1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ እና የኢትዮጵያ ሥነ-ሥዕል

ሐሙስ፣ ሰኔ 23 2014

በአንድ ሃገር የሰለጠነ እይታዊ ባህል ያለዉን ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሥነ-ሥዕል ከፍተኛ ድርሻ አለዉ፤ የሰዉ ልጅ እዉቀትን ከሚገበይባቸዉ፤ ዓለምን ከሚተረጉምባቸዉ ከሚያትትባቸዉ እና ከሚዳኝባቸዉ ጉዳዮች አንዱ እይታዊ ጥበብ ነዉ። ለበርካታ ወጣት ሠዓልያን ያላቸዉን ክህሎት ያስተላለፉት ሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ ሲታወሱና ሲመሰገኑ ይኖራሉ።

https://p.dw.com/p/4D9cI
Äthiopien Kunst von Mehari Teshome
መሐሪ ተሾመ ምስል Mehari Teshome

የሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ ማስታወሻ

«በኢትዮጵያ የሥነ-ጥበብ ነገር፤ ያልተደራጀ ስርዓት ያልተበጀለት በመሆኑ፤ ጥበበኞቹ ሳይታገዙ እዉቅና ሳይሰጣቸዉ ያልፋሉ። የሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ ግን ሽልማትን አግኝተዉ  ነዉ ያለፉት። ህይወታቸዉን ሁሉ ሲሰሩት በነበረዉ በጎ ተግባር መንፈሳቸዉን አድሰዋል።   ያፈርዋቸዉ እና ያስተማሩዋቸዉ ሰዓሊዎች ሽልማቶቻቸዉ ናቸዉ። እዉቅናን በነሱ አግኝተዋል። ዘላለምም ሲታወሱ ይኖራሉ።  የአለ የሥነ-ጥበብ እና ዲዛይን ት/ቤት እራሱ ባለዉለታ ናቸዉ። »

Äthiopien Kunst von Leykun Girma
ሥዕል፤ ለይኩን ግርማምስል Leykun Girma

በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የአለ የሥነ-ጥበብ እና ዲዛይን ት/ቤ ዳይሬክተር ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ የተናገሩት ነዉ። ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥዕል ዘርፍ እድገት፤ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስላበረከቱትና በተለይ ለአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ለአለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ከዉጭ ሆነዉ ለረጅም ዓመታት የሥዕል ባለሞያዎችን በማነፅ የጀርባ አጥንት ሆነዉ ሲያገለግሉ ስለነበሩት ስለ ሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየትን ተከትሎ የተናገሩት ነበር። ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ፤ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘዉ በዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት አስተማሪ ነበሩ።  ከዝያም ለረጅም ዓመታት በመድሐንያለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ ጡረታ ከወጡ በኋላ ደግሞ በቤታቸዉ ዉስጥ ወጣት የሥዕል ተሰጥዖ ያላቸዉን ተማሪዎች እጆቻቸዉን ይዘዉ የቅብ ብሩሾቻቸዉ የገሩ እና በርካታ አንቱ የተባሉ ባለሞያዎችን ያፈሩ ሠዓሊ ነበሩ። ሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ ለግል ጥቅም ሳይሆን ሃገራቸዉን ባላቸዉ ሁሉ ያገለገሉ ነበሩ ሲሉ ተመሪዎቻቸዉ ያነስዋቸዋል። ተማሪዎቻቸዉ ቲቸር ተስፋዬ የሚልዋቸዉ፤ ሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ ኢትዮጵያ ባላት ሁለት የመንግሥት እና ሦስት የግል የሥዕል ትምህርት ቤቶች ብቁ እንዲሆኑ እና ገብተዉ እንዲማሩ፤ ተማሪዎችን ያሰልጥኑ የነበር። አቶ ተስፋዬ ጥበብን የሚያከብሩ አንድ ተቋም ነበሩ። ለዛሬዉ ህይወቴ ሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል ሲል የነገረን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአምስት ዓመታት በላይ፤ በፔንቲንግ ዲፓርትመንት ወይም በቀለም ቅብ ክፍል ዉስጥ ሲያገለግል የነበረዉ ሠዓሊ ተሰማ አስራት፤ አሁን ደግሞ በዚሁ የሞያ ዘርፍ በካታር አየር መንገድ ተቀጥሮ ዶሃ ካትር ነዋሪ ከሆነ ዓመታቶችን አስቆጥሮአል። በሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ቢያዝንም፤ ሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ በሥዕል ሞያ ባነፅዋቸዉ ልጆቻቸዉ ህያዉ እንደሆኑ አልደበቀም።

Äthiopien Kunst von Mehari Teshome
ሥዕል፤ መሐሪ ተሾመ ምስል Mehari Teshome
Äthiopien  Tesfaye Nigatu
ሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱምስል Privat

«ሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ፤ ለየት ያለ አመለካከት ያላቸዉ ሰዉ ናቸዉ። ጥበብን ለነፍሳቸዉ እርካታ ነበር የሚሰሩት።  ምንም አይነት እዉቅናን እና የግል ጥቅምን ሳይፈልጉ ራሳቸዉን ደብቀዉ፤ ከቤተሰቦቻቸዉ ከራሳቸዉ ሰዓታቸዉን ወስደዉ፤ ዛሬ አንቱ ለተባሉ የኢትዮጵያ ሠዓልያን እና ለጥበቡ፤ ህይወታቸዉን የከፈሉ ሠዓሊ ነበሩ። ሥዕል ከቁም ነገር የማይቆጠርበት እና እንደ ትርፍ ነገር ተደርጎ በሚቆጠርበት ሃገር ያደግን ሰዎች ነን። ያስተምሩበት የነበረዉ በመድኃኒዓለም ትምህርት ቤት ለማስተማርያ የሚሆን ክፍል ያገኙት በልመና ነበር። የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ ቀና ስለነበር ክፍል  ሰጥዋቸዉ ነበር። በየወሩ ለምንማርበት እንከፍል የነበረዉ፤ ለቁሳቁስ መግዣ ያህል የሚሆን ገንዘብ ብቻ ነበር  የምንሰጠዉ። በጣም ትንሽ ብር ነበር። ወደ 20 ብር አካባቢ ይሆን ነበር። ወደ ከፍተኛ የሥዕል ተቋም ወደ ሆነዉ ወደ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ለመግባት ተማሪ ሁሉ መጀመርያ እሳቸዉ ጋር ተምሮ ነበር ወደ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ለመግባት ፈተና የሚቀመጠዉ። ቲቸር ተስፋዬ እከሌ ከከሌ ሳይሉ ለነፍሳቸዉ ይሰሩ የነበሩ በጣም ጥሩ አስተማሪ ነበሩ።»  

Äthiopien Kunst von Leykun Girma
ሥዕል፤ ለይኩን ግርማምስል Leykun Girma

ሠዓሊ ተሰማ አስራት፤ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የአለ የሥነ-ጥበብ እና ዲዛይን ት/ቤትን እንዳጠናቀቀ፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአምስት ዓመታት በላይ፤ በፔንቲንግ ዲፓርትመንት ወይም በቀለም ቅብ ክፍል ዉስጥ አገልግሎአል። አሁን ደግሞ በዚሁ የሞያ ዘርፍ በካታር አየር መንገድ ተቀጥሮ ዶሃ ካትር ነዋሪ ከሆነ ዓመታቶችን አስቆጥሮአል። ለስራ ወደ ጀርመን ወደ ሉፍታንዛ ድርጅት ሃምቡርግ ከተማ ይመጣ እንደነበርም ተናግሮአል።

ሠዓሊ ተሰማ አስራት፤የጥበብ አባታችን ለሚላቸዉ ለሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ አንድ የማስታወሻ ፕሮግራም ለማዘጋጀት ከአጋር ሠዓልያን ጋር በመነጋገር ላይ እንደሆን ጠቁሞአል። በሌላ በኩል እዉቀትን እንዴት ማስተላለፍ እንደሚገባ ያሳዩን ሠዓሊ ተስፋዬ እኛም ይህን አርአያ ይዘን መቀጠል እንዳለብን አስተምረዉናል፤ አኛን ተክተዉ፤ ታላላቅ ባለሞያዎችን አፍርተዉ በመሄዳቸዉ ቲቸር ተስፋዬ ሞቱ አልልም ሲል ገልፆአል። 

Äthiopien Kunst von Mehari Teshome
መሐሪ ተሾመ ምስል Mehari Teshome

ሌላዋ የሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ ተማሪ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የአለ የሥነ-ጥበብ እና ዲዛይን ት/ቤ መምህርት እና ሠዓሊ ሩት አድማሱ ትባባላለች። የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ ለሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ የእናመሰግናለን ዝግጅት ካደረጉት ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት።

«እኔ አቶ ተስፋዬ ንጋቱ ተማሪ ነኝ። መድኃኒያለም ቤታቸዉም ሲያስተምሩ ሁለቱም ጋር ተምርያለሁ።  ሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ ጡረታ እስኪወጡ በመድኃኒያለም ትምህርት ቤት አስተምረዋል። ጡረታ ከወጡ በኋላ ደግሞ ቤታቸዉ ዉስጥ ሳሎን ቤታቸዉን፤ የስእል ማስተማርያ ክፍል አድርገዉ ተማሪዎቻቸዉን በሥዕል ትምህርት አንፀዋል። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሠዓልያን በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የከፍተኛ ትምህርታቸዉን ከመጀመራቸዉ በፊት መጀመርያ አቶ ተስፋዬ ጋር ሄደዉ የሥዕልን መሰረታዊ ነገር ተምረዉ ነበር ለመግብያ ፈተና የሚቀመጡት። አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ዉስጥ የሚገኘዉ የሥዕል ትምህርት ቤት በሥዕል ትምህርት የከፍተኛ ትምህርትን ለመከታተል ከሚመዘገቡ ከ 1300  ተፈታኞች መካከል ወደ 25 የሚሆን ተማሪዎችን ብቻ በመቀበሉ አልፎ ለመግባት ያለዉ ትግል እጅግ ከፍተኛ ነዉ ። አቶ ተስፋዬ ንጋቱ ጋር የስዕል መሰረታዊ ትምህርትን ተምሮ አዲስ አበባ አለ የሥዕል ትምህርት ቤት የገባ፤ ሁሉን ነገር አዉቆ ስለሚገባ ምንም የሚቸግረዉ ነገር አይኖርም። ወደ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ለመግባት ለፈተና ከመቅረቡ በፊት ተማሪዉ ወደ አቶ ተስፋዬ ጋር የሚሄደዉ ማብቃት ስለሚችሉ ነዉ። ይህን ደግሞ ተማሪዉ ሁሉ ያዉቅ ነበር። ፈተናዉን ተፈትነን ለቃለ ምልልስ ስንቀርብ ከየት እንደመጣን ሲጠይቁን ከአቶ ተስፋዬ ንጋቱ ጋር ብለን ከመለስን መሰረታዊ ትምህርቶችን እንደተማርን ፈታኞቻችን ጠንቅቀዉ ያዉቁም ነበር። በመኖርያ ቤታቸዉ ሳሎን ቤታቸዉን የሥዕል ማስተማርያ ክፍል አድርገዉት ፤ በአንድ ወገን ሞዴል የሚሰሩ፤ በአንድ በኩል ደግሞ ኮፒ የሚሰሩ ባለሞያዎች ሥዕልን የሚለማመዱበት ነበር። አቶ ተስፋዬ ጋር ሥዕልን የምንማረዉ በሳምንት አምስት ቀን እና ሙሉ ቀን ነበር። ምሳችንን ይዘን እየሄድን እዝያዉ እሳቸዉ ጋር እየዋል ነበር የምንለማመደዉ።»  

Äthiopien Kunst von Mehari Teshome
ሥዕል፤ መሐሪ ተሾመ ምስል Mehari Teshome

እንደ ሠዓሊ ሩት አድማሱ ሁሉ ሠዓሊ፤ መሐሪ ተሾመ እንዲሁም ለይኩን ግርማ ስለ ሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ ተሞክሮዋቸዉ በሰፊዉ አጫዉተዉናል። ሠዓሊ መሐሪ ተሾመ በአሁኑ ወቅት የራሱ ስቱድዮ ያለዉ ሙሉ ጊዜዉንም በሥዕል ስራ እንደሚያሳልፍ ነግሮናል። የሥዕል ጥበብን ያገኘዉ ከመምህሩ ከአቶ ተስፋዬ ንጋቱ ጋር እንደነበር ሲናገር በኩራት ነዉ።

በአንድ ሃገር የሰለጠነ እይታዊ ባህል ያለዉን ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሥነ-ሥዕል ከፍተኛ ድርሻ አለዉ፤ የሰዉ ልጅ እዉቀትን ከሚገበይባቸዉ፤ ዓለምን ከሚተረጉምባቸዉ ከሚያትትባቸዉ እና ከሚዳኝባቸዉ ጉዳዮች አንዱ እይታዊ ጥበብ ነዉ፤ ያሉን በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የአለ የሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ት/ቤ ዳይሬክተር ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ ፤ መምህር ተስፋዬ ንጋቱ፤ በኢትዮጵያ የበርካታ ወጣት ሠዓልያንን የእይታ ባህል በማሰልጠን እና በማጎልበት ረገድ ያላቸዉን ጥበብ አስተላልፈዉ፤ በስራቸዉ ህያዉ ሆነዉ ሲታወሱና ሲመሰገኑ ይኖራሉ ሲሉ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ከመቶ ሚሊዮን ለሚበልጥ ህዝብ አምስት የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ብቻ መኖሩን ግን አሳዛኝ ብለዉታል። 

Äthiopien  Tesfaye Nigatu
ሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱምስል Privat

ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረባቸዉ ህመም በ 89 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት መምህር ተስፋዬ ንጋቱ፤ የአራት ሴቶች እና የአራት ወንዶች አባት እንዲሁም የአምስት የልጅ ልጆች አያት ነበሩ። ሠዓሊ ተስፋዬ ንጋቱ በንጉሱ ዘመን ባገኙት የትምህርት እድል በሥነ ስዕል የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን በቀድሞዋ ቼኮስሎቫክያ እንዳጠናቀቁ የህይወት ታሪካቸዉ ያሳያል። ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሚገኘዉ በጣት ለሚቆጠረዉ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት የጀርባ አጥንት ሆነዉ፤ በህይወት እስከተለዩ ድረስ ያገለገሉት እና በርካታ ድንቅ ሠዓልያንን የተኩት መምህር ተስፋዬ ንጋቱን ለመዘከርና ቤተሰቦቻቸዉን ለመርዳት በኢትዮጵያ የሠዓልያኑ ዓለም የእናመሰግናለን መድረክ ለማዘጋጀት እቅድ እንደያዘ ተማሪዎቻቸዉ ተናግረዋል።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ