1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሥመ ጥሩው የመብት ተሟጋች ጆን ልዊስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 11 2012

ጥቁር አሜሪካዊው የመብት ተሟጋች ጆን ልዊስ በ80 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ከሰልማ ወደ ሞንትጎሜሪ የጥቁሮችን የመምረጥ መብት ለማስከበር በተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ የመንግሥት ኃይሎች በፈጸሙት ጥቃት ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቆ ነበር።ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በአሜሪካ ወታደር ላልሆኑ ሰዎች የሚሰጠውን ከፍተኛ የነፃነት ሜዳይ አበርክተውላቸዋል

https://p.dw.com/p/3fX8q
USA I Demokrat John Robert Lewis gestorben
ምስል Getty Images/R. Diamond

ጥቁር አሜሪካዊው የመብት ተሟጋች ጆን ልዊስ በ80 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ከማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር ጎን ለሰብዓዊ መብት መከበር የተሰለፉት ጆን ልዊስ የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ሆነው እያገለገሉ ጭምር በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርገዋል።

የአሜሪካ ዴሞክራቲክ ፓርቲ አባል የነበሩት ልዊስ ካንሰር ታመው ሕክምና በመከታተል ላይ እንደነበሩ ባለፈው አመት ይፋ አድርገው ነበር። “ለነፃነት፣ ለዕኩልነት፣ እና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር በተመሳሳይ ዓይነት ትግል ውስጥ ነበርኩ” ያሉት ጆን ልዊስ ለካንሰርም ቢሆን በቀላሉ እጅ እንደማይሰጡ ሕመማቸውን ይፋ ሲያደርጉ ተናግረው ነበር።

በአሜሪካ የሕዝብ መጓጓዣዎች ጥቁሮች የሚደርስባቸውን መድሎ ለመታገል የ21 አመት ወጣት ሳሉ ፍሪደም ራይደርስ የተባለ ማኅበር ከመሰረቱት መካከል አንዱ ነበሩ። ከዚያ በኋላ በጥቁር አሜሪካውያን የፍትኅ እና የዕኩልነት ትግል ውስጥ ላቅ ያለ ሚና ከነበራቸው አንዱ ሆነዋል።

ማርቲን ሉተር ኪንግ “ሕልም አለኝ” የሚል ታዋቂ ንግግራቸውን ያደረጉበት እና በጎርጎሮሳዊው 1963 ዓ.ም. በዋሽንግተን የተካሔደ ሰልፍ ካስተባበሩ መሪዎች ወጣቱ ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ጆን ልዊስ ነበሩ።

USA I Demokrat John Robert Lewis gestorben
ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በአሜሪካ ወታደር ላልሆኑ ሰዎች የሚሰጠውን ከፍተኛ የነፃነት ሜዳይ በጎርጎሮሳዊው 2011 ዓ.ም. ለጆን ልዊስ አበርክተውላቸዋልምስል Getty Images/P. Martinez Monsivais

ከሰልማ አላባማ ወደ ሞንትጎሜሪ የጥቁሮችን የመምረጥ መብት ለማስከበር በተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ የመንግሥት ኃይሎች በፈጸሙት ጥቃት ጭንቅላታቸው ላይ ተመተው ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቆ ነበር። ከአምስት አመታት በፊት ከፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ጋር በጸጥታ ኃይሎች ጭንቅላታቸውን በተመቱበት በዚያው ድልድይ በድጋሚ ተሰልፈው ታሪኩን ዘክረዋል።

ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በአሜሪካ ወታደር ላልሆኑ ሰዎች የሚሰጠውን ከፍተኛ የነፃነት ሜዳይ በጎርጎሮሳዊው 2011 ዓ.ም. ለጆን ልዊስ አበርክተውላቸዋል።

ጆን ልዊስ በጎርጎሮሳዊው የካቲት 21 ቀን 1940 ዓ.ም. በአላባማ ትሮይ የተባለ ቦታ ተወለዱ። የመቀመጥ አድማዎችን በማስተባበር፤ ሰላማዊ የተማሪዎች የትግል ማኅበራትን በማቋቋም እና የፖሊስ የኃይል እርምጃዎችን የሚያወግዙ ዘመቻዎችን በመምራት በአሜሪካ የመብት ትግል ላቅ ያለ ሚና ተጫውተዋል። በጎርጎሮሳዊው 1986 ዓ.ም. የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ሆነው የተመረጡት ልዊስ ለመርኅ ጥብቅና በመቆማቸው ከፍ ያለ ክብር የሚቸራቸው ፖለቲከኛ ለመሆን በቅተዋል።