1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ርዳታ ወደ ትግራይ ያለምንም እክል እየደረሰ ነዉ ተባለ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 4 2015

በትግራይ ክልል 23 አጋሮች በአየር እና በየብስ እያቀረቡት ያለው እርዳታ ያለምንም መደናቀፍ በስፋት መቀጠሉን የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ተናገረ። ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው ወደ ክልሉ ምግብና መድኃኒትን ጨምሮ 690 ሺህ ሊትር ነዳጅና ለሥራ ማስኬጃ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ተጓጉዟል።

https://p.dw.com/p/4Krq7
Äthiopien Tigray Konflikt Symbolbild
ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች የተጎዳውን ሕዝብ መደገፍ ሳይታጎል ቀጥሏል

በትግራይ ክልል እየቀረበ በሚገኘው የሰብዓዊ ድጋፍ ላይ እየተሳተፉ ነው የተባሉት 23 አጋሮች በአየር እና በየብስ እያቀረቡት ያለው እርዳታ ያለምንም መደናቀፍ በስፋት መቀጠሉን የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ተናገረ። ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው እስከ ሕዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ወደ ክልሉ ምግብ እና መድኃኒትን ጨምሮ 690 ሺህ ሊትር ነዳጅ እና ለሥራ ማስኬጃ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በአውሮፕላን ተጓጉዟል።

Humanitäre Krise im Norden Äthiopiens nimmt zu
ምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

በኢትዮጵያ ከ26 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በመጪው ዓመት እርዳታ ይፈልጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ እና ሁሉንም ፍላጎቶች ለማሟላት 3.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ከሰሞኑ የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው መረጃ ያሳያል። የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኢትዮጵያ በዘላቂነት ከተረጂነት ችግር እንድትወጣ ሕዝብ በሥራ መትጋት እና መተባበር ይጠበቅበታል ሲል ገልጿል።

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ እንዳሉት በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች የተጎዳውን ሕዝብ በመደበኛነት መደገፍ ሳይታጎል ቀጥሏል። ለትግራይ ክልል በመንግሥት እና በ 23 አጋር በተባሉ አካላት በየብስና በአየር በሦስት መተላለፊያ ወይም ኮሪደሮች ማለትም በአፋር አብአላ ፣ በጎንደር - ማይፀምሪ - ሽሬ፣ በኮምቦልቻ - ቆቦ - አላማጣ መስመሮች የሚቀርበው እርዳታ ያለምንም መደናቀፍ እየቀረበ ነው።

"እስከ ሕዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም ለትግራይ ክልል በመንግሥት እና በአጋር አካላት ለተረጂዎች የቀረበ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እንዲሁም ነዳጅ አለ። ይህን በሚመለከት ምግብ እና አልሚ ምግብ 89 ሺህ 217.80 ሜትሪክ ቶን በየብስ ተጓጉዟል። መድኃኒት 1222 ሜትሪክ ቶን ሄዷል። ነዳጅ 690 ሺህ ሄዷል። ለሥራ ማስካጃ 576 ሚሊዮን ብር ወደ ሽሬ እና መቀሌ በአየር ተልኳል" ብለዋል።

 Äthiopien humanitäre Hilfe
ምስል AP Photo/picture alliance

ኮሚሽኑ ከሳምንታት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተቋሙን የሦስት ወራት የሥራ ክንውን ሲያቀርብ "በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ወደ 8.8 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች እርዳታ ለማቅረብ ተጨማሪ 13 ቢሊዮን ብር ምደባ እንደሚያስፈልገው" ተናግሮ ነበር። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 22.1 ሚሊዮን ዜጎች እርዳታ ጠባቂ መሆናቸውም አስታውቆ ነበር። በተለይ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች የሚስተዋለውን ከፍተኛ መፈናቀል በመጥቀስ የተቋማቸውን የድጋፍ አቅርቦት የተጠየቁት አቶ ደበበ "በሌሎች ቦታዎች መርህን ተከትለን ነው ድጋፍ የምናቀርበው። በተፈጥሮም ይሁን ሰዎች በሚፈጥሩት ችግር ምክንያት የድጋፍ ጥያቄ ሲቀርብ በቅድሚያ የአካባቢው መስተዳድር ያግዛል ከአቅሙ በላይ ሲሆን ኮሚሽኑን ይጠይቃል። ያንን መሰረት አድርገን ጥያቄው በቀረበ በ 72 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ባለው አቅም ልክ ምላሽ እንሰጣለን። ሆኖም ይህ የሚሆነው እክል እስካልገጠመ ደረስ ነው። ጥያቄ ቀርቦልን ምላሽ ሳንሰጥ የቀረንበት ጊዜ የለም" ብለዋል። ሆኖም ዘላቂ መፍትሔ ላይ መተኮር እንዳለበትም ገልፀዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ሰሞኑን ባወጣው መረጃ በምዕራብ ወለጋ ከ106 ሺህ በላይ፣ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ደግሞ 116 ሺህ ተፈናቃዮች አሉ ብሏል። ለእነዚህ ተፈናቃዮች የኦሮሚያ ክልል ምን እያገዘ ነው የሚለውን ለማወቅ ወደ ክልሉ የሥራ ኃላፊ ደጋግመን ብንደውልም ምላሽ አልሰጡንም።

Symbolbild Äthiopien Ankunft des Konvois mit Hilfslieferungen in Tigray
ምስል Amanuel Sileshi/AFP

ወለጋ ውስጥ ጉተን በተባለው ከተማ አሁንም መፈናቀል መኖሩን የገለፁ አንድ እምኝ ሕዝብ አሁንም ችግር ውስጥ መሆኑን ገልፀዋል። "የጉትን ሕዝብ አሁን እየለቀቀ ነው። የከተማው ሕዝብ እየተፈናቀለ ነው። " በኢትዮጵያ ከ26 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በመጪው ዓመት እርዳታ ይፈልጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ እና ሁሉንም ፍላጎቶች ለማሟላት 3.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ አስታውቋል።

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ