1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ራዕይ የተጋሩ ኢትዮጵያዊያን ሀገር አቀፍ ሕዝባዊ ንቅናቄ በድርድሩ ተሳትፎ ሊኖረኝ ይገባል ማለቱ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 3 2014

ራዕይ የተጋሩ ኢትዮጵያውያን ሀገር አቀፍ ህዝባዊ ንቅናቄ የተባለው የፖለቲካ ድርጅት በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል ሊደረግ በታሰበው ድርድር ውስጥ ተሳትፎ ሊኖረኝ ይገባል ሲል ጠየቀ። ፓርቲው በተለይ ለምክትልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን እንዲሁም ለአፍሪካ ሕብረትና ለምዕራባዊያን አገራት ተወካዮች ይህንኑ በመጠየቅ ደብዳቤ ልኳል።

https://p.dw.com/p/4FK1j
Äthiopien Tigray | Hauptstadt Mekele
ምስል MICHAEL TEWELDE/AFP/Getty Images

ፓርቲው ለምክትልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ለአፍሪካ ሕብረትና ለምዕራባዊያን አገራት ተወካዮች ደብዳቤ ልኳል

ራዕይ የተጋሩ ኢትዮጵያውያን ሀገር አቀፍ ህዝባዊ ንቅናቄ የተባለው የፖለቲካ ድርጅት በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል ሊደረግ በታሰበው ድርድር ውስጥ ተሳትፎ ሊኖረኝ ይገባል ሲል ጠየቀ። ፓርቲው በተለይ ለምክትልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን እንዲሁም ለአፍሪካ ሕብረት እና ለምዕራባዊያን አገራት ተወካዮች በጻፈው ደብዳቤ ሁለቱ ወገኖች ብቸኛ የድርድር ሂደቱ ተሳታፊዎች መሆናቸው እንደማይገባ ገልጿል።

በሁለቱ ወገኖች ብቻ የሚደረግ ድርድር የትግራይን ሕዝብ ችግርም ሆነ የኢትዮጵያን ሰላም በዘላቂነት አያመጣም ብሏል ፓርቲው። ከ1967 ዓ. ም ጀምሮ በሕወሓት ያልተምለሱ ጥያቄዎች አሉን የሚለው ፓርቲው በድርድር ውስጥ ተሳታፌ የምሆን ከሆነ ሕወሓትንም ሆነ ብልፅግና ፓርቲዎችን የምጠይቃቸው ጥያቄዎች አሉኝ ብሏል። ምንም እንኳን አቀርባለሁ ያላቸውን ጥያቃዌች ለጊዜው ግልጽ ማድረግ ባይፈልግም።

የፓርቲው መስራች እና ሊቀምንበር አቶ ሊላይ ኃይለማርያም የጥያቄያቸው ዋና አላማ ምን እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ነሐሴ 19 ቀን 2013 ዓ.ም ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልላዊ ፓርቲነት የእውቅና ፈቃድ ያገኘው ራዕይ ፓርቲ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ፓርቲዎች የሚያነሱትን የተሳትፎ ጥያቄ እንደሚደግፍም አስታውቋል።

አቶ ሊላይ ኃይለማርያም በሁለቱ ወገኖች ማለትም በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል ሊደረግ የታቀደው የሰላም ውይይት ሁሉንም ወገኖች የማያሳትፍ ከሆነ በመሠረታዊነት የትግራይን ሕዝብ ችግርም ሆነ የኢትዮጵያን ሰላም በዘላቂነት አያረጋግጥም ብለዋል።

ሰባት መሠረታዊ አምዶች እንዳሉት የሚገልፀው ራዕይ ፓርቲ በፈጣሪ ማመን፣ ሰንደቅ አላማችን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ መሆኑን ማረጋገጥ፣ ከኢትዮጵያውያን ጋር ተፈቃቅሮ መኖር፣ ቀማኛነትን እና ጉቦኝነትን በትግራይ ክልል ማስወገድ፣ መሬት በግለሰቦች እጅ እንዲሆን ማድረግ እና ጾታዊ ጥቃቶችን ማስወገድ መሆናቸውን አሳውቋል።

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ