1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሥራ ፈላጊዎቹ ምሩቃን ስለ ሰኞው ምርጫ ምን ይላሉ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 12 2013

ለሰኞው ምርጫ ሽር ጉድ በምትለው ኢትዮጵያ ከአርባ አምስቱ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች እና የግል ከፍተኛ የትምህር ተቋማት በየአመቱ የሚመረቁ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ሥራ ማግኘት ይፈትናቸዋል። የምሩቃኑ ቁጥር እየጨመረ የኢትዮጵያም ኤኮኖሚ ለወጣቶቹ ፍላጎት ምላሽ መስጠት እየቸገረው ሲሔድ ቢታይም መፍትሔ አልተገኘም።

https://p.dw.com/p/3vDcd
Äthiopien | Straßenszene Debre Birhan
ምስል Eshete Bekele/DW

ሥራ ፈላጊዎቹ ምሩቃን ስለ ሰኞው ምርጫ ምን ይላሉ?

ከከፍተኛ የትምህር ተቋማት ተመርቀው ሥራ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በመጪዎቹ ወራት ሥልጣን ከሚቆጣጠረው መንግሥት ለበርካታ ጥያቄዎቻቸው ብዙ መልሶች ይሻሉ። ወደ ደብረ ብርሃን የተጓዘው 

ዛሬ ቅዳሜ ላምሮት ገብረ ሕይወት ልደቷ ነው። 23 አመት ሞላት። የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኬምስትሪ ምሩቅ ስትሆን ሥራ ፈላጊ ነች። በመጪው ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓም በሚደረገው ስድስተኛ የኢትዮጵያ አገራዊ ምርጫ ድምጽ ስትሰጥ የመጀመሪያዋ ይሆናል።

“የመጀመሪያዬ ስለሆነ፣ የማላውቀውን ላውቅ ስለሆነ የተለየ ነገር ይኖረዋል ግድ ነው” ትላለች ላምሮት ስለ ሰኞ የምርጫ ቀጠሮዋ ለዶይቼ ቬለ ስትናገር።

እንደ ላምሮት ሁሉ ሰኞ በደብረ ብርሐን ከተማ ከሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በአንዱ ቀጠሮ ከያዙ ወጣቶች መካከል ከሐሮማያ ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነት እና ተግባቦት በዚህ አመት የተመረቀችው በእምነት ተሾመ ከዚህ ቀደም በተካሔዱ ምርጫዎች ድምጽ ለመስጠት እድሜዋ አልደረሰም ነበር። እሷም እንደ ላምሮት ሰኞ የመምረጥ መብቷን ለመጀመሪያ ጊዜ ትጠቀማለች።

 “አንደኛ የመምረጥ መብቴን ወደ ተግባር ላውለው ነው። እሱን ተጠቅሜ ይመራኛል፣ ይጠቅመኛል፣ ለአገሬ ለውጥ ያመጣል ብዬ የማስበውን ነው የምመርጠው። ለሥራዬም ቢሆን ለራሴም ጥቅም ቢሆን ጥሩ ነገር ያመጣልኛል ብዬ አስባለሁ። ዴሞክረሲ ዴሞክራሲ የሚል ሽታም ስላለ ምን አልባት እውን ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ” የምትለው በእምነት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላ ሥራ ፍለጋ ከመጀመሯ በፊት በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርቷ ተስተጓጉሎ ተስፋ መቁረጥን ቀመስ አድርጋለች።

በእምነት እና  ጓደኞቿ መጋቢት 2012 የተቋረጠው ትምህርታቸው  ሕዳር 2013 ተጀምሮ ነው ከወራት በፊት የተመረቁት። ከዚያ ሥራ ፍለጋ ተጀመረ። ሁለት የራዲዮ ጣቢዎች ብቻ በሚገኙባት ደብረ ብርሃን በጋዜጠኝነት ለተመረቀችው በእምነት ሥራ ማግኘት ግን ፈታኝ ሆኗል።

“እዚህ በጋዜጠኝነት ሥራ እንደማላገኝ አውቃለሁ። የሚወጡት ማስታወቂያዎች በሙሉ ሶስት አመት አራት አመት የሥራ ልምድ ያለው ሰው ነው የሚፈልጉት። ብዙ እድል አለ ብዬ የማስበው አዲስ አበባ ነው። አዲስ አበባ ብዙ ማስታወቂያዎች ይወጣሉ አንድ ሁለት ቦታ አስገብቼ ነበር ግን አልጠሩኝም። የተመረቅኩት በጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ስለሆነ ምን አልባት በተግባቦት አገኛለሁ ብዬ ነው ተስፋ የማደርገው። ደብረ ብርሃን ላይ ያለው ሁለት ሚዲያ ነው። የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት አንድ የሥራ ማስታወቂያ ወጥቶ ነበር። ተፈትኜ ሳላልፍ ቀርቼ ነው” ስትል እስካሁን የሥራ ፍለጋው ያጓዛትን መንገድ ታስረዳለች።

Äthiopien | Straßenszene Debre Birhan
ምስል Eshete Bekele/DW

ፈተናው የበእምነት ብቻ አይደለም። ለሰኞው ምርጫ ሽር ጉድ በምትለው ኢትዮጵያ ከአርባ አምስቱ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች እና የግል ከፍተኛ የትምህር ተቋማት በየአመቱ የሚመረቁ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ሥራ ማግኘት ይፈትናቸዋል። የምሩቃኑ ቁጥር እየጨመረ የኢትዮጵያም ኤኮኖሚ ለወጣቶቹ ፍላጎት ምላሽ መስጠት እየቸገረው ሲሔድ ቢታይም መፍትሔ አልተገኘም። የኮሮና ወረርሽኝ የፈጠረው ተጽዕኖ ደግሞ ላምሮትን ለመሳሰሉ ምሩቃን ፈተናውን አወሳስቦታል።

“ሁለት ቦታ ሲቪዬን አስገብቺለሁ። በዚያ ላይ የምንሔድባቸው ኢንዱስትሪዎች ገና ሥራቸውን ያልጨረሱ ናቸው። ማስታወቂያ አላወጡም። ሁለት ቦታ ነው ሶስት ቦታ ማስታወቂያ ሲወጣ ቢያንስ ቢያንስ አንድ አመት የሥራ ልምድ ይጠይቃል” በማለት ትናገራለች።

 “እሱ ደግሞ እኛን አያካትትም ማለት ነው። ምንም ውጤት ቢኖር ምንም የመሥራት አቅሙ ቢኖር የሥራ ልምድ ግድ ነው። አዲስ ኢንዱስትሪ ስለሆነ ፍሬሽ ማስገባት ይከብደናል ስለሚሉ ሌላ ቦታ ነው የምንሞክረው። ለእሱ እድል አናገኝም” ብላለች ላምሮት

ላምሮት በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ዶክተር እንዳለ የተባሉ መምህር አቅም እንዳላቸው፣ ወጥተው መሥራት እንደሚችሉ እየነገሩ ተስፋ እንዳይቆርጡ የመከሯቸውን እያስታወሰች “እንታገላለን”  ትላለች። “ወደፊት ጥሩ ቦታ እደርሳለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ”  የምትለው ላምሮት ሰኞ ድምጽ ለመሥጠት ስትዘጋጅ የሰላም እና የጸጥታ ጉዳይ ትኩረት እንደሚያሻቸው ለዶይቼ ቬለ ተናግራለች።

“አሁን የሚያሸንፈው ፓርቲ ሰላም ላይ ነው መስራት ያለበት ብዬ አስባለሁ። የተማረውም ሁሉም ወጥቶ ሰርቶ የሚገባው ሰላም ሲኖር ነው። በሰላም ምክንያት ብዙ የተስተጓጎሉ ነገሮች አሉ። ሰላም ሲሆን ብዙ ሰው መስራት ያለበትን ሐሳቡ ይመጣለታል። ስራውም እድሉም የሌለው ሰላም ባለመኖሩ ይመስለኛል” በማለት አቋሟን ታብራራለች።

ሰላም እና ጸጥታ ስራ ፈላጊዋ በእምነት እንደ ላምሮት ሁሉ ትኩረት ከምትሰጣቸው ጉዳዮች ቀዳሚው ነው። ምርጫ አሸንፎ የሚመሠረት መንግሥት “የጸጥታ ሃይሎችን በማሰማራትም ሊሆን ይችላል ሰላምን ማስከበር አለበት ለምትለው በእምነት የኑሮ ውድነት እና የሥራ አጥነት ችግሮችም አንገብጋቢ ጥያቄዎች ናቸው።

“በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ስላሉ ኤኮኖሚውን በጣም ማስተካከል አለበት። በጣም ኑሮ ተወዷል። ሰዉ እያለቀሰ ያለው በእህል ውድነት ነው። ስለዚህ ኤኮኖሚውን ማረጋጋት አለበት ብዬ አስባለሁ። ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ ለእኛ ለተመረቅንውም ሆነ እስካሁን ሥራ አጥተው ለተቀመጡ ሰዎች ስራ ፈጥሮ እንኩ ሳይሆን መንገዱን ማመቻቸት አለበት ብዬ አስባለሁ” ብላለች።

በደብረ ብርሃ ከተማ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ብልፅግና ፓርቲ፣የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ-ፍትህ ፓርቲ ፣የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፣እናት ፓርቲ ፣ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ስድስት እጩዎች አቅርበዋል። ከስድስቱ አንዷ ብቻ እንስት ናቸው። ለአማራ ክልል ምክር ቤት ደግሞ ከኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በቀር አምስቱ ፓርቲዎች ሁለት ሁለት እጩዎች ከተማዋን ለሚወክሉ መቀመጫዎች ያወዳድራሉ።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ