1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰብዓዊ ርዳታ ለቤንሻንጉል

ሰኞ፣ ጥቅምት 12 2011

ካለፈው መስከረም አጋማሽ ጀምሮ የትራንስፖርትም ሆነ የንግድ ግንኙነት ተቋርጦበት ወደሰነበተው የቤንሻንጉል ጉሙዙ ካማሺ ዞን ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ መግባታቸውን የክልሉ መንግስት አስታወቀ። ተሽከርካሪዎቹ ከስፍራው የደረሱት በመከላከያ ሰራዊት እጀባ ነው ተብሏል። 

https://p.dw.com/p/36yaz
Karte Äthiopien Ethnien EN

ተሽከርካሪዎቹ እህል፣ዱቄት፣ ዘይትና ሌሎችም እርዳታዎች ጭነዋል

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘላለም ጃለታ ለDW እንደተናገሩት ንብረትነታቸው የክልሉ የሆኑ ሶስት ተሽከርካሪዎቹ በዞኑ ውስጥ ወደሚገኙት ካማሺ እና ያሶ ወረዳዎች ገብተዋል። ተሽከርካሪዎቹ የምግብ እህል፣ ዱቄት፣ ዘይት እና ሌሎችንም እርዳታዎች ጭነው ወደ ስፍራው መጓዛቸውን ገልጸዋል። 
እርዳታው በካማሺ ዞን ውስጥ ላሉ “57 ሺህ 625 እርዳታ ፈላጊዎች ይከፋፈላል” ብለዋል።“እነዚህ እዚያው ካማሺ ውስጥ ወደ ጫካም ገብተው የነበሩ፣ ከገጠርም ወደ ከተማ ማዕከል ገብተው የነበሩ እንደዚሁም አስቤዛ ባለመግዛታቸው ሲቸግሩ የነበሩ የመንግስት ሰራተኞች እና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ናቸው” ሲሉ አቶ ዘላለም ለDW አስረድተዋል።
ተሽከርካሪዎቹ በከፍተኛ የመከላከያ ሰራዊት አጀብ ወደ ስፍራው መጓዛቸውን የገለጹት የጽህፈት ቤት ኃላፊው “መንገዱ አሁንም ቢሆን ማንኛውም ዜጋ በነጻነት የሚንቀሳቀስበት አይደለም” ሲሉ በአካባቢው ያለውን የጸጥታ ችግር አሳሳቢነት ጠቁመዋል። “በተለይ ከአሶሳ ወደ ካማሺ የሚወስደው መንገድ ችግር አለበት። ስራ የሚጠይቅ ነው” ይላሉ አቶ ዘላለም።    
ባለፈው መስከረም 16 አራት የካማሺ ዞን አመራሮች ከኦሮሚያ ክልል ስብሰባ ተሳትፈው ሲመለሱ ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ በካማሺ ዞንና በኦሮሚያ ክልል አጎራባች አካባቢዎች የሚኖሩ 44 ሰዎች ባልታወቁ ኃይሎች መገደላቸውን የክልሉ መንግስት አስታውቆ ነበር። የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ የሟቾቹን ቁጥር 74 ያደረሰው ሲሆን ከ90 ሺህ በላይ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰድደዋል ብሏል። እንደ አቶ ዘላለም ገለጻ በካማሺ ዞን ባሉ አምስት ወረዳዎች በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ መረጋጋት ሰፍኗል።

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ