስር ቤት ሆነዉ ትናት ዘከሩት።አል-በሽር የዛሬ 30 ዓመት የመሩና ያቀነባበሩት መፈንቅለ መንገስት «ደም ያልፈሰሰበት» እንደነበረ ሁሉ፣ባለፈዉ ሚያዚያ ከስልጣን የተወገዱበት መፈንቀለ መንግስትም ደም አልፈሰሰበትም ነበር።ሱዳን ግን ዛሬም እንደ ዛሬ 30ዓመቱ ድርድር እየተጀመረ እንደከሸፈባት፣ የሰላም ቃል እየተገባ እንደታጠፈባት፣የዉጪ ኃይላት ግራ-ቀኝ እንዳላጓት፣ በአደባባይ ሠልፍ እንደተጮኸባት ከሁሉም በላይ ዜጎችዋ እንደተገደሉ፤ እንደቆሰሉ፣ እንደታሰሩባት ቁልቁል ትነጉዳለች።የሰሞኑ ምስቅልቅሏ መነሻ፣ የኋላ ዳራዋ ማጣቀሻ፣የዉጪዎቹ ጣልቃ ገብነት  መድረሻችን ነዉ።

የሱዳን ሕዝብ ሐገሪቱን የሚገዛዉ ወታደራዊ ሁንታ ስልጣን እንዲለቅ ባደባባይ ሰልፍ ይጠቃል።ሲቢሊዊ አስተዳደር እንዲመሠረት ያሳስባል።ለተቃዉሞ እንደተሰለፉ የተገደሉ ወገኖቹ ደም በከንቱ እንደማይቀር ይፈክራል።ለፍትሕ ልዕልና፣ ለሰላም ስርፀት ለተጨማሪ ትግልም ይጮኻል፣ ሙታንን ይዘክራልም።

«እዉነቱን ለመናገር የተገደሉት ሰዎች ከኔ የተሻሉ አይደሉም።የእነዚያ ስዉዓን ሞት በሁላችንም ጫንቃ ላይ ነዉ።ልንረሳቸዉ አንችልም፣ ላንዲት ደቂቃም ቢሆን (ከትግሉ) አናፈገፍግም።እንደነሱ ካልተገድልን ፍትሕ እንዲያገኙ እንታገላለን»

ትላለች እሷ።ሰሚ ያጣ ጩኸት፤ አድማጭ የለሽ መልዕክት።

ግድያዉም ቀጥሏል።ከትናንት ጀምሮ በመላዉ የሱዳን ታላላቅ ከተሞች አደባባይ የወጣዉን ሕዝብ ለመበተን ፀጥታ አስከባሪዎች በከፈቱት ተኩስ እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ 10 ሰዎች መገደላቸዉ ተዘግቧል።እስከ ትናንት ድረስ ሰባት ሰዎች መገደላቸዉን ገዢዉ ወታደራዊ ሁንታ አምኗል።ከ200 በላይ ቆስለዋል።ለግድያ-ጉዳቱ ግን ከዚሕ ቀደም እንደሚለዉ ሁሉ ሰልፉን ያደጁትን ወገኖች ተጠያቂ አድርጓል።

ሰልፈኛዉን ይገድላል ተብሎ የሚወቀሰዉ ፈጥኖ ደራሽ ጦር (RSF) አዛዥ እና የወታደራዊ ሁንታዉ ምክትል ሊቀመንበር ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሐምዲቲ) ትናንት እንዳሉትማ የጥፋት «መልዕክተኞች» ያሏቸዉ ኃይላት ጦራቸዉን ጭምር እያጠቁ ነዉ።«የወታደሮቹ ተልዕኮ ተቃዉሞ ሰልፈኞችን ከጥቃት መከላከል ነዉ።አጥፊዎችን ግን አናምንም።ባሁኑ ወቅት እንኳን ከወጣቶች ማዕከል እና ከዋናዉ የሕክምና መስሪያ ቤት ፊትለፊት ነጥሎ ገዳዮች መሽገዋል።በሰዎች ላይ ይተኩሳሉ።ሶስት የፈጥኖ ደራሽ ጦር ባልደረቦችና አምስት ወይም ስድስት ሲቢሎችን መትተዋል።»

የፖለቲካ ተንታኝ የሱፍ ያሲን እንደሚሉት ቀድሞዉ የጃንጃዊድ መሪ የሚሉትን ማመን አይቻልም።ግራ-አጋቢ ተቃራኒም ነዉና።ከዚሕም በላይ ጄኔራሉ እንዳሉት የሚያዙት ጦር እንደማንኛዉም ሰልፈኛ በአነጣጥሮ ተኳሾች ከተጠቃ ሰልፈኛዉን ቀርቶ እራሱንም ከጥቃት መከላከል አይችልም ማለት ነዉ።እነ ጄኔራል ዳዳሎ የሚመሩት ወታደራዊ ሁኑንታ እንደ ግድያ-ተቃዉሞዉ ሁሉ የሰፊይቱን አፍሪቃዊት ሐገር አጠቃልይ ፖለቲካም እያመሰቃቀለዉ ነዉ።

ከዚሕ ቀደም ኢትዮጵያ ያቀረበችዉን የሽምግልና ሐሳብ እንደሚቀበለዉ አስታዉቆ ከተቃዋሚዎቹ ጋር ያቋረጠዉን ድርድር ለመጀመር ዝግጁ መስሎም ነበር።እስካሁን ግን ድርድር የሚባል ነገር የለም።የኢትዮጵያ አደራዳሪዎችን በስልክ ለማነጋገር ሞክረን ነበር።«ሥራ ይበዛብናል» በሚል ምክንያት ለዛሬ አስተያየታቸዉን ሊሰጡን አልቻሉም።ወይም አልፈለጉም።የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት ግን ከኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር እስከ ዩናይትድ ስቴትሱ ረዳት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የሞከሩት ሽምግልና ቢያንስ እስካሁን ገቢር ያልሆነዉ በተቃዋሚዎቹ ሳይሆን በጦር ጄኔራሎቹ እንቢተኝነት ነዉ።«የጄኔራሎቹ አላማ ሰበብ አስባብ እየፈጠሩ በስልጣን ላይ መቆየት ነዉ።» ይላሉ

የወታደራዊ ሁንታዉ ምክትል ሊቀመንበር ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ግን ወታደራዊ ምክር ቤታቸዉ አሁንም ለድርድ ስምምነት ዝግጁ ነዉ ይላሉ።ገለልተኛም ጭምር።

«ስምምነት ላይ መድረስ እንፈልጋለን።ከሁሉም ጋር አጠቃላይ ስምምነት ማድረግ እንፈልጋለን።እኛ የወታደራዊ ምክር ቤት አባላት ገለልተኞች ነን።የአብዮቱ ጠባቂዎች ነን።የዉዝግቡ አካል መሆን አንፈልግም።»

ሱዳን። የግራ-አጋቢ ጄኔራሎች ሐገር።ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ መፈንቅለ መንግሥትና የጦር ጄኔራሎች አገዛዝ ተለይቷት የሚያዉቀዉ ለአጫጭር ጊዜያት ብቻ ነዉ።በየዘመኑ ቀዳሚያቸዉን እያስወገዱ ሥልጣን የሚይዙ የጦር መኮንኖች ለሕዝባቸዉ የሚገቡትን የሰላም ብልፅግና ተስፋ ገቢር አድርገዉ አያዉቁም።

ያሁኖቹ ጄኔራሎች ደግሞ የሚገቡት ቃል ለ«ይዋል ይደ» ትዝብት እንኳን የማይበቃ «ቅጥፈት» መስሉ ወይም  ቅጥፈት ሆኖ አፍሪቃዊቱን ሰፊ ሐገር ቁልቁል እያሰገራት ነዉ።የወታደራዊዉ ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ጄኔራል ዳጋሎ እንዳሉት ጦሩ የዉዝግቡ አካል ካልሆነ የሚሊዮን ዜጎቹን ድምፅ ሰምቶ ስልጣኑን ለተመራጭ መሪ የማያስረክብበት ምክንያት በርግጥ እንቆቅልሽ ነዉ።

የካርቱም መንግስታት ደቡብ ሱዳን፣ ዳርፉር፣ ይሁን ኮርዶፋን ከሸመቁ አማፂያን ጋር ሲዋጉ ዉጊያዉ የመንግሥት እና ያማፂያን ብቻ አልነበረም።ከሰላሳ ዘመን በላይ ባስቆጠረዉ በደቡብ ሱዳኑ ጦርነት

ከአዲስ አበባ እስከ ሞስኮ፣ ከካይሮ እስከ ሪያድ፤ ከለንደን እስከ ዋሽግተን ያሉ የሶሻሊስ፣ የአረብ፣የካፒታሊስት ሐገራት ሲራኮቱበት ነበር።የዳርፉሩን ዉጊያ ከቀድሞዉ የሊቢያ መሪ እስከ አሜሪካ የፊልም ተዋኞች ሲያንቦራጭቁት ነበር።

የሱዳን ሕዝብ ካለፈዉ ሕዳር ጀምሮ በአምባ ገነን ገዢዉ ላይ ያደረገዉ አመፅ ከታለመለት ግብ እንዳይደርስ ያጨናጎሉት የሱዳን ጄኔራሎች ብቻ አይደሉም።የካይሮ፣የሪያድና የአቡዳቢ ገዢዎች ጭምር እንጂ።ከሊቢያ እስከ ሶሪያ፣ ከግብፅ እስከየመን በየአካባቢዉ ብልጭ የሚሉ ሕዝባዊ አብዮቶችን ለማዳፋን ሲሽቀዳደሙ ሺዎችን የሚፈጁ፤የሚያፋጁት የሰወስቱ ሐገራት ገዚዎች ሱዳኖችኖችንም እርስበርስ እያላተሙ ነዉ።ለጥፋት።

ዋሽግተኖች «ለእግረ-መንገድ» ዲፕሎማሲ ረዳት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉን ወደ ካርቱም ከመላክ በላይ እስካሁን ያሉ፣ያደረጉ፣ያቀዱትም መኖር አለመኖሩን እናዉቅም።የደቡብ ሱዳን፣ የዳርፉር፣የአብዬ ጦርነት ግን የካርቱም ገዢዎችን አቅም ሥለሚያዳክም ለአሜሪካ ፖለቲከኞች አይደለም ለፊልም ተዋኞቻቸዉ ሳይቀር ጦርነታቸዉ ነበር።የካርቱም ገዢዎችን በጦር ወንጀለኝነት እስከ ማስከሰስ የደረሱትም ያለ ምክንያት አይደለም።

ሱዳኖች የጦር ጄኔራሎች፣ የሲቢል ፖለቲከኞች፣የሰራተኛ ማሕበራት ተወካዮች ብለዉ የገጠሙት ዉዝግብ የዋሑን ሱዳናዊ እየፈጀ፣ወጥቶ የመግባት ዋስትናዉን እያሳጣዉ ነዉ።ሱዳን መጨረሻዋ ሊቢያን፣ሶሪያን፣ የመንን ወይም ቱኒዚያን መሆን አለመሆኑ በርግጥ አይታወቅም።ሕዝቡ ያደባባይ ሰልፉን ለማቆም፣ የጦር ጄኔራሎቹም ሥልጣን ለማስረከብ ዝግጁ ዓይደሉም።

ጄኔራሎቹ ለሽማግሌም እስካሁን የሚመቹ አልሆኑም።የካይሮ፣ ሪያድ፣ አቡዳቢ ገዢዎች የሱዳንን ሕዝብ ወደ እልቂት ጠርዝ ሲገፉት የሚሊዮኖቹ ድምፅ ዋሽግተን፣ብራስልስና ለንደን ላይ ለመሰማት የሰለለበት ሰበብ ምክንያት በርግጥ ያስተዛዝባል። ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ